ከመጥፋት የተረፈ ድንቅ መጽሐፍ
ከመጥፋት የተረፈ ድንቅ መጽሐፍ
“የዚህን ያህል ከባድ ተቃውሞ ያጋጠመው ሌላ መጽሐፍ የለም፤ ሆኖም ሥልጣንና ችሎታ ያላቸው እንዲሁም አንደበተ ርቱዕ የሆኑ ሰዎች የሰነዘሩበትን ማንኛውንም ጥቃት ተቋቁሟል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባ መጽሐፍ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ ይህ መጽሐፍ አምላክ ለሰው ልጆች የላከውን መልእክት እንደያዘ ስለሚናገር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ ይህን መጽሐፍ ባለማንበብህ የሚቀርብህ ጠቃሚ ነገር ይኖራል ማለት ነው።
ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት እንድትሰጥ የሚያነሳሳህ ሌላው ምክንያት ደግሞ አሁን በእጃችን ካሉ እጅግ ጥንታዊ መጻሕፍት አንዱ ስለሆነ እንዲሁም በበርካታ ቋንቋዎች በመተርጎምና በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ ስለሌለው ነው። ባለፉት ዘመናት በሙሉ፣ በብዛት በመሸጥ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ከመሆኑም ሌላ በየዓመቱ በብዛት ከተሸጡ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛል።
በታሪክ ዘመናት ሁሉ መጽሐፉን አፍኖ ለማስቀረት የተደረገውን ጥረት ስንመለከት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መልእክት የያዘ እንደሆነ መናገሩ፣ የዕድሜው አንጋፋነትና ስርጭቱ ይበልጥ ያስደምመናል። አልበርት ባርንዝ የተባሉት የ19ኛው መቶ ዘመን የሥነ መለኮት ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “የዚህን ያህል ከባድ ተቃውሞ ያጋጠመው ሌላ መጽሐፍ የለም፤ ሆኖም ሥልጣንና ችሎታ ያላቸው እንዲሁም አንደበተ ርቱዕ የሆኑ ሰዎች የሰነዘሩበትን ማንኛውንም ጥቃት ተቋቁሟል።”
እኚሁ ጸሐፊ፣ ሰዎች በተፈጥሮአቸው ተደጋጋሚ ጥቃት ለተሰነዘረበት ለማንኛውም ነገር ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል። “ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ብዙ ጦርነቶችን ተቋቁሞ ያለፈ የጦር ሠራዊት የለም” ብለዋል፤ አክለውም እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “የዚህን መጽሐፍ ያህል በርካታ ከበባዎችን የመከተ ብሎም ኃይለኛ ጦርነቶችን የተቋቋመና ዘመናት ቢፈራረቁበትም ጸንቶ የቆመ ጥንታዊ ቅጥር የለም፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በተደጋጋሚ ጊዜ በከባድ ማዕበል ቢንገላታም ከቦታው ንቅንቅ ሳይል የቆየ ዐለት የለም።”
በርካታ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በዛሬው ጊዜ ሊገኙ አልቻሉም ወይም ከጥቅም ውጭ ሆነዋል አሊያም ተረስተው ቀርተዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከባድ ጥቃት ቢሰነዘርበትም አልጠፋም። አንዳንዶች ብዙኃኑ ይህን መጽሐፍ እንዲያገኘው ለማድረግ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስን በታላቅ ጉጉት ከሚያነቡት ሰዎች በመንጠቅ መጽሐፉንም ሆነ አንባቢዎቹን በሕዝብ ፊት በእሳት አጋይተዋቸዋል።
ይህን መጽሐፍ አንዳንዶች በጣም ሲወድዱት ሌሎች ግን አምርረው የጠሉት ለምንድን ነው? መጽሐፉ ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ አልፏል? ሊያጠፉት የሞከሩትስ እነማን ነበሩ? ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ መጽሐፉ ከመጥፋት ሊተርፍ የቻለው ለምንድን ነው? የያዘው መልእክት ለአንተ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
[በገጽ 2, 3 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በመጽሐፍ ቅዱስ ዝግጅት ረገድ ጉልህ የሆኑ ዓመታት
ከ1513 ዓ.ዓ.–98 ዓ.ም. ገደማ መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ ተጻፈ
100 በመጽሐፍ መልክ ስለተዘጋጀ ይዞ ለመንቀሳቀስ ይበልጥ አመቺ ሆነ
405 ጀሮም ወደ ላቲን ተረጎመው
1380 ዊክሊፍ ከላቲን ወደ እንግሊዝኛ ተረጎመው
1455 ጉተንበርግ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ አተመ
1525 ቲንደል ወደ እንግሊዝኛ ተረጎመው
1938 ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታተመ
2011 ከ2,500 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል