በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐቀኝነት እውነተኛ ስኬት ያስገኛል

ሐቀኝነት እውነተኛ ስኬት ያስገኛል

ሐቀኝነት እውነተኛ ስኬት ያስገኛል

“አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [አይደለም]።”​—ሉቃስ 12:15

በሕይወት ውስጥ ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ ሠርቶ ገንዘብ ማግኘት ነው። አምላክ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን የማሟላት ኃላፊነት ጥሎብናል።​—1 ጢሞቴዎስ 5:8

ይሁንና ገንዘብም ሆነ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸው ነገሮች መሠረታዊ ፍላጎትህን ለማሟላት የሚያገለግሉ ከመሆን አልፈው በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ቢይዙስ? በሕይወትህ ውስጥ ዋነኛ ዓላማህ ገንዘብ መሰብሰብ ቢሆንስ? ሀብትን ለማካበት ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች እዚህ ግባቸው ላይ ለመድረስ ሲሉ ማጭበርበር ይቀናቸዋል። ሐቀኛ አለመሆን እውነተኛ ስኬት እንደማያስገኝ የሚገነዘቡት በጣም ዘግይተው ነው። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ገንዘብን መውደድ ብዙ ሥቃይ ያስከትላል።​—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

ስኬት ማለት ሀብት መሰብሰብ ብቻ እንዳልሆነ የተገነዘቡ አራት ሰዎችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ለራሳችን ያለን ግምት

“ከበርካታ ዓመታት በፊት፣ የሚሊዮን ዶላር የሕይወት ኢንሹራንስ መግዛት የሚፈልግ አንድ ሰው አነጋግሬ ነበር። ይህን ኢንሹራንስ ብሸጥ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ይከፈለኝ ነበር። ሆኖም ግለሰቡ ኢንሹራንሱን የሚገዛው ለእኔ ከሚከፈለኝ ገንዘብ ግማሹን ከሰጠሁት ብቻ እንደሆነ ነገረኝ። እኔም የጠየቀኝ ነገር ከሙያው ሥነ ምግባር ጋር የሚጋጭ ከመሆኑም በላይ ሕገ ወጥ እንደሆነ ገለጽኩለት።

“ሐሳቡን ለማስቀየር ስል፣ ‘የግል ሕይወትህንና ገንዘብህን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ሐቀኛ ላልሆነ ሰው መስጠት ትፈልጋለህ?’ ብዬ ጠየቅሁት። አቋሜን በድጋሚ ከገለጽኩለት በኋላ ኢንሹራንሱን በእኔ በኩል መግዛት ከፈለገ እንደገና ሊያነጋግረኝ እንደሚችል ጠቆምኩት። ሆኖም ግለሰቡ ከዚያ በኋላ ተመልሶ አልመጣም።

“ይህ ሰው በጠየቀኝ ነገር ተስማምቼ ቢሆን ኖሮ ንጹሕ አቋሜ ይጎድፍ እንዲሁም እንደ አንድ ክርስቲያን መጠን ለራሴ ያለኝ ግምት ይቀንስ ነበር። ሐቀኛ ባልሆነ ድርጊት እንድካፈል ላደረገኝ ሰው ባሪያ እሆን ነበር።”​—ዶን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የአእምሮ ሰላም

በዚህ መጽሔት መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ዳኒ፣ የጎበኘው ፋብሪካ የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ማሟላት ስለመቻሉ ቢዋሽ ኖሮ ጠቀም ያለ ጉቦ ማግኘት ይችል ነበር። ታዲያ ዳኒ ምን ምላሽ ሰጠ?

“ሥራ አስኪያጁን ለመስተንግዶው ካመሰገንኩት በኋላ ገንዘቡን መለስኩለት። ግለሰቡ ገንዘቡን እንድወስድ ጫና ያደረገብኝ ከመሆኑም ሌላ ፋብሪካቸው የመሥሪያ ቤታችንን የጥራት መመዘኛ ካለፈ ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚሰጠኝ ቃል ገባልኝ። እኔ ግን ገንዘቡን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆንኩም።

“ገንዘቡን ተቀብዬ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ ይታወቅ ይሆን የሚለው ስጋት ሁልጊዜ ይረብሸኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ አለቃዬ ስለ ሁኔታው በሆነ መንገድ ሰማ። ሐቀኝነት የጎደለው ምንም ነገር ባለማድረጌ እፎይታና ታላቅ ደስታ ተሰማኝ። ‘ስስታም ሰው በቤተ ሰቡ ላይ ችግር ያመጣል፤ ጕቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል’ የሚለው በ⁠ምሳሌ 15:27 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ወደ አእምሮዬ መጣ።”​—ዳኒ፣ ሆንግ ኮንግ

የቤተሰብ ደስታ

“በግንባታ መስክ ተሰማርቼ በግሌ እሠራለሁ። ደንበኞችን ማታለል ወይም ከግብር ማምለጥ የምችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ይሁን እንጂ ምንጊዜም በሐቀኝነት ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ በማድረጌ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ተጠቅመናል።

“ሐቀኝነት ከሥራ ወይም ከንግድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በመላ ሕይወታችን መታየት ያለበት ነገር ነው። የትዳር ጓደኛችሁ አምላክ ስለ ሐቀኝነት ያወጣውን መሥፈርት እንደማይጥስ ማወቃችሁ በቤተሰባችሁ ውስጥ ይበልጥ የመተማመን መንፈስ እንዲኖር ያደርጋል። ታማኝነትን በፈለግኸው ጊዜ እንደምታጠልቀውና ሳትፈልግ ደግሞ እንደምታወልቀው ልብስ አድርገህ እንደማታየው የትዳር ጓደኛህ ማወቋ በመካከላችሁ የመተማመን ስሜት እንዲኖር ያደርጋል።

“በዓለም ላይ ትልቅ የተባለው ኩባንያ ባለቤት ብትሆን እንኳ ይህ በቤተሰብህ ውስጥ ችግር እንዳይኖር ሊያደርግ አይችልም። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተሌ ሕይወቴ ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን ረድቶኛል። ገንዘብና ስግብግብነት የሚቆጣጠሩት ይህ ዓለም በራሱ መንገድ ስለማይመራኝ ከቤተሰቤ ጋር የማሳልፈው ጊዜ አለኝ።”​—ደርዊን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት

“ሥራዬ ለኩባንያችን የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን መግዛትን ያካትታል። አንዳንድ ጊዜ የሽያጭ ሠራተኞች፣ ኩባንያችን ዕቃ ሲገዛ ማግኘት የሚገባውን ቅናሽ ሙሉ በሙሉ ለኩባንያው ከመስጠት ይልቅ የተወሰነውን ገንዘብ ለእኔ ሊሰጡኝ እንደሚችሉ ይነግሩኛል። ነገር ግን ይህን ማድረግ ከኩባንያችን እንደ መስረቅ ይሆንብኛል።

“የማገኘው ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ገንዘብ ባገኝ ይጠቅመኛል። ይሁን እንጂ ንጹሕ ሕሊና ከመያዝና በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ከማግኘት ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ማንኛውንም ግብይት ሳካሂድ በ⁠ዕብራውያን 13:18 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በመከተል ‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር’ እጥራለሁ።”​—ራኬል፣ ፊሊፒንስ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የሐቀኝነት መርሆች

ተቀባይነት ያለው የሙያ ሥነ ምግባር ከቦታ ቦታ ይለያያል። ይሁን እንጂ ከሙያ ሥነ ምግባር አኳያ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መሠረት ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። ሐቀኝነት የሚንጸባረቅበት አሠራር የሚከተሉትን ስድስት መርሆች ያካተተ ነው፦

እውነተኛ

መርህ፦ “አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ።”​—ቆላስይስ 3:9

ታማኝ

መርህ፦ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፣ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን።”​—ማቴዎስ 5:37

እምነት የሚጣልበት

መርህ፦ “የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ።”​—ምሳሌ 25:9

ሐቀኛ

መርህ፦ “ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ፣ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል።”​—ዘፀአት 23:8

ፍትሐዊ

መርህ፦ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው።”​—ማቴዎስ 7:12

ሕጋዊ

መርህ፦ “ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ . . . ስጡ።”​—ሮም 13:7

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በሥራ ዓለም ታማኝ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ወስን። ለምሳሌ፣ ቅድሚያ የምትሰጠው ሀብት ለማካበት ነው ወይስ በአምላክ ዘንድ ጥሩ አቋም ለመያዝ?

አስቀድመህ ተዘጋጅ። ሐቀኝነትህን ሊፈትኑ የሚችሉ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ አስቀድመህ በማሰብ ምን ምላሽ እንደምትሰጥ ተዘጋጅ።

አቋምህን አሳውቅ። አዲስ ሥራ በምትጀምርበት ጊዜ የምትመራባቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች ለሌሎች በዘዴ አሳውቅ።

የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ወይም የሙያ ሥነ ምግባርን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ሲያጋጥሙህ የአንተን እሴቶች ከሚጋራ ሰው ምክር ጠይቅ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐቀኛ ከሆንክ የአእምሮ ሰላም ይኖርሃል