የአምላክ ቃል ለብዙኃኑ እንዳይዳረስ የተደረገ ጥረት
የአምላክ ቃል ለብዙኃኑ እንዳይዳረስ የተደረገ ጥረት
ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ መጽሐፍ ቅዱስን ሕዝቡ በሚግባባባቸው ቋንቋዎች ለመተርጎም ጥረት ተደረገ። መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈባቸው የዕብራይስጥ ወይም የግሪክኛ ቋንቋዎች አንብበው ሊረዱ የሚችሉ ሰዎች ብዙ አልነበሩም። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው በእነዚህ የጥንት ቋንቋዎች ብቻ ቢሆን ኖሮ አብዛኞቻችን የአምላክን ቃል መረዳት አስቸጋሪ ይሆንብን ነበር።
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ300 ዓመት ገደማ በፊት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ግሪክኛ መተርጎም ተጀመረ። ይህ ትርጉም የግሪክ ሴፕቱጀንት (የሰባ ሊቃናት ትርጉም) በመባል ይታወቃል። ከ700 ያህል ዓመታት በኋላ ጀሮም ቩልጌት የሚባለውን ዝነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጀ። በዘመኑ በሮም ግዛት ውስጥ የሕዝቡ የመግባቢያ ቋንቋ ላቲን ስለነበር ጀሮም የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደዚህ ቋንቋ ተረጎማቸው።
ውሎ አድሮ ግን ላቲን የሕዝቡ የመግባቢያ ቋንቋ መሆኑ እየቀረ መጣ። ላቲን የሚችሉት ጥሩ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም የሚደረገውን ጥረት ትቃወም ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክኛና ከላቲን ውጪ በሌላ ቋንቋ መገኘት የለበትም ብለው ይከራከሩ ነበር። *
የቤተ ክርስቲያን መከፋፈልና የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጎም
በዘጠነኛው መቶ ዘመን መቶድየስና ሲረል የተባሉ የተሰሎንቄ ሚስዮናውያን፣ በባይዛንቲየም የነበረውን ምሥራቃዊ ቤተ ክርስቲያን ወክለው የስላቭ ቋንቋ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሠራበት ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመሩ። ዓላማቸው
ግሪክኛም ሆነ ላቲን የማይችሉት የምሥራቅ አውሮፓ የስላቭ ሕዝቦች ስለ አምላክ በገዛ ቋንቋቸው እንዲማሩ መርዳት ነበር።ይሁን እንጂ የባይዛንታይንን ክርስትና መስፋፋት ለመግታት ላቲንን እንደ መሣሪያ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ የጀርመን ቀሳውስት እነዚህን ሚስዮናውያን አጥብቀው ተቃወሟቸው። እነዚህ ቀሳውስት፣ ሕዝቡ መንፈሳዊ ትምህርት ከማግኘቱ ይበልጥ የሚያሳስባቸው የፖለቲካው ጉዳይ እንደነበረ ግልጽ ነው። በሕዝበ ክርስትና ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ቅርንጫፎች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል እየተካረረ በመሄዱ በ1054 የሮም ካቶሊክና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ተለያዩ።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይተረጎም የተደረገ ትግል
ውሎ አድሮ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላቲንን እንደ ቅዱስ ቋንቋ አድርጋ መመልከት ጀመረች። በመሆኑም የቦሂምያ መስፍን የሆኑት ቭራቲስላውስ በ1079 የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችን በስላቭ ቋንቋ ለማከናወን እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሪጎሪ ሰባተኛ “እንዲህ ያለውን ነገር ፈጽሞ ልንፈቅድ አንችልም” ሲሉ ጽፈዋል። ይህን ያሉት ለምን ነበር?
ግሪጎሪ እንዲህ ብለዋል፦ “ጉዳዩን በጥንቃቄ የሚመረምሩ ሁሉ አምላክ ቅዱስ ጽሑፉ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግልጽ እንዳይሆን እንደፈለገ ማስተዋል ይችላሉ። ይህን ያደረገበት ምክንያት ቅዱስ ጽሑፉ ለሁሉ ሰው ግልጽ ቢሆን እንደ ተራ ነገር ሊታይና ተገቢውን አክብሮት ሊያጣ አሊያም ውስን እውቀት ያላቸው ሰዎች በተሳሳተ ሁኔታ ሊረዱትና ስህተት ላይ ሊወድቁ ስለሚችሉ ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ እጅ የመግባቱ አጋጣሚ በጣም ውስን ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ ሁኔታው በዚሁ እንዲቀጥል ትፈልግ ነበር። ይህ ዓይነቱ አቋም ቀሳውስቱ በብዙኃኑ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው አስችሏል። ለቀሳውስቱ ብቻ እንደተመደቡ የሚታሰቡ ነገሮችን ተራው ሕዝብ እንዲያውቅ አልፈለጉም።
በ1199 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት ሳልሳዊ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይኛ ለመተርጎምና በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ለመወያየት ስለደፈሩ “መናፍቃን” ጽፈው ነበር። ኢየሱስ የተናገረው “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ እንዲሁም ዕንቁዎቻችሁን በአሳማ ፊት አትጣሉ” የሚለው ሐሳብ በእነዚህ ሰዎች ላይ እንደሚሠራ ኢኖሰንት ገልጸዋል። (ማቴዎስ 7:6) እንዲህ ያሉበት ምክንያት ምን ነበር? “ቅዱሳን መጻሕፍት ላቅ ያሉ በመሆናቸው የትኛውም ተራና ያልተማረ ሰው እነዚህን መጻሕፍት ለማጥናትም ሆነ ለሌሎች ለመስበክ መድፈር የለበትም” ብለዋል። ብዙውን ጊዜ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ትእዛዝ የተቃወመ ሁሉ ኢንክዊዚሽን ለሚባለው የሮም ካቶሊክ ችሎት መርማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን እነሱም ቁም ስቅሉን በማሳየት ወንጀል እንደፈጸመ እንዲናዘዝ ያደርጉት ነበር። አቋማቸውን ለመቀየር እምቢተኛ የሆኑ ደግሞ በቁማቸው ይቃጠሉ ነበር።
ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይኖራቸውና እንዳያነቡት ለማድረግ በተካሄደው ረጅም ዘመናት የፈጀ ትግል ወቅት፣ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ እንዳይውልና በሌሎች ቋንቋዎች እንዳይተረጎም ለመከልከል ሲሉ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንትን ደብዳቤ ይጠቀሱ ነበር። ኢኖሰንት ይህን አዋጅ ካወጡ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ በሚግባባባቸው ቋንቋዎች የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችንና አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍ ቅዱሶቹን ይዘው የተገኙ ሰዎችን ማቃጠል ተጀመረ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት የካቶሊክ ሃይማኖት በተስፋፋባቸው የአውሮፓ ክፍሎች ያሉ ጳጳሳትና መሪዎች፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት ሳልሳዊ የጣሉት እገዳ እንዲከበር ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት አብዛኞቹ ትምህርቶቻቸው በቤተ ክርስቲያን ወግ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ
የተመሠረቱ እንዳልሆኑ ያውቁ ነበር። ምዕመኖቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያገኙ ከፈለጉባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ካነበቡ በቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶችና በቅዱሳን መጻሕፍት መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል ይችላሉ።ተሐድሶው ያስከተላቸው ውጤቶች
የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ መጀመር የአውሮፓን ሃይማኖታዊ ገጽታ ለውጦታል። ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተሐድሶ ለማካሄድ የተነሳውና ውሎ አድሮም በ1521 ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋረጠው ከቅዱሳን መጻሕፍት ባገኘው ግንዛቤ ምክንያት ነው። በመሆኑም ጥሩ ተርጓሚ የነበረው ሉተር ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጨርሶ ከተለየ በኋላ ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያገኝ ጥረት ማድረግ ጀመረ።
ሉተር መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ መተርጎሙና ይህ ትርጉም በስፋት መሰራጨቱ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ትኩረት ሳበ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሉተርን መጽሐፍ ቅዱስ የሚተካና በካቶሊክ ሃይማኖት ዘንድ እውቅና ያገኘ ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ተሰማት። ብዙም ሳይቆይ እንዲህ ያሉ ሁለት የጀርመንኛ ትርጉሞች ብቅ አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ከሆነ 25 ዓመት እንኳ ሳይሞላ ይኸውም በ1546 የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የትሬንት ጉባኤ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምን ጨምሮ የማንኛውም ሃይማኖታዊ ጽሑፍ ኅትመት በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ደነገገ።
የትሬንት ጉባኤ የሚከተለውን ድንጋጌ አስተላለፈ፦ “ከአሁን በኋላ ቅዱሳን መጻሕፍት . . . በተቻለ መጠን ትክክል በሆነው መንገድ ሊታተሙ ይገባል፤ በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ጉዳይ የሚመለከቱ መጻሕፍትን የደራሲው ስም ሳይጻፍበት ማተምም ሆነ ማሳተም አሊያም [የሰበካው] ጳጳስ መርምሮ ሳይፈቅድ እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን መሸጥ ሌላው ቀርቶ መያዝ እንኳ ሕገ ወጥ ተግባር ነው።”
በ1559 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖል አራተኛ በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተከለከሉ መጻሕፍትን ዝርዝር የያዘውን የመጀመሪያ ጽሑፍ አሳተሙ። ይህ ጽሑፍ በስፓንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በደች፣ በጀርመንኛ፣ በጣሊያንኛና በፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስን መያዝ የተከለከለ እንደሆነ ይገልጻል፤ አንዳንድ የላቲን ትርጉሞችም ታግደው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የፈለገ ማንኛውም ሰው ከጳጳሳት ወይም ኢንክዊዚሽን ከሚባለው ችሎት መርማሪዎች የጽሑፍ ፈቃድ ማግኘት እንደሚኖርበት ይነገረው ነበር፤ ይህን ማድረግ ደግሞ በመናፍቅነት ሊያስጠረጥር ስለሚችል የማይሞከር ነገር ነበር።
በአካባቢያቸው በሚነገረው ቋንቋ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን ለመያዝ ወይም ለማሰራጨት የደፈሩ ሁሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቁጣ ገፈት ቀማሽ ይሆኑ ነበር። ብዙዎች በቁጥጥር ሥር ይውሉ፣ ግንድ ላይ ታስረው በሚዘገንን ሁኔታ ይቃጠሉ፣ የዕድሜ ይፍታህ እስራት ይበየንባቸው ወይም የመርከብ ቀዛፊ ሆነው ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ይፈረድባቸው ነበር። ከየቦታው የተሰበሰቡ መጽሐፍ ቅዱሶች ይቃጠሉ ነበር። እንዲያውም የካቶሊክ ቀሳውስት እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ መጽሐፍ ቅዱሶችን እየሰበሰቡ ማቃጠላቸውን ቀጥለው ነበር።
እንዲህ ሲባል ግን የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጅና ጠበቃ ነበር ማለት አይደለም። በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን አንዳንድ የፕሮቴስታንት
የሥነ መለኮት ምሁራን፣ ሃየር ክሪቲሲዝም የሚባል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሂስ በመሰንዘር ላይ ያተኮረ የአጠናን ዘዴ ማራመድ ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ብዙ ሰዎች በዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ላይ የተመሠረተውን ሕይወት በፍጥረት ሳይሆን እንዲሁ በአጋጣሚና ያለ ፈጣሪ ጣልቃ ገብነት በዝግመተ ለውጥ የመጣ እንደሆነ የሚገልጸውን ትምህርት ተቀበሉ።የሥነ መለኮት ምሁራን ሌላው ቀርቶ በርካታ ቀሳውስት እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛው በአፈ ታሪክና በተረት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። በዚህም ምክንያት በዛሬው ጊዜ የፕሮቴስታንት ቀሳውስትና ብዙዎቹ ምዕመኖቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አንጻር ትክክል እንዳልሆነ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት ጥያቄ ላይ የሚጥሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ልብ ብለህ ይሆናል፤ በተጨማሪም ባለፉት መቶ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስን ጨርሶ ለማጥፋት የተደረጉት ሙከራዎች በጣም አስገርመውህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቃቶች ከሽፈዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ተቋቁሞ ከመጥፋት መትረፍ ችሏል!
ከመጥፋት ሊተርፍ የቻለበት ምክንያት
እርግጥ ነው፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸውና ለዚህ መጽሐፍ ሲሉ ሕይወታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጥፋት ሊተርፍ የቻለበት ዋነኛው ምክንያት ከሰብዓዊ ፍቅር የላቀ ኃይል ከለላ ሆኖለት ስለነበረ ነው። በአጭር አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ሊዘልቅ የቻለው ጸሐፊዎቹ መጽሐፉን የጻፉት በአምላክ መንፈስ አመራር በመሆኑ ነው።—ኢሳይያስ 40:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:25
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ትምህርት ማንበባችንና በሥራ ላይ ማዋላችን ሕይወታችንን፣ ጤንነታችንን እና የቤተሰባችንን ሕይወት እንድናሻሽል ይረዳናል። አምላክ፣ ሰዎች ሁሉ እሱን የመውደድ፣ የማገልገልና ውሎ አድሮም ያዘጋጀውን ዘላለማዊ በረከት የማጨድ አጋጣሚ እንዲያገኙ ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ከመጥፋት ተርፎ በብዙ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ይፈልጋል። የእኛም ፍላጎት ይኸው እንደሆነ ጥርጥር የለውም!
ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) አምላክ ቅን የሆኑ ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ይኸውም ኢየሱስ ባነበባቸውና ባስተማረባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት ነው።
አንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘውና አምላክ ለሰው ልጆች ስለሰጠው መልእክት ይበልጥ እንድትማር እናበረታታሃለን። ይህን መጽሔት የሚያዘጋጁት የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። *
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ይህ አመለካከት የስቪሉ ኢሲዶር ከሚባሉት የስፔን ጳጳስ (560-636 ዓ.ም.) ጽሑፍ የመነጨ ሳይሆን አይቀርም። እኚህ ሰው እንዲህ ብለዋል፦ “ሦስት ቅዱስ ቋንቋዎች ያሉ ሲሆን እነሱም ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛና ላቲን ናቸው። እነዚህ ቋንቋዎች በዓለም ላይ ካሉ ሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ የላቁ ናቸው። ምክንያቱም ጲላጦስ የጌታችንን ክስ በመስቀሉ አናት ላይ የጻፈው በእነዚህ ሦስት ቋንቋዎች ነው።” እርግጥ ነው፣ ክሱ በእነዚህ ሦስት ቋንቋዎች እንዲጻፍ የወሰኑት አረማዊ የሆኑት ሮማውያን እንጂ በአምላክ የተመሩ ሰዎች አልነበሩም።
^ አን.28 በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች ለአንተ አመቺ ወደሆነው በመጻፍ ወይም www.watchtower.org በሚለው ድረ ገጻችን አማካኝነት ከእነሱ ጋር መገናኘት ትችላለህ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ እጅ የመግባቱ አጋጣሚ በጣም ውስን ሲሆን ይህም ቀሳውስቱ በብዙኃኑ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው አስችሏል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱሶችን ለመያዝ ወይም ለማሰራጨት የደፈሩ ሁሉ ከተያዙ ግንድ ላይ ታስረው ይቃጠሉ ወይም የዕድሜ ይፍታህ እስራት ይበየንባቸው ነበር
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸው መልሶች
ፈጣሪ ለሚከተሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ ይፈልጋል፦
● የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?
● መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?
● ሙታን የት ናቸው?
● የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ እውነተኛ ደስታ ማግኘት ስለምንችልበት መንገድ የሚገልጽ ጠቃሚ ምክር ይዟል።
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ዓመታት
636 ዓ.ም. ገደማ
የስቪሉ ኢሲዶር የተባሉት ጳጳስ ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛና ላቲን “ቅዱስ” ቋንቋዎች በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሊዘጋጅ የሚገባው በእነዚህ ቋንቋዎች ብቻ እንደሆነ ገለጹ
1079
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሪጎሪ ሰባተኛ፣ መስፍን ቭራቲስላውስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የስላቭን ቋንቋ ለመጠቀም ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት ሲሆን “ውስን እውቀት” ያላቸው ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ማግኘት እንደሌለባቸው ገለጹ
1199
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት ሳልሳዊ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎምና ለመወያየት የደፈረን ማንኛውንም ሰው እንደ መናፍቅ ይመለከቱታል። የእሳቸውን አዋጅ የጣሰ ማንኛውም ሰው ሁሉ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ተሠቃይቶ እንዲሞት ይደረጋል
1546
የትሬንት ጉባኤ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ካልሰጠች በቀር ማንኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማተም እንደማይፈቀድ ደነገገ
1559
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖል አራተኛ፣ ሕዝቡ በሚጠቀምባቸው ቋንቋዎች የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን መያዝን ከለከሉ። በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከያሉበት ተሰብስበው ይቃጠላሉ፤ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱሶቹ ባለቤቶችም አብረው ይቃጠላሉ
[የሥዕል ምንጭ]
Pope Gregory VII: © Scala/White Images/Art Resource, NY; Pope Innocent III: © Scala/Art Resource, NY; Council of Trent: © Scala/White Images/Art Resource, NY; Pope Paul IV: © The Print Collector, Great Britain/HIP/Art Resource, NY
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
From Foxe’s Book of Martyrs