በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በመላው እንግሊዝ በመሃል ከተማ በሚገኙ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች [ኤ ቲ ኤም] ላይ ሰዎች በሚጫኗቸው ቁልፎች ላይ የተደረገው ምርመራ እንዳሳየው እነዚህ ቁልፎች የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች መቀመጫዎችን ያህል በጎጂ ባክቴሪያዎች የተበከሉ ናቸው።​—ዘ ቴሌግራፍ፣ ብሪታንያ

“አንዳንድ ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት ባልጠበቁት ቦታ [ለምሳሌ በዚህ ዓመት በኒው ዚላንድና ባለፈው ዓመት ደግሞ በሄይቲ] የመሬት መናወጦች ይከሰታሉ፤ ለዚህም ምክንያቱ የመሬት መናወጡ በመሬት ገጽ ላይ ባሉ ያልታወቁ ስንጥቆች አካባቢ ስለሚደርስ ነው። . . . ይህ ደግሞ አሳሳቢ የሆነ ጥያቄ ያስነሳል፦ ‘ባልተጠበቁ ወይም መኖራቸው በማይታወቅ ስንጥቆች አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ ስንት ታላላቅ የመሬት መናወጦች ይኖሩ ይሆን?’”​—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“በዓለም ላይ ያሉት አራት የናጠጡ ሀብታሞች . . . ያላቸው ጥሪት በዓለም ላይ እጅግ ድሃ የሆኑት 57 አገሮች ካላቸው ሀብት ይበልጣል።”​—ፎሪን ፖሊሲ፣ ጥር/የካቲት 2011፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በፖላንድ የንግድ ድርጅቶች ካሏቸው ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሠራተኞቻቸው እንደሰረቋቸው ወይም እንዳጭበረበሯቸው ገልጸዋል።​—ጋዜታ ፕራትሳ፣ ፖላንድ

በብራዚል የሚገኝ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሙሽሮች ጋብቻቸውን ለመፈጸም አርፍደው ከደረሱ 300 የአሜሪካ ዶላር መቅጣት ጀምሯል። ተጋቢዎቹ ከሥነ ሥርዓቱ በፊት ገንዘብ እንዲያስይዙ የሚጠየቁ ሲሆን ገንዘባቸው የሚመለስላቸው በሰዓቱ ከደረሱ ብቻ ነው።​—ጂ1፣ ብራዚል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰውነታቸውን ክፍል አይለግሱም

ዮዜፍ ራትሲንገር፣ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካርዲናል በነበሩበት ጊዜ ቢሞቱ የሰውነታቸውን ክፍል ለሌላ ሰው ለመለገስ ፈቃደኛ እንደነበሩ ላ ሪፐብሊካ የተሰኘው የጣሊያን ጋዜጣ ዘግቧል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክት 16ኛ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ግን የሰውነታቸውን ክፍል ለመለገስ ፈቃደኛ አልሆኑም። ለምን? “የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አካል የመላው ቤተ ክርስቲያን ንብረት ነው” በማለት ከቫቲካን ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ዚግሙንት ዢሞፍስኪ ተናግረዋል። “ስለዚህ አንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከሞቱ በኋላ ልዩ ክብር ሊሰጣቸው ስለሚችል አካላቸው ምንም ሳይጎድል እንዳለ ተጠብቆ መቀመጡ ተገቢ እንደሆነ ግልጽ ነው።”

ሕይወትን በገንዘብ መለወጥ?

ሰዎች ከዕድሜያቸው ላይ አንድ ዓመት ቀንሰው በአንድ ሚሊዮን ዩሮ እንዲሸጡ ቢጠየቁ ይህን ለማድረግ ይስማማሉ? በጀርመን ከ4 ወንዶች መካከል ከ1 በላይ የሚሆኑት እና ከ6 ሴቶች መካከል አንዷ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች እንደሚሆኑ ኤምኒድ ተብሎ የሚጠራው የሕዝብ አስተያየት የሚሰበስብ ተቋም ለሪደርስ ዳይጀስት ዶይችላንት ባካሄደው ጥናት ላይ ገልጿል። ጥያቄ የቀረበላቸው ሰዎች ወጣቶች በሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነቱን ስምምነት ለመፈጸም ይበልጥ ፈቃደኛ እንደሚሆኑ ጥናቱ አሳይቷል፤ ከ14 እስከ 29 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት መካከል 29 በመቶ የሚሆኑት እንዲሁም ከ30 እስከ 39 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ካሉት መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ሰዎች ዕድሜያቸው በጨመረ መጠን ሕይወትን ይበልጥ ውድ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ከዕድሜያቸው ላይ አንድ ዓመት ቀንሰው ለመሸጥ ፈቃደኞች እንደሚሆኑ የገለጹት ከ50 እስከ 59 ዓመት ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል 13 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ ከ60 ዓመት በላይ ከሆኑት መካከል ደግሞ 11 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።