ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በጀርመን አገር ከ10 ሕፃናት መካከል 7ቱ የኢንተርኔት “ተጠቃሚዎች” ናቸው። ወላጆቻቸው የኢንተርኔት ድረ ገጽ ላይ ስለ ሕፃናቱ አጭር መረጃ ያሰፍራሉ፣ የኢሜይል አድራሻ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ ወይም ፎቶግራፋቸውን አሊያም የአልትራሳውንድ ምስሎቻቸውን ድረ ገጹ ላይ ያስቀምጡላቸዋል። ይሁንና ልጆቹ ሲያድጉም ኢንተርኔት ላይ የወጣው ምስል ምንጊዜም ከእነሱ ጋር ስለሚያያዝ ወላጆች በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ባለሞያዎች ይመክራሉ።—ቤቢ ኡንት ፋሚሊያ፣ ጀርመን
መንግሥት ያወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በሩሲያ በየዓመቱ 14,000 ሴቶች በቤት ውስጥ በሚፈጸም የኃይል ጥቃት ምክንያት ይሞታሉ።—ሪያ ኖቮስቲ፣ ሩስያ
በኤቨረስት ተራራ ላይ ከ6,858 ሜትር እስከ 7,752 ሜትር ባለው ከፍታ ላይ የሚጥለው በረዶ አርሰኒክ እና ካድሚየም የያዘ ሲሆን እነዚህ ኬሚካሎች በረዶው ውስጥ የሚገኙበት መጠን ለመጠጥ ውኃ አደገኛ ነው። ለዚህም ምክንያቱ የሰው ልጆች ያስከተሉት ብክለት እንደሆነ ይታሰባል።—ሶይል ሰርቬይ ሆራይዘንስ፣ ዩ ኤስ ኤ
በቻይና መጽሐፍ ቅዱሶችን እንዲያትም የተፈቀደለት ብቸኛው ኩባንያ በቅርቡ 80 ሚሊዮንኛ ቅጂውን አትሞ አውጥቷል። ኩባንያው በየወሩ 1 ሚሊዮን መጽሐፍ ቅዱሶችን የሚያትም ሲሆን ይህም በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከሚታተመው አንድ አራተኛ ያህል ነው።—ዚንህዋ፣ ቻይና
“ከአሥር በመቶ በትንሹ የሚበልጡ (10.1 በመቶ) አሜሪካውያን በካቶሊክ እምነት ውስጥ ቢያድጉም ትልቅ ሰው ከሆኑ በኋላ ቤተክርስቲያኒቱን ለቅቀው ወጥተዋል።”—ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር፣ ዩ ኤስ ኤ
በ2010 የደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች
አንድ የታወቀ የኢንሹራንስ ኩባንያ በ2010 በመላው ዓለም 950 የተፈጥሮ አደጋዎች እንደደረሱ መዝግቧል፤ ይህ አኃዝ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአማካይ በየዓመቱ ከደረሱት የተፈጥሮ አደጋዎች (785 ነበሩ) የበለጠ ነው። ባለፈው ዓመት ከደረሱት የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ የከፉት አምስት አደጋዎች የሚከተሉት ናቸው፦ በሄይቲ፣ በቺሊና በቻይና የደረሱት የመሬት መናወጦች፣ ፓኪስታንን ያጥለቀለቀው ጎርፍ እንዲሁም በሩሲያ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ከፍተኛ ሙቀትና የአየር መበከል። በሰሜን አውሮፓ በአይስላንድ ከፈነዳው እሳተ ገሞራ የወጣው አመድ ያስከተለው ቀጥተኛ ጉዳት ያን ያህል ባይሆንም በአየር ትራንስፖርት ላይ ከባድ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአውስትራሊያ በረዶ የቀላቀሉ ሁለት ከባድ ወጀቦች ከ2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የገንዘብ ኪሣራ አስከትለዋል። “ኢንሹራንስ ያልሸፈናቸውን ጉዳቶችን ጨምሮ የደረሰው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ባለፈው ዓመት ከነበረው 50 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዘንድሮ ወደ 130 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ብሏል” በማለት የለንደኑ ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል።
ኒያንደርታሎች እንደ እኛ ነበሩ?
“ኒያንደርታሎች ከሆሞ ሳፒየንስ [ከሰዎች] እንደሚያንሱ የሚገልጸው ለብዙ ዘመን ተቀባይነት አግኝቶ የቆየ አመለካከት እየተቀየረ ነው፤ ምክንያቱም እኛ ብቻ እንዳሉን ይታሰቡ የነበሩ ችሎታዎች እነርሱም እንደነበሯቸው ታውቋል” በማለት ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። በቅርብ የተደረሰባቸው ግኝቶች እንደሚያሳዩት ኒያንደርታሎች መጠለያና ምድጃ ይሠሩ፣ በእሳት ይጠቀሙ፣ ልብስ ይለብሱ፣ ምግብ ያበስሉ፣ መሣሪያዎችን ይሠሩ እንዲሁም ጦራቸውን ከእጀታው ጋር የሚያያይዙበት ሙጫ ያዘጋጁ ነበር። በተጨማሪም የታመሙ ግለሰቦችን ይንከባከቡ፣ ትርጉም ያላቸው ጌጣ ጌጦችን ያደርጉና ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች ተገኝተዋል። በሴይንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የፊዚካል አንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሪክ ትሪንከስ “ኒያንደርታሎች እንደ እኛ ነበሩ፤ ምናልባትም የማሰብ ችሎታቸው ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።