በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ለእንስሳት ያስባል?

አምላክ ለእንስሳት ያስባል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ለእንስሳት ያስባል?

በርካታ እንስሳት ዝርያቸው ሊጠፋ ተቃርቧል። ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ይህ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተፋጠነ እንደሆነ ያምናሉ። የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ እንዲሁም ሰዎች ቀደም ሲል የእንስሳት መኖሪያ የነበረውን አካባቢ አላግባብ በመጠቀማቸው ሳቢያ እንስሳት ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚዘጋጁ ምግቦች፣ እንስሳት እርስ በርስ እንዲጣሉ የሚደረግባቸው ጭካኔ የተሞላባቸው ስፖርቶች እንዲሁም ሰዎች የቤት እንስሳትን የሚጥሉ መሆናቸው ሁኔታውን ይበልጥ አባብሰውታል።

ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንዲህ ያለው ሁኔታ የሕዝብ ብዛት መጨመር የሚያስከትለው የማይቀር ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም የአምላክ ዓላማ ይህ ነበር? እንስሳትን ሰዎች እንዲያሠቃዩአቸው ትቷቸዋል? አምላክ ለእንስሳት እንደሚያስብላቸው እንዴት እናውቃለን?

ገና ከጅምሩ በግልጽ የታየ አሳቢነት

አምላክ ዓሦችን፣ ወፎችንና የየብስ እንስሳትን ከፈጠረ በኋላ በሥራው ተደስቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:21, 25) ፈጣሪ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሁሉንም ፍጥረታት ይወዳቸዋል እንዲሁም ያስብላቸዋል። አምላክ እንስሳትን በደመ ነፍስ “እጅግ ጠቢባን” እንዲሆኑ አድርጎ ከመፍጠር በተጨማሪ ባዘጋጀላቸው የመኖሪያ አካባቢ ተመችቷቸው እንዲኖሩ የሚያስፈልጋቸውን ምግብም ሰጥቷቸዋል። በእርግጥም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንደሚከተለው ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው፦ “ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በሰጠሃቸውም ጊዜ፣ አንድ ላይ ያከማቻሉ፤ እጅህንም ስትዘረጋ፣ በመልካም ነገር ይጠግባሉ።”​—ምሳሌ 30:24፤ መዝሙር 104:24, 25, 27, 28

እውነት ነው፣ አምላክ እንስሳትን ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም ተገዢ አድርጓቸዋል። እንስሳት የማመዛዘን ችሎታም ሆነ ከፈጣሪያቸው ጋር ዝምድና የመመሥረት ፍላጎት እንዲኖራቸው ተደርገው አልተፈጠሩም። (2 ጴጥሮስ 2:12፤ ይሁዳ 19) ከዚህ በተቃራኒ አዳም “በእግዚአብሔር መልክ” የተፈጠረ በመሆኑ ከእንስሳት የላቀ ፍጡር ነበር። አዳም የፈጣሪውን የይሖዋን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ነበረው። (ዘፍጥረት 1:27፤ ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) ይህ መሆኑ ግን ሰዎች ከፈጣሪያቸው ዓላማ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በእንስሳት ላይ ሥልጣናቸውን እንዲጠቀሙ መብት አይሰጣቸውም።

ለምሳሌ ያህል፣ አዳም ለእንስሳት ስም ማውጣት የጀመረው ይሖዋ ይህን የማድረግ መብት ስለሰጠው ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ አዳም ለእያንዳንዳቸው “ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት” ሲል እንስሳቱን ወደ እሱ ‘በማምጣት’ አግዞታል። (ዘፍጥረት 2:19) ሰው እንስሳትን በመንከባከብ ረገድ የሚያደርገው ጥረት ሊሳካለት የሚችለው የፈጣሪውን አመራር ከተከተለ ብቻ ነው።

አምላክ ከልቡ ያስብላቸዋል!

የሚያሳዝነው ነገር፣ አዳም በፈጣሪው ላይ ዓመፀ። የእሱ ማመፅ በመላው የሰው ዘርና በምድር ላይ ባለው ሕያው ፍጡር ሁሉ ላይ አስከፊ መዘዝ አስከተለ። ይሁን እንጂ ፈጣሪ፣ እንስሳት እንዴት ሊያዙ እንደሚገባ በግልጽ ተናግሯል። ምንም እንኳን የሰው ልጅ እንስሳትን ለምግብነትና ለሌሎችም ጠቃሚ አገልግሎቶች እንዲያውላቸው ከጊዜ በኋላ ቢፈቀድለትም አምላክ እንስሳት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲያዙ ፈጽሞ አልፈቀደም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤ ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው” በማለት ይናገራል።​—ምሳሌ 12:10

የሚገርመው፣ አምላክ ለጥንቷ የእስራኤል ብሔር ከሰጣቸው ሕግጋት መካከል ከእንስሳት ደህንነት ጋር የተያያዙ ሕግጋት ይገኙበታል። እስራኤላውያን በየሳምንቱ አንድ ቀን ምንም ሳይሠሩ እንዲያርፉ የተሰጣቸው የሰንበት ሕግ እንስሶቻቸውም ጭምር ማረፍ እንዲችሉ አጋጣሚ ይፈጥር ነበር። (ዘፀአት 23:12) በዚህ ቅዱስ ቀን ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት ባይፈቀድም ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸውን እንስሶቻቸውን እንዲረዱ ይጠበቅባቸው የነበረ መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። (ሉቃስ 14:5) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ፣ ከብቶች ሥራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ መብላት እንዳይከለከሉና እንስሳት ከልክ ያለፈ ጭነት እንዳይጫኑ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። (ዘፀአት 23:5፤ ዘዳግም 25:4) በሬና አህያን አንድ ላይ ጠምዶ ማረስ ተከልክሎ ነበር፤ ይህም ሁለቱም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ያደርጋል። (ዘዳግም 22:10) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እንስሳት በአግባቡ፣ በአክብሮትና በርኅራኄ ሊያዙ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል!

ብዙ ሰዎች የሚያተኩሩት በራሳቸው ጥቅም ላይ በመሆኑ በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ችግር ችላ ቢሉትም አምላክ ግን ለእንስሳት ይራራል። የነነዌ ሕዝብ ንስሐ በመግባታቸውና አምላክ ሊያመጣባቸው ከነበረው ፍርድ በማምለጣቸው ምክንያት ነቢዩ ዮናስ ምሕረት የጎደለው አመለካከት ባንጸባረቀ ጊዜ ይሖዋ “ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሶች ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?” በማለት ተናግሯል። (ዮናስ 4:11) አዎን፣ ፈጣሪ ለእንስሳቱም ጭምር አዝኗል!

ወደፊትም እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ማረጋገጫ ተሰጥቷል

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ እንስሳት የሚደርስባቸው ነገር ያሳስበዋል። የሚወደው ልጁ ኢየሱስ፣ አንዲት ድንቢጥ እንኳ አባቱ ሳያውቅ መሬት ላይ እንደማትወድቅ ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:29) ከዚህ በተቃራኒ የሰው ልጅ አካባቢውን ለመንከባከብ ጥረት ቢያደርግም እንኳ የሚያደርገው ነገር በአካባቢው ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሙሉ በሙሉ መገንዘብ አይችልም። የሰው ልጆች ለእንስሳት አሳቢ እንዲሆኑ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለባቸው።

ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ [የምትሞላበት]” ጊዜ እንደሚመጣ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 11:9) እንዲህ ባለው እውቀት አማካኝነት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ምድርን በአግባቡ ለመያዝ የሚያስፈልጋቸውን ትምህርትና ሥልጠና ያገኛሉ። በዚያን ጊዜ ፈጣሪ በሰውና በእንስሳት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ስለሚያደርግ አምላክ በመጀመሪያ አስቦት የነበረው ዓይነት ሁኔታ በምድር ላይ ይሰፍናል።

መጽሐፍ ቅዱስ በዚያን ጊዜ የሚመጣውን ከፍተኛ ለውጥ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፣ የአንበሳ ደቦልና የሰባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። ላምና ድብ በአንድነት ይሰማራሉ፤ ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፤ ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጕድጓድ ይከትታል።” ይህ ምንኛ የሚያስደስት ተስፋ ነው!​—ኢሳይያስ 11:6-8

ይህን አስተውለኸዋል?

● አምላክ፣ የሰው ልጆች እንስሳትን የሚይዙበት መንገድ ያሳስበዋል?​—ምሳሌ 12:10፤ ማቴዎስ 10:29

● በሰዎችና በእንስሳት መካከል ፍጹም ስምምነት ሊኖር ይችላል?​—ኢሳይያስ 11:6-9

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ለእንስሳት አሳቢነት ማሳየት የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ይጠይቃል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

La Voz de Galicia/Fotógrafo: Víctor Mejuto