በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐቀኝነትን ለማጉደል የሚገፋፉ ፈተናዎች

ሐቀኝነትን ለማጉደል የሚገፋፉ ፈተናዎች

ሐቀኝነትን ለማጉደል የሚገፋፉ ፈተናዎች

“በሥራው ዓለም ሐቀኛ መሆን ድሮ የቀረ ነገር ነው፤ ሐቀኛ ለመሆን የሚሞክሩ ሁሉ ለኪሳራ መዳረጋቸው አይቀርም።”​—ስቲቨን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በዚህ አስተያየት ትስማማለህ? ብዙውን ጊዜ ሐቀኝነትን ማጉደል ቢያንስ ጊዜያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ አይካድም። በመሆኑም ሐቀኛ ለመሆን የሚሞክሩ ሰዎች ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸዋል። ተጽዕኖ ከሚያደርጉባቸው ነገሮች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት፦

የልብ ምኞት፦ ተጨማሪ ገንዘብ ወይም የቅንጦት ዕቃ ቢያገኝ ማን ይጠላል? በመሆኑም ሐቀኝነት በጎደለው መንገድ ጥቅም የሚገኝበት አጋጣሚ ሲኖር ፈተናውን ማለፍ ከባድ ሊሆን ይችላል።

● “ኩባንያችን ኮንትራት የሚሰጣቸውን ድርጅቶች የምመርጠው እኔ ነኝ። ብዙ ጊዜ ጉቦ ይቀርብልኛል። በቀላሉ የሚገኝ ገንዘብ ለብዙ ሰዎች በጣም አጓጊ ነው።”​—ፍራንዝ፣ መካከለኛው ምሥራቅ

ትርፍን ለማሳደግ የሚደረግ ጫና፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢኮኖሚው ሁኔታ ጥሩ ባለመሆኑ በመላው ዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ቀዝቅዟል። በተጨማሪም የንግድ ተቋማት፣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚለዋወጠው ቴክኖሎጂ ያስከተለውን ሁኔታ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጨምረውን የአገር ውስጥና ዓለም አቀፋዊ ውድድር ለመቋቋም ይገደዳሉ። ሠራተኞች፣ የመሥሪያ ቤታቸው ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች ያስቀመጡላቸው ግብ ላይ ለመድረስ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም እንደሆነ ይሰማቸዋል።

● “ሌላ አማራጭ ያለን አልመሰለንም። . . . እንዲህ ካላደረግን ኩባንያውን እናከስረዋለን።”​—ራይንሃርት ሲካቼክ፣ በጉቦ ምክንያት የታሰረ​—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ

ሌሎች የሚያሳድሩት ጫና፦ አንዳንድ ጊዜ የሥራ ባልደረቦችህ ወይም ደንበኞችህ ልክ እንደ እነሱ እንድታጭበረብር ይጠይቁህ አልፎ ተርፎም ሊያስገድዱህ ይሞክሩ ይሆናል።

● “የመሥሪያ ቤታችን ደንበኛ የሆነ የአንድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ‘የበኩሉን ድርሻ’ ካልሰጠሁት ድርጅታቸው ደንበኝነቱን እንደሚያቋርጥ ነገረኝ፤ በአጭሩ ጉቦ ስጠኝ ማለቱ ነበር።”​—ዮሐን፣ ደቡብ አፍሪካ

ባሕል፦ በአንዳንድ ባሕሎች፣ ሰዎች ከተገበያዩ በኋላ ስጦታ መለዋወጣቸው የተለመደ ነው። ይሁንና የስጦታው መጠንና ስጦታው የተሰጠበት ሁኔታ የንግድ ልውውጡ ሐቀኝነት የጎደለው እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። በብዙ አገሮች ምግባረ ብልሹ የሆኑ ባለሥልጣናት ሥራቸውን ለማከናወን ገንዘብ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፤ እንዲሁም ገንዘብ ለሰጧቸው ሰዎች ለየት ያለ ነገር ያደርጉላቸዋል።

● “ምንጊዜም ቢሆን በጉርሻና በጉቦ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አስቸጋሪ ነው።”​—ዊሊያም፣ ኮሎምቢያ

የኑሮ ሁኔታ፦ በድህነት በደቀቁ እንዲሁም ሕግና ሥርዓት በጠፋባቸው አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ሐቀኝነታቸውን ለማጉደል ጫናው ይበረታባቸዋል። እንደነዚህ ባሉ አካባቢዎች ለማጭበርበር ወይም ለመስረቅ እምቢተኛ የሆኑ ሰዎች ለቤተሰቦቻቸው እንደማያስቡ ተደርገው ይቆጠራሉ።

● “ስታጭበረብር እስካልተያዝክ ድረስ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም የተለመደ፣ አስፈላጊና ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።”​—ቶማሲ፣ ኮንጎ ኪንሻሳ

ሐቀኝነት የሚጠፋው እንዴት ነው?

ሰዎች ሐቀኝነት እንዲያጎድሉ የሚደረግባቸው ጫና ከፍተኛ ተጽዕኖ ያስከትላል። በአውስትራሊያ በሥራ አስኪያጆች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከ10 ሰዎች ውስጥ 9ኙ ጉቦና ሙስና “ስህተት ቢሆንም የግድ አስፈላጊ እንደሆነ” ይሰማቸዋል። በጥናቱ የተካፈሉት ሥራ አስኪያጆች፣ ኮንትራቶችን ለማግኘት ወይም ኩባንያቸውን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ሲሉ ስህተት እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች እንደሆኑ ተናግረዋል።

እንዲያም ሆኖ በማጭበርበር ድርጊት የሚካፈሉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸውን ሐቀኛ አድርገው ይቆጥራሉ። ስለ ራሳቸው ያላቸውን አመለካከት ከምግባራቸው ጋር የሚያስታርቁት እንዴት ነው? ጆርናል ኦፍ ማርኬቲንግ ሪሰርች እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ትርፍ ለማግኘት ብለው ቢያጭበረብሩም፣ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዳላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ሲሉ በተወሰነ መጠን ሐቀኛ በመሆን ራሳቸውን ያታልላሉ።” የሕሊናቸውን ወቀሳ ለማብረድ ሲሉ፣ ለሚፈጽሙት የማጭበርበር ድርጊት ሰበብ ለማቅረብና ድርጊቱን ለማስተባበል ወይም ቀላል ለማስመሰል ይሞክራሉ።

ለምሳሌ ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች ለዘብ ባሉ ቃላት ይገለጻሉ። መዋሸት ወይም ማጭበርበር “መቀላጠፍ” ወይም “ብልጥ መሆን” ይባላል። ጉቦ ደግሞ “መጠቃቀም” ወይም “እጅ መንሻ” ተብሎ ይገለጻል።

ሌሎች ደግሞ ለሐቀኝነት የሚሰጠውን ፍቺ በማዛባት አጠያያቂ ለሆኑ ተግባሮች ማሳበቢያ ለማግኘት ይሞክራሉ። ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር በሚያያዝ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠራው ቶም “ሰዎች ሐቀኛ እንደሆኑ የሚሰማቸው እውነተኛ የሆነውን ነገር ስላደረጉ ሳይሆን በሕግ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላላደረጉ ነው” ብሏል። በንግዱ ዓለም በአመራር ቦታ ላይ ይሠራ የነበረው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት በሚጋለጥበት ጊዜ እንደ ነውር ቢታይም ሳትያዝ ልታመልጥ ከቻልክ ተቀባይነት እንዳለው ነገር ይቆጠራል። ሳይያዙ የሚያመልጡ ሰዎች ‘በብልጠታቸው’ ይደነቃሉ።”

እንዲያውም ብዙዎች ስኬታማ ለመሆን ማጭበርበር የግድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። በንግድ ዓለም የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያለው አንድ ሰው እንደተናገረው በንግዱ መስክ የሚታየው “የፉክክር መንፈስ ብዙ ጊዜ ሰዎች ‘ሥራውን ለማግኘት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት የለብህም’ እንዲሉ ይገፋፋቸዋል።” ይሁንና ይህ እውነት ነው? ወይስ ሐቀኝነት የጎደላቸውን ድርጊቶች ትክክል እንደሆኑ ለማስመሰል የሚፈልጉ ሰዎች ‘የውሸት ምክንያት በማቅረብ ራሳቸውን እያታለሉ’ ነው? (ያዕቆብ 1:22) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ሐቀኝነት ያሉትን ጥቅሞች እንመለከታለን።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሰዎች ሐቀኛ እንደሆኑ የሚሰማቸው እውነተኛ የሆነውን ነገር ስላደረጉ ሳይሆን በሕግ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላላደረጉ ነው”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች ስኬታማ ለመሆን ማጭበርበር የግድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ