በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነው የትኛው አመለካከት ነው?

ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነው የትኛው አመለካከት ነው?

ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነው የትኛው አመለካከት ነው?

በምድራችን ላይ ሕይወት ሲጀምር የተመለከተ አንድም ሰው የለም። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሕያው ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ ሲቀየር ለምሳሌ በደረቱ የሚሳብ እንስሳ ወደ አጥቢ እንስሳ ሲለወጥ ያየም የለም። * ስለዚህ ስለ ሕይወት አመጣጥ አንድ መደምደሚያ ላይ መድረስ የምንችለው ያሉትን ማስረጃዎች መሠረት በማድረግ ነው። እንዲሁም ማስረጃዎቹን እኛ ወደምንፈልገው አቅጣጫ ከማጣመም ይልቅ የሚያሳዩትን ነገር እንዳለ መቀበል ይኖርብናል።

ይሁን እንጂ ብዙ አምላክ የለሾች በማቴሪያሊዝም ንድፈ ሐሳብ ስለሚመሩ ማለትም ሕይወት የተገኘው ቁሳዊ ከሆነ ነገር ብቻ እንደሆነ ስለሚያምኑ ማስረጃዎቹን የሚመረምሩት የተዛባ አመለካከት ይዘው ነው። የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ሪቻርድ ለዎንተን “ማቴሪያሊዝምን ለመቀበል ቀደም ሲል ቁርጥ አቋም ይዘናል” በማለት ጽፈዋል። እነዚህ ምሁራን የማቴሪያሊዝም ንድፈ ሐሳብ ትክክል ለመሆኑ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ ስለሌላቸው “አምላክ ደጃፋችን ላይ እንዲደርስ አንፈልግም” እንዳሉ ሪቻርድ ለዎንተን ገልጸዋል። በመሆኑም በማቴሪያሊዝም ንድፈ ሐሳብ የሚያምኑ ሰዎች ብቸኛ አማራጫቸው የሆነውን የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ተቀብለዋል።

ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ ለሳይንስ ያላቸውን አመለካከት የሚያዛባ አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አንዳንዶች አምላክ ዓለምን የፈጠረው ከተወሰኑ ሺህ ዓመታት በፊት ቃል በቃል በስድስት ቀናት ውስጥ ነው የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አላቸው። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያውኑም እንዲህ ያለ አመለካከት ስለያዙ ማስረጃዎቹን አጣምመው መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል በመተርጎም ከደረሱበት መደምደሚያ ጋር ለማስማማት ይሞክራሉ። ( “አንድ ‘ቀን’ ምን ያህል ርዝመት አለው?” የሚለውን በገጽ 9 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ስለ ሳይንስ ይህን የመሰለ ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ለእምነታቸው መሠረት የሚሆን ማስረጃ ሲፈልጉ አጥጋቢ መልስ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።

ከሁሉም እውነታዎች ጋር የሚስማማው የትኛው አመለካከት ነው?

አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አራማጆች ለሕያዋን ነገሮች መሠረት ስለሆኑት ውስብስብ ሞለኪውሎች አመጣጥ የሚከተሉትን ነገሮች ያምናሉ፦

1. ቁልፍ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በሆነ መንገድ ተዋህደው መሠረታዊ የሆኑ ሞለኪውሎችን አስገኙ።

2. ከዚያም እነዚህ ሞለኪውሎች ዲ ኤን ኤ፣ አር ኤን ኤ ወይም ፕሮቲን ለመሥራት በሚያስፈልገው ትክክለኛ ቅደም ተከተል አንድ ላይ ተጣመሩ፤ እነዚህ ሦስት ነገሮች ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ተግባራት ለመፈጸም የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ይዘዋል።

3. ሞለኪውሎቹ ራሳቸውን በራሳቸው ለማባዛት የሚያስፈልጋቸውን ትክክለኛ ቅድም ተከተል በሆነ መንገድ አገኙ። መባዛት ባይችሉ ኖሮ ዝግመተ ለውጥም ሆነ ሕይወት ራሱ ሊኖር አይችልም።

ለሕይወት መሠረት የሆኑት ሞለኪውሎች የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ ሳይኖር አስደናቂ የሆነ ችሎታቸውን ከየት አገኙ? በዝግመተ ለውጥ መስክ የተደረገው ምርምር ስለ ሕይወት አመጣጥ ለሚነሱ ጥያቄዎች አጥጋቢ ማብራሪያም ሆነ መልስ ሊሰጥ አልቻለም። ነገሮችን በዓላማ የሠራ ፈጣሪ መኖሩን የሚክዱ ሰዎች፣ የአምላክን ችሎታ ማሰብ ለማይችሉ ሞለኪውሎችና የተፈጥሮ ኃይሎች እየሰጡ ነው።

ይሁን እንጂ ሐቁ ምን ያሳያል? አሁን ያለን መረጃ እንደሚያሳየው ሞለኪውሎች ውስብስብ የሆነ ሕይወትን ማስገኘት አይችሉም፤ እንዲያውም የፊዚክስ ሕግጋት እንደሚጠቁሙት ውስብስብ ነገሮች ለምሳሌ ማሽን፣ ቤትና ሌላው ቀርቶ ሕያው ሴል እንኳ በጊዜ ሂደት ይፈራርሳሉ እንጂ እየተሻሻሉ አይሄዱም። * የዝግመተ ለውጥ አራማጆች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ሊፈጸም እንደሚችል ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢቮሉሽን ፎር ዳሚስ የተባለው መጽሐፍ ዝግመተ ለውጥ ሊኖር የቻለው ምድር “ከፀሐይ ከፍተኛ ኃይል [ስለምታገኝና] ይህ ኃይል ነገሮች ይበልጥ ውስብስብ እንዲሆኑ” ስለሚያደርግ እንደሆነ ይገልጻል።

ያልተደራጁ ነገሮችን በሥርዓት ለማስቀመጥ ለምሳሌ ጡብ፣ እንጨትና ምስማርን ተጠቅሞ ቤት ለመሥራት ኃይል እንደሚያስፈልግ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ኃይል በጥንቃቄ መቆጣጠርና በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ማንኛውም ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ኃይል ነገሮች ቶሎ እንዲበላሹ ያደርጋል። ለምሳሌ የፀሐይ ኃይልና የአየር ሁኔታ አንድን ሕንፃ ቶሎ እንዲያረጅ ያደርጉታል። * የዝግመተ ለውጥ አማኞች፣ ኃይልን ተቆጣጥሮ ነገሮችን ለመፍጠር ማዋል የተቻለው እንዴት እንደሆነ አጥጋቢ ማብራሪያ ሊሰጡ አይችሉም።

በሌላ በኩል ግን ሕይወትም ሆነ መላው ጽንፈ ዓለም ‘ታላቅ ኃይል’ ያለው ጥበበኛ ፈጣሪ ሥራዎች መሆናቸውን ስናምን ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ያለው የመረጃ ሥርዓት በጣም ውስብስብ የሆነበትን ምክንያት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ከሆኑት ጋላክሲዎች አንስቶ እስከ ጥቃቅን አተሞች ያሉትን ቁስ አካላት የሚቆጣጠሩት የረቀቁ የተፈጥሮ ኃይሎች እንዴት ሊኖሩ እንደቻሉ ጭምር ማብራራት እንችላለን። *​—ኢሳይያስ 40:26

በፈጣሪ ማመን በአሁኑ ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት ካገኘው ግዑዙ ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው ከሚገልጸው አመለካከትም ጋር ይስማማል። ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል።

አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶች የማቴሪያሊዝምን ፍልስፍና የሚደግፍ ሐሳብ ማቅረብ አስቸጋሪ እንዲሆን እንዳደረጉ አይካድም፤ ይህም አንዳንድ አምላክ የለም ባዮች አቋማቸውን እንዲመረምሩ አነሳስቷቸዋል። * አዎ፣ አምላክ የለሽ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች አስደናቂ የሆነው ጽንፈ ዓለም፣ የፈጣሪያችንን የይሖዋ አምላክን ‘የማይታይ ባሕርይ’ እና ‘ዘላለማዊ ኃይል’ የሚያንጸባርቅ የሚታይ ማስረጃ እንደሆነ ተቀብለዋል። (ሮም 1:20) ይህን ጉዳይ ይበልጥ መመርመር ትፈልጋለህ? ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠውና በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ጉዳይ የለም። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ኧርነስት ማየር በዝግመተ ለውጥ አጥብቀው የሚያምኑ ቢሆንም “በቅሪተ አካላት ስብስብ ላይ ክፍተት” እንደሚታይ በሌላ አባባል አዳዲስ ዓይነት ዝርያዎች በድንገት ብቅ እንደሚሉ ገልጸዋል።

^ አን.11 እንዲህ ያለው መፈራረስ የሚኖረው የሳይንስ ሊቃውንት የቴርሞዳይናሚክስ ሁለተኛ ሕግ ብለው በሚጠሩት ሕግ ምክንያት ነው። በቀላል አነጋገር ይህ ሕግ፣ በሥርዓት የተደራጁ ነገሮች እየተበላሹ እንደሚሄዱ ይገልጻል።

^ አን.12 ዲ ኤን ኤ በሚውቴሽን (በጂን ላይ በአጋጣሚ የሚከሰት ለውጥ) ሊቀየር ይችላል፤ ለዚህም እንደ ጨረርና ኬሚካል ያሉ ነገሮች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ለውጦች አዳዲስ ዝርያዎችን አያስገኙም።​—“የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?” የሚለውን በመስከረም 2006 ንቁ! ላይ የወጣ ርዕስ ተመልከት።

^ አን.13 ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ተመልከት።

^ አን.15 “ያደግሁት አምላክ የለሽ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው” የሚለውን በኅዳር 2010 ንቁ! ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.15 ከፍጥረትና ከዝግመተ ለውጥ ጋር በተያያዘ ስለሚነሱት ጥያቄዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ​መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባሉትን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ብሮሹሮች ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሰው ልጆች ጂኖም እየተሻሻለ ነው?

አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት የሰዎች ዲ ኤን ኤ በተደጋጋሚ ጊዜያት በተከሰተ ሚውቴሽን የተነሳ እክል እየታየበት መምጣቱ በጣም እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ነው። ይህ ሐሳብ እውነት ከሆነ የሰው ልጆች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እየተሻሻሉ እንደሆኑ የሚናገረውን ንድፈ ሐሳብ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። ይሁን እንጂ የሰው ልጆችን ጂኖም የፈጠረው አምላክ ከሆነ ጉድለቶች ሊኖሩት የቻለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንስ ሊነግረን የማይችለውን ሐቅ ይኸውም የሰው ልጆች ፍጽምና የጎደላቸው የሆኑት በኃጢአት ወይም አምላክን ባለመታዘዝ ምክንያት እንደሆነ ይነግረናል። ሮም 5:12 “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ” ይላል። እንግዲያው በሰው ልጆች ጂኖም ላይ እክል እየታየ መሆኑ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ የሚያፈርስ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል። ታዲያ እንዲህ ሲባል በሰው ልጆች ጂኖም ላይ የሚታየው ጉድለት ሁልጊዜ እየተባባሰ ይቀጥላል ማለት ነው? አይደለም። አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ እርምጃ እንደሚወስድና በመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምክንያት የደረሱብንን ጉዳቶች በሙሉ እንደሚያስተካክል ቃል ገብቷል። አዎን፣ በሰው ልጆች ጂኖም ላይ የሚታየውን እክል ሊያስተካክለው የሚችለው ፈጣሪያችን እንጂ የማሰብ ችሎታ የሌለው ዝግመተ ለውጥ አይደለም።​—ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 አንድ “ቀን” ምን ያህል ርዝመት አለው?

“ቀን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያየ ርዝመት ያለውን ጊዜ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ስድስቱም የፍጥረት “ቀናት” በ⁠ዘፍጥረት 2:4 (የ1954 ትርጉም) ላይ “አምላክ ሰማይንና ምድርን [ያደረገበት]ቀን” ተብለው ጠቅለል ተደርገው ተገልጸዋል። እያንዳንዱ ቀን ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚሸፍን ግልጽ ነው። የሚገርመው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ ስድስት “ቀናት” እንዳበቁ ቢጠቅስም ሰባተኛው ቀን ግን ማብቃቱን አይናገርም። ለምን? ይህ ቀን ዛሬም ስላልተጠናቀቀ ነው።​—ዘፍጥረት 2:3፤ ዕብራውያን 4:4-6, 11

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ነገሮች እንክብካቤ ካልተደረገላቸው ይፈራርሳሉ

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ኃይልና ሌሎች ባሕርያቱ በጽንፈ ዓለም ላይ ተንጸባርቀዋል