በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወት መኖር ሲታክትህ

በሕይወት መኖር ሲታክትህ

በሕይወት መኖር ሲታክትህ

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት እስኪያስቡ ድረስ ተስፋ የሚቆርጡበት መሠረታዊ ምክንያት ምን እንደሆነ ይናገራል። የአምላክ ቃል ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር ይናገራል። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ያለባቸው ጫና ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ እንደሆነባቸው ይሰማቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ መክብብ 7:7) አንድ ሰው በኑሮ ጭንቀቶች በሚዋጥበት ጊዜ ከሥቃይ እፎይታ ለማግኘት ሲል የገዛ ሕይወቱን ስለማጥፋት ሊያስብ ይችላል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ወደ አእምሮህ የሚመጣብህ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም!

ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ሊመስል ቢችልም እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ያለኸው አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ፤ የሚያሳዝነው በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ከአንድ ዓይነት ችግር ጋር እየታገለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ” ይናገራል። (ሮም 8:22) ያለብህ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ የሚያገኝ ባይመስልም ብዙውን ጊዜ ነገሮች በጊዜ ሂደት መሻሻላቸው አይቀርም። ታዲያ እስከዚያው ድረስ ምን ሊረዳህ ይችላል?

የሚሰማህን ነገር ለጎለመሰና እምነት ለምትጥልበት ወዳጅህ አዋየው። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፣ ደግሞም ለመከራ ቀን እንደተወለደ ወንድም ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:17 NW) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዮብ የተባለ ጻድቅ ሰው ከባድ መከራ በደረሰበት ወቅት ስለተሰማው ነገር ለሌሎች ተናግሮ ነበር። ኢዮብ በወቅቱ የተሰማውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ፤ ስለዚህም ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቃለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።” (ኢዮብ 10:1) የሚሰማህን ነገር ለሌሎች ማካፈልህ ያጋጠመህን የስሜት ውጥረት ሊቀንስልህ የሚችል ሲሆን ስለ ሁኔታው ያለህ አመለካከትም እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። *

ለአምላክ የልብህን ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። አንዳንዶች ጸሎት ውጥረትን ከማስታገስ ያለፈ ፋይዳ የለውም የሚል አመለካከት አላቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን ከዚህ የተለየ ነው። መዝሙር 65:2 ይሖዋ አምላክን ‘ጸሎት ሰሚ’ በማለት የሚጠራው ሲሆን 1 ጴጥሮስ 5:7 ደግሞ “እሱ ስለ እናንተ ያስባል” በማለት ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ የመተማመንን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፦

“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”​ምሳሌ 3:5, 6

“[ይሖዋ] ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።”​መዝሙር 145:19

“በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”​1 ዮሐንስ 5:14

“እግዚአብሔር ከክፉዎች ሩቅ ነው፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።”​ምሳሌ 15:29

እየደረሱብህ ያሉትን ችግሮች ለአምላክ የምትነግረው ከሆነ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁልጊዜ በእርሱ ታመኑ፤ ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ” በማለት የሚያበረታታበት በቂ ምክንያት አለው።​—መዝሙር 62:8

ተጨማሪ እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ

ራሳቸውን የሚያጠፉ አብዛኞቹ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ በመንፈስ ጭንቀት ሲሠቃዩ የኖሩ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። * ይህም የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማል። አንድ ሐኪም በጭንቀት ለሚሠቃየው ግለሰብ መድኃኒት ሊያዝለት ወይም በአመጋገቡ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ምክር ሊለግሰው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ከሕክምናው በተጨማሪ ፕሮግራም አውጥቶ ስፖርት መሥራት ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ብዙ ሰዎች የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን እርዳታ በማግኘታቸው ተጠቅመዋል። *

መጽሐፍ ቅዱስ መጽናኛና ተስፋ የሚያስገኝ ብዙ ሐሳብ ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ በ⁠ራእይ 21:4 ላይ ይሖዋ አምላክ የሚያደርገውን ነገር አስመልክቶ ሲናገር “እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል” ይላል። ይህ አምላክ የገባው ቃል ሲሆን በዚህ ተስፋ ላይ ማሰላሰልህ እፎይታ ሊያስገኝልህ ይችላል።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ይህን ተስፋ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እያካፈሉ ነው። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች በዚህ አስጨናቂ ዘመንም እንኳ እውነተኛ ተስፋ እያገኙ ነው። ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ወዳለ የመንግሥት አዳራሽ ሄደህ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላለህ። በተጨማሪም www.watchtower.org የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 አንዳንዶች ራስን ማጥፋትን ለመከላከል ወደ ተቋቋሙ ድርጅቶች ወይም ወደ ሥነ አእምሮ ሕክምና ተቋማት በመደወል እርዳታ ማግኘት ችለዋል።

^ አን.13 የመንፈስ ጭንቀትን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሐምሌ 2009 ንቁ! መጽሔትን ከገጽ 3-9 ተመልከት።

^ አን.13 ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝ እርዳታ

● “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”​—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

● “እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።”​—መዝሙር 34:4

● “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።”​—መዝሙር 34:18

● “ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል።”​—መዝሙር 147:3

[በገጽ 17 እና 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ራስህን የማጥፋት ሐሳብ ሲመጣብህ . . .

የሚሰማህን ነገር እምነት ለምትጥልበት ወዳጅህ አዋየው

ለአምላክ የልብህን ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው

የሕክምና ባለሙያ የሚሰጠውን እርዳታ ለማግኘት ጣር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ለጓደኞችና ለቤተሰብ የተሰጠ ምክር

አንድ የተጨነቀ ሰው ራሱን ለማጥፋት እያሰበ መሆኑን ብዙውን ጊዜ ከሁሉ ቀድመው የሚያውቁት የቤተሰቡ አባላትና ጓደኞቹ ናቸው። በዚህ ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የግለሰቡን ሕይወት ማዳን ትችላላችሁ! የተጨነቀው ሰው ሲናገር ጭንቀቱ እንደሚሰማችሁ በሚያሳይ መንገድ አዳምጡ። ችግሩን እንደተረዳችሁለት እንዲያውቅ አድርጉ። መጽሐፍ ቅዱስ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) የተጨነቀው ሰው እርዳታ እንዲያገኝ አበረታቱት፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ እንዲያገኝ እገዛ አድርጉለት።