በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐቀኛ መሆን ጠቃሚ ነው

ሐቀኛ መሆን ጠቃሚ ነው

ሐቀኛ መሆን ጠቃሚ ነው

“ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ይጣፍጠዋል፤ በመጨረሻ ግን አፉን ኰረት ሞልቶት ያገኘዋል።”​—ምሳሌ 20:17

በሥራ ዓለም ስኬታማ ለመሆን ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶችን መፈጸም የግድ አስፈላጊ ነው? አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ማጭበርበር ብዙውን ጊዜ ጎጂ ነው። ለምን? ምክንያቱም ሐቀኛ የሆነ ሰው ከሚያጭበረብር ሰው የበለጠ እምነት ይጣልበታል፤ እንዲህ ያለ የመተማመን ስሜት መኖሩ ደግሞ ዘላቂ ለሆነ ስኬት ወሳኝ ነው።

እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን ያለው ጥቅም

አንተ ባታስተውለውም እንኳ በሐቀኝነት ረገድ ያተረፍከው ስም ስኬታማ ለመሆንህ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ባለፈው ርዕስ ላይ የጠቀስነው ፍራንዝ ያጋጠመው ነገር ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። “ሥራ እንደ ጀመርኩ አካባቢ አሠሪዎቼ ሐቀኛና ታማኝ መሆኔን እኔ ሳላውቅ በተለያዩ ዘዴዎች ይፈትኑ ነበር። ከጊዜ በኋላ እንደተረዳሁት ፈተናዎቹን አልፌያለሁ። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ኃላፊነትና ነፃነት የተሰጠኝ ከመሆኑም ሌላ ሐቀኛ መሆኔ መልሶ ክሶኛል። እኔ የምሠራውን ሥራ በተሻለ ሁኔታ ሊሠሩ የሚችሉና ከእኔ የበለጠ እውቀት ያላቸው ሌሎች ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ አሠሪዎቼ ስለሚያምኑኝ በሥራዬ ላይ ልቆይ ችያለሁ።”

አላስፈላጊ ችግር ውስጥ አትግባ

ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው በንግድ ሥራ የተሰማራው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “በአጭር ጊዜ ለመበልጸግ ሲሉ ሕጎችን የሚያጣምሙ ግለሰቦችን ሳይ ‘ይዘገይ ይሆናል እንጂ የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀርም’ ብዬ አስባለሁ። በሌላ አባባል ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ይዋል ይደር እንጂ በሆነ መንገድ ችግር ማስከተሉ አይቀርም። አጠያያቂ የሆኑ በርካታ የንግድ አጋጣሚዎችን ላለመቀበል መርጠናል። እንደነዚህ ባሉት ሥራዎች ከተካፈሉት ኩባንያዎች ብዙዎቹ ከጊዜ በኋላ የተዘጉ ሲሆን አንዳንድ ግለሰቦችም በወንጀል ተከስሰዋል። የእኛ ኩባንያ ግን እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች አላጋጠሙትም።”

ኬን በደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ የከብት እርባታ በጀመረበት ጊዜ ለባለሥልጣናት ጉቦ በመስጠት ከውጭ የሚያስመጣቸው ዕቃዎች ቶሎ እንዲገቡለት ማድረግና ከቀረጥ ማምለጥ ይችል ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በርካታ ከብት አርቢዎች በዚህ የተለመደ አሠራር ተጠቅመዋል። እኛ ግን ሥራችንን በሐቀኝነት እናከናውን ስለነበር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ለማስገባት አሥር ዓመት ፈጅቶብናል። ታዲያ እንዲህ ማድረጋችን ጥቅም አስገኝቶልናል? አዎ! ጉቦ የከፈሉትን ሰዎች ምግባረ ብልሹ የሆኑ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጉቦ እየጠየቁ ያስቸግሯቸዋል።”

ተፈታታኝ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን መቋቋም

አንድ ድርጅት ከስሮ ሊዘጋ በሚመስልበት ጊዜ ባለቤቶቹ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም ጫናው ይበረታባቸዋል። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች በሐቀኝነት ረገድ ጥሩ ስም ማትረፍ ያለውን ጠቀሜታም ሊያሳዩ ይችላሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ የመኖሪያ ቤቶች ኢንዱስትሪ ችግር አጋጥሞት በነበረበት ጊዜ የግንባታ ድርጅቱ የከሰረበትን ቢልን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎቹ ትላልቅ ደንበኞቻችን በመክሰራቸው የነበረባቸውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዕዳ ሳይከፍሉን ድርጅታቸው ተዘጋ። ሁኔታው ጨርሶ ተስፋ አስቆራጭ በሆነበት ወቅት የእኛ ዓይነት ሥራ ከሚሠሩት ድርጅቶች ወደ አንዱ ሄጄ ሊቀጥረን ይችል እንደሆነ ጠየቅኩ። ይህ በሆነ በ48 ሰዓት ውስጥ ድርጅቱ፣ እኔንና አብዛኞቹን ሠራተኞቼን እንደሚቀጥረን ተነገረኝ። የድርጅቱ ኃላፊዎች በጥሩ ሥራዬና በሐቀኝነቴ መልካም ስም እንዳለኝ ገለጹልኝ።”

ከላይ ተሞክሯቸው የተገለጹት ሰዎች በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሌሎች የሕይወታቸው ዘርፎች እንደሚያደርጉት ሁሉ በሥራቸው ረገድም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ይከተላሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሐቀኝነታቸው በሥራቸው ስኬታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል።

እርግጥ ነው፣ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ጠቃሚ መስሎ የሚታይባቸው ሁኔታዎች እንደሚኖሩ አይካድም። ይሁንና ስኬት የሚለካው በገንዘብ ብቻ ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንተ ባታስተውለውም እንኳ በሐቀኝነት ረገድ ያተረፍከው ስም ስኬታማ ለመሆንህ አስተዋጽኦ ያደርጋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በጥሩ ሥራዬና በሐቀኝነቴ መልካም ስም እንዳለኝ ገለጹልኝ።”​—ቢል፣ ዩናይትድ ስቴትስ