ከምንም በላይ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ጥያቄ
ከምንም በላይ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ጥያቄ
“የሰው ልጅ ወደ ሕልውና ከመጣበት ዘመን ጀምሮ ‘አምላክ አለ?’ ከሚለው ጥያቄ ይበልጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ጥያቄ ኖሮ ያውቃል?” ይህን ጥያቄ ያነሱት ፍራንሰስ ሴለርስ ኮሊንስ የተባሉ የጄኔቲክስ ተመራማሪ ናቸው። በእርግጥም እኚህ ሰው ያነሱት ነጥብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። አምላክ የለም ከተባለ ሕይወት የአሁኑ ብቻ ይሆን ነበር፤ ከዚህም ሌላ ሥነ ምግባርን በተመለከተ መመሪያ ሊሰጥ የሚችል የበላይ አካል አይኖርም።
አንዳንድ ሰዎች የአምላክን መኖር የሚጠራጠሩት ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት በአምላክ ስለማያምኑ ነው። ይሁን እንጂ የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው አንዳንድ ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ አመለካከቶች እንኳ በጣም የተሳሳቱ ሊሆኑ ይችላሉ።
የሚያሳዝነው ነገር ብዙዎቹ የዓለም ሃይማኖቶች፣ የተረጋገጠ ማስረጃ ካላቸው ሳይንሳዊ ሐቆች ጋር የሚጻረር ነገር በማስተማር ተጨማሪ ግራ መጋባት ፈጥረዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው፣ አምላክ ዓለምን የፈጠረው ከተወሰኑ ሺህ ዓመታት በፊት እንደሆነና ይህንንም ያደረገው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ መሆኑን የሚገልጸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ትምህርት ነው።
ብዙ ሰዎች እርስ በርስ በሚጋጩት ንድፈ ሐሳቦችና ፍልስፍናዎች ግራ ስለሚጋቡ ስለ አምላክ ሕልውና ሐቁን ለማወቅ የሚያደርጉትን ጥረት እርግፍ አድርገው ይተዉታል። ይሁን እንጂ ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ አስተማማኝ መልስ ከማግኘት ይበልጥ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድርና ጠቃሚ የሆነ ምን ነገር ሊኖር ይችላል? እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን አምላክን አይተነው አናውቅም፤ እንዲሁም አጽናፈ ዓለምና ሕይወት ያላቸው ነገሮች ወደ ሕልውና ሲመጡ አላየንም። ስለዚህ በአምላክ መኖር የምናምንም ሆንን የማናምን፣ አመለካከታችን በመጠኑም ቢሆን እምነት ይጠይቃል። እምነታችን ግን በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
እውነተኛ እምነት በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው
እምነት፣ በተወሰነ መጠንም ቢሆን በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ሥራ የምንቀጠረው ደመወዝ እንደምናገኝ ስለምንተማመን ነው። እህል የምንዘራው ዘሩ እንደሚያድግ እርግጠኞች ስለሆንን ነው። ከዚህም ሌላ ወዳጆቻችንን እናምናቸዋለን። እንዲሁም ጽንፈ ዓለም በሚመራባቸው የተፈጥሮ ሕግጋት እንተማመናለን። ከላይ በተዘረዘሩት ነገሮች ላይ ያለን እምነት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በማስረጃ የተደገፉ ናቸው። በተመሳሳይም በአምላክ ሕልውና የምናምነው በጠንካራ ማስረጃ ላይ ተመሥርተን ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 11:1 ላይ “እምነት . . . እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው” ይላል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “እምነት. . . የማናያቸው ነገሮች እውን መሆናቸውን እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል” ይላል። (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ነጥቡን ለማብራራት እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ሰው በባሕር ዳርቻ ላይ እየተንሸራሸረ ሳለ በድንገት መሬቱ ሲናወጥ ተሰማው። ከዚያም ውኃው ወደ ባሕሩ ሲሸሽ ተመለከተ። በመሆኑም ይህ ክንውን ሱናሚ ሊመጣ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ተገነዘበ። በዚህ ምሳሌ ላይ የመሬቱ መናወጥና የውኃው መሸሽ በአንድነት ሆነው ገና ላልታየው እውነታ ማለትም ለሱናሚው መምጣት “ተጨባጭ ማስረጃ” ናቸው። ግለሰቡ ስለዚህ ጉዳይ ያለው እውቀት ሱናሚ ሊመጣ እንደሆነ እንዲያምን ስለሚያደርገው ሕይወቱን ለማትረፍ ከፍ ወዳለ ቦታ ይሸሻል።
በአምላክ መኖር ማመንም በእውቀት ላይ የተመሠረተና አሳማኝ በሆነ ማስረጃ የተደገፈ መሆን አለበት። አምላክን በዓይንህ ‘ባታየውም እውን ሊሆንልህ’ የሚችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው። እንዲህ ያለውን ማስረጃ ለመመርመርና ለመገምገም የሳይንስ ሊቅ መሆን ይኖርብሃል? የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ሎሬት ቭላዲሚር ፕሬሎግ “የኖቤል ተሸላሚዎች ስለ አምላክ፣ ስለ ሃይማኖትና ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ሕይወት ከሌሎች ሰዎች የበለጠ እውቀት የላቸውም” ብለዋል።
ቅን ልቦና እንዲሁም ለእውነት ያለህ ጥማት ማስረጃዎቹን አእምሮህን ክፍት አድርገህ እንድትመረምር ሊያነሳሱህ ይገባል፤ እነዚህ ማስረጃዎች ወደ ትክክለኛው መደምደሚያ እንዲመሩህ ምኞታችን ነው። ታዲያ ልንመረምራቸው የምንችል ምን ማስረጃዎች አሉ?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገበሬዎች የዘሩት ዘር እንደሚያድግ እምነት አላቸው