ትዳርን የተሳካ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ትዳርን የተሳካ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
“ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ [ፈጠራቸው።] ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’ . . . ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 19:4-6 ላይ እንደተናገረው።
የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በሚለዋወጡበት በዚህ ዓለም ሰዎች ለትዳር ትልቅ ቦታ መስጠታቸው እየቀረ መጥቷል። ብዙ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩት ውበታቸው እስኪረግፍ ወይም ችግር እስኪያጋጥማቸው ድረስ ነው፤ ምናልባትም ለመለያየት ወይም ለፍቺ የሚያበቃቸው ችግር ያን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል። የሚያሳዝነው ነገር ብዙውን ጊዜ ልጆች በዚህ ምክንያት ለከባድ የስሜት ቀውስ የሚዳረጉ መሆናቸው ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ ሁኔታ ብዙም አያስገርማቸውም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ስለምንኖርበት ‘የመጨረሻ ቀን’ ሲናገር ቤተሰቦችን አንድ ላይ የሚያስተሳስሩት እንደ ታማኝነት፣ እውነተኛ ፍቅርና ተፈጥሯዊ ፍቅር ያሉ ባሕርያት እየጠፉ እንደሚሄዱ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ታዲያ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መሸርሸራቸውና ይህ ሁኔታ በቤተሰብ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አያሳስብህም? ትዳርንስ ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ?
እንዲህ ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ሐሳብ ማግኘት ትችላለህ፤ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዘመን የማይሽረው ምክር በርካታ ባለትዳሮችን እየረዳ ነው። እስቲ በዚህ ርዕስ ውስጥ ትዳር ስኬታማ እንዲሆን ሊረዱ የሚችሉ ቢያንስ አምስት መመሪያዎችን እንመልከት። *
ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ የሚረዱ አምስት ቁልፍ ነገሮች
(1) ጋብቻን ቅዱስ ጥምረት እንደሆነ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ከሥዕሉ በታች ከተጠቀሰው የኢየሱስ ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ኢየሱስም ሆነ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ጋብቻን ቅዱስ ጥምረት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በጥንት ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ወንዶች፣ ወጣት ሴቶችን ለማግባት ሲሉ ሚስቶቻቸውን በፈቱ ጊዜ አምላክ ጠንከር ያለ ምክር መስጠቱ ጋብቻን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ያሳያል። አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ወጣት ሳለህ ላገባሃት ሚስትህ የገባኸውን ቃል ኪዳን አፍርሰሃል። እሷ አጋርህ ስትሆን አንተም ሚልክያስ 2:14-16 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ ትዳርን አቅልሎ የማይመለከት ከመሆኑም ሌላ ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን የሚይዙበትን መንገድ ልብ ብሎ ይከታተላል።
ለእሷ ታማኝ ሆነህ ለመኖር በአምላክ ፊት ቃል ገብተህላት የነበረ ቢሆንም የገባህላትን ቃል አፍርሰሃል።” ከዚያም ይሖዋ “ከእናንተ መካከል አንዱ በሚስቱ ላይ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ መፈጸሙን እጠላለሁ” በማለት ጠንከር ያለ ምክር ሰጠ። ((2) ኃላፊነት የሚሰማህ ባል ሁን። ቤተሰብን የሚመለከቱ አስፈላጊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያሳልፍ ሰው መኖር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይህን የሥራ ድርሻ የሰጠው ለባል ነው። ኤፌሶን 5:23 ‘ባል የሚስቱ ራስ ነው’ ይላል። ይሁን እንጂ ባል ራስ ነው ሲባል አምባገነን ይሆናል ማለት አይደለም። ባል ከሚስቱ ጋር “አንድ ሥጋ” እንደሆነ ማስታወስ የሚኖርበት ሲሆን ሊያከብራትና ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሊያማክራት ይገባል። (1 ጴጥሮስ 3:7) መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል” የሚል ምክር ይሰጣል።—ኤፌሶን 5:28
(3) ባልሽን የምትደግፊ ሁኚ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሚስትን ለባሏ “ረዳት” እንደሆነች አድርጎ ይገልጻታል። (ዘፍጥረት 2:18) ረዳት ሆና በምታከናውነው ነገር ለትዳሯ ስኬታማነት የበኩሏን አስተዋጽኦ ታበረክታለች። የባሏ ረዳት ወይም ማሟያ እንደመሆኗ መጠን ከእሱ ጋር ከመፎካከር ይልቅ ፍቅራዊ ድጋፍ ትሰጠዋለች፤ በዚህ መንገድ በቤተሰቡ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ትችላለች። ኤፌሶን 5:22 “ሚስቶች . . . ለባሎቻቸው ይገዙ” ይላል። ይሁንና አንዲት ሚስት በአንድ ጉዳይ ላይ ከባሏ ጋር ባትስማማስ? በዚህ ጊዜ ባሏ እሷን እንዲያነጋግራት በምትፈልግበት መንገድ ይኸውም አክብሮት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ አስተያየቷን መግለጽ ትችላለች።
(4) ምክንያታዊ ሁኑ፤ እንዲሁም ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጠብቁ። ከትዳር ጓደኛሞች መካከል አንዱ አሳቢነት ወይም ደግነት የጎደለው ቃል በመናገሩ አሊያም የገንዘብ ወይም ከባድ የጤና ችግር በመከሰቱ ምክንያት ወይም ልጆችን ማሳደግ በሚያስከትለው ውጥረት የተነሳ በትዳር ውስጥ ችግር ሊፈጠር ይችላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያገቡ ሰዎች “በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ያም ሆኖ መከራ ወይም ችግር ስላጋጠመ ብቻ ትዳሩ ሊናጋ አይገባውም። እንዲያውም ሁለት ሰዎች ከተዋደዱ እና አምላካዊ ጥበብ ካላቸው አለመግባባት ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም ይኖራቸዋል። ታዲያ በቤተሰባችሁ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ጥበብ አላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል።”—ያዕቆብ 1:5
(5) አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሁኑ። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ላለው ፍቺ ብቸኛ መሠረት ከሆነው ከዝሙት ወይም ከጋብቻ ውጭ ከሚፈጸም የፆታ ግንኙነት የበለጠ ትዳርን የሚያናጋ ነገር የለም። (ማቴዎስ 19:9) መጽሐፍ ቅዱስ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤ ምክንያቱም አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋል” ይላል። (ዕብራውያን 13:4) ታዲያ ባልና ሚስት የፆታ እርካታ ለማግኘት ከትዳራቸው ውጪ ሌላ ሰው ለመፈለግ እንዳይፈተኑ ምን ማድረግ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ ሚስትም ብትሆን ለባሏ እንደዚሁ ታድርግለት” በማለት ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 7:3, 4
አንዳንድ ሰዎች እነዚህን አምስት መመሪያዎች ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ወይም ዘመን ያለፈባቸው እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኘው ውጤት ያማረ ነው። እንዲያውም እነዚህን መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘው ውጤት በማንኛውም የሕይወቱ ዘርፍ የአምላክን መመሪያ ለመከተል የሚጥር ሰው ከሚያገኘው ውጤት ጋር ይመሳሰላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” (መዝሙር 1:2, 3) “ሁሉ” የሚለው ቃል ስኬታማ የሆነ ትዳርንም ይጨምራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 ከትዳር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የየካቲት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።
ይህን አስተውለኸዋል?
● አምላክ ለፍቺ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?—ሚልክያስ 2:14-16
● አንድ ባል ሚስቱን መያዝ ያለበት እንዴት ነው?—ኤፌሶን 5:23, 28
● ትዳር ስኬታማ እንዲሆን የሚረዳው ከየት የሚገኘው ጥበብ ነው?—መዝሙር 1:2, 3