ዴንጊ አስጊነቱ ጨምሯል
ዴንጊ አስጊነቱ ጨምሯል
“የሞሬሎስ ጤና አገልግሎት . . . ከኤሚልያኖ ሳፓታ ከተማ ምክር ቤት የጤና ቦርድ ጋር በመተባበር . . . የይሖዋ ምሥክሮች አካባቢያቸው የዴንጊ አስተላላፊ ትንኞች መራቢያ እንዳይሆን ላከናወኑት የቡድን ሥራ ይህን ጊዜያዊ የምሥክር ወረቀት . . . ለመንግሥት አዳራሻቸው ሰጥቷል።”
የሜክሲኮ ባለሥልጣናት በሽታ አስተላላፊ የሆኑት ትንኞች ስጋት የፈጠሩባቸው መሆኑ ተገቢ ነው። እንቅልፍ የሚነሱት እነዚህ አነስተኛ ትንኞች ለዴንጊ በሽታ ምክንያት የሆነውን አደገኛ ቫይረስ ያስተላልፋሉ። በ2010 በሜክሲኮ ውስጥ ብቻ 57,000 የሚያክሉ ሰዎች ለሕይወት አስጊ በሆነው በዚህ በሽታ ተይዘዋል። የዴንጊ በሽታ ከሜክሲኮ ሌላ በአሁኑ ጊዜ ከ100 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ይገኛል። እንዲያውም የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ግምታዊ አኃዝ መሠረት በመላው ዓለም በየዓመቱ 50 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በዴንጊ በሽታ ይያዛሉ፤ እንዲሁም ከዓለም ሕዝብ መካከል ሁለት አምስተኛ የሚሆነው በበሽታው የመያዝ አደጋ ተጋርጦበታል። በዚህ ምክንያት የጤና ባለሥልጣናት ዴንጊ ቫይረስን ከሚያስተላልፉ ትንኞች አንዷ የሆነችውን ኤዪዲስ ኢጂፕቲ የተባለች ባለ ነጭ ነጠብጣብ ትንኝ ጨርሶ ለማጥፋት ፕሮግራሞችን ቀርጸዋል። *
ዴንጊ ይበልጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው ሞቃታማና ከፊል ሞቃታማ በሆኑ አካባቢዎች ሲሆን በተለይ ደግሞ በዝናባማ ወራት ብሎም እንደ ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ከደረሱ በኋላ ባሉት ወቅቶች ስርጭቱ ይጨምራል። ይህ የሆነው እንስቷ ትንኝ እንቁላሎቿን የምትጥለው ውኃ ባቆሩ ቦታዎች ስለሆነ ነው። * በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች ለቤት አገልግሎት የሚያውሉትን ውኃ የሚያጠራቅሙት በገንዳዎች ውስጥ ስለሆነ የጤና ባለሙያዎች ገንዳዎቹን እንዲከድኑ ለሕዝቡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ይሰጣሉ። እንዲህ ማድረግ ገንዳዎቹ የትንኝ መራቢያ እንዳይሆኑ ይከላከላል። በተጨማሪም ሰዎች ከግቢያቸው አሮጌ ጎማዎችን፣ ጣሳዎችን፣ የአትክልት መትከያዎችንና የፕላስቲክ ዕቃዎችን ጨምሮ ውኃ ሊያቁሩ የሚችሉ ማናቸውንም ነገሮች ካስወገዱ እነዚህ ትንኞች እንዳይራቡ መከላከል ይችላሉ።
የዴንጊን ምልክቶች ለይቶ ማወቅና በሽታውን መቋቋም
ዴንጊ የሚያሳያቸው የሕመም ምልክቶች ከኢንፍሉዌንዛ ጋር በጣም ስለሚመሳሰሉ ብዙ ጊዜ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ላይረዱ ይችላሉ። ይሁንና የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ አንድ ሰው ከትኩሳት ጋር ተያይዞ ቆዳው ላይ ሽፍታ ከወጣበት፣ በውስጠኛው የዓይኑ ክፍል ሕመም የሚሰማው ከሆነ እንዲሁም የጡንቻ ሕመም ካለውና መገጣጠሚያውን በኃይል የሚቆረጣጥመው ከሆነ (አጥንት ሰባሪ ትኩሳት ተብሎም የሚጠራው ለዚህ ነው) በዴንጊ በሽታ ተይዞ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይኖርበታል። ትኩሳቱ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ሊቆይ ይችላል።
ዶክተሮች እስከ ዛሬ ለዴንጊ በሽታ መድኃኒት ባያገኙም አብዛኛውን ጊዜ እረፍት በማድረግና ብዙ ፈሳሽ በመጠጣት ራስን በራስ ማከም ይቻላል። ይሁን እንጂ በሽታው ዴንጊ ሾክ ሲንድሮም ወደሚባል ደረጃ ወይም ሄመሬጂክ ፊቨር ወደተባለ ደም መፍሰስ የሚያስከትል ኃይለኛ ትኩሳት ሊያድግ ስለሚችል ሕመምተኛው በቂ ክትትል ሊደረግለት ይገባል። ለሞት ሊያደርሱ የሚችሉት እነዚህ የሕመም ደረጃዎች ግለሰቡ የመጀመሪያው ትኩሳት ጋብ ካለለት በኋላም ወይም እየተሻለው እንደሆነ በሚሰማው ጊዜም ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው እዚህ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው? በሽተኛው ኃይለኛ የሆድ ሕመም ሊሰማው፣ ለረጅም ጊዜ ሊያስመልሰው፣
ነስር እና የድድ መድማት ሊያጋጥመው፣ ዓይነ ምድሩ ሊጠቁርና ቆዳው ላይ የበለዘ መልክ ያለው እባጭ ሊወጣበት ይችላል። በተጨማሪም መቅበጥበጥ፣ ከመጠን ያለፈ የውኃ ጥም፣ የቆዳ መገርጣትና የሰውነት መቀዝቀዝ እንዲሁም በጣም ዝቅተኛ የሆነ የደም ግፊት የዴንጊ ሾክ ሲንድሮም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።ዴንጊ በባክቴሪያ ሳይሆን በቫይረስ የሚመጣ በሽታ በመሆኑ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን መውሰድ ምንም ጥቅም የለውም። በተጨማሪም እንደ አስፕሪንና አይቢዩፕሮፌን ያሉ የሕመም ማስታገሻዎች ይበልጥ ለደም መፍሰስ አደጋ ስለሚያጋልጡ ሕመምተኛው እነዚህን መድኃኒቶች ባይወስድ የተሻለ ነው። አራት ዓይነት የዴንጊ ቫይረሶች በመኖራቸው አንድ ሰው ከአንድ ጊዜ በላይ የዴንጊ በሽታ ሊይዘው ይችላል።
በዴንጊ ከተያዝክ በደንብ እረፍት አድርግ፤ እንዲሁም ብዙ ፈሳሽ ውሰድ። በተጨማሪም ትንኞቹ እንዳይነክሱህና በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያዛምቱ በተቻለ መጠን ስትተኛ አጎበር ተጠቀም።
ይሁንና መጀመሪያውንም በሽታው እንዳይዝህ፣ በትንኞቹ የመነደፍ አጋጣሚህን መቀነስ የምትችለው እንዴት ነው? ረጅም እጅጌ ያለው ልብስ፣ ረጅም ሱሪ ወይም ረጅም ቀሚስ መልበስ እንዲሁም ትንኞቹን የሚያባርሩ ነገሮችን መጠቀም ሊረዳ ይችላል። ትንኞቹ በማንኛውም ሰዓት ሊነድፉ ቢችሉም ይበልጥ ንቁ የሚሆኑት ግን ፀሐይ ከወጣች በኋላ ባሉት ሁለት ሰዓታት እና ፀሐይ ከመግባቷ በፊት ባሉት ሁለት ሰዓታት ውስጥ ነው። በተጨማሪም በምትተኛበት ጊዜ የትንኝ ማባረሪያ መድኃኒት የተረጨ አጎበር ተጠቀም።
ለዴንጊ በሽታ መከላከያ ክትባት ለመሥራት የሚደረገው ጥረት ይሳካ እንደሆነና እንዳልሆነ ጊዜ የሚያሳየን ነገር ነው። ያም ሆነ ይህ የአምላክ መንግሥት ይህን በሽታ ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ሕመም ማስወገዱ አይቀርም። በእርግጥም፣ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል” የሚለው ተስፋ የሚፈጸምበት ጊዜ ይመጣል።—ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በአንዳንድ አገሮች ኤዪዲስ አልቦፒክተስ እንደተባሉ ያሉ ሌሎች የትንኝ ዝርያዎችም የዴንጊን ቫይረስ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
^ አን.4 አብዛኛውን ጊዜ፣ ኤዪዲስ የሚባሉት ትንኞች ከተፈለፈሉባቸው ቦታዎች ርቀው የሚሄዱት ግፋ ቢል ጥቂት መቶ ሜትሮች ብቻ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የመራቢያ ቦታዎችን በመለየት እርምጃ ውሰድ
1. የተጣሉ ጎማዎች
2. የዝናብ መውረጃ አሸንዳዎች
3. አበባ የተተከለባቸው ዕቃዎች
4. የፕላስቲክ ዕቃዎች
5. የተጣሉ ጣሳዎችና በርሜሎች
በትንኝ የመነከስ አጋጣሚን ለመቀነስ
ሀ. ረጅም እጅጌ ያለው ልብስ፣ ረጅም ሱሪ ወይም ረጅም ቀሚስ መልበስ። ትንኞችን የሚያባርር ነገር መጠቀም
ለ. ሲተኙ አጎበር መጠቀም
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Source: Courtesy Marcos Teixeira de Freitas