በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኢንተርኔት እንዳትጭበረበር ተጠንቀቅ!

በኢንተርኔት እንዳትጭበረበር ተጠንቀቅ!

በኢንተርኔት እንዳትጭበረበር ተጠንቀቅ!

በፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ዊልያም ጡረታ የወጣ መምህር ነው፤ አንድ ቀን የኢንተርኔት አገልግሎት ከሚሰጠው ድርጅት የተላከ የሚመስል ኢሜይል ደረሰው። ኢሜይሉ፣ ዊልያም ለድርጅቱ የአገልግሎት ሒሳብ የሚከፍልበት መረጃ እንደጠፋ ይገልጻል። ዊልያም ከኢሜይሉ ጋር የተላከለትን ቅጽ ከሞላ በኋላ መልሶ ላከው። የግል መረጃዎቹን የላከው በኩዊንስ፣ ኒው ዮርክ ለሚኖር ሺቫ ለተባለ አጭበርባሪ እንደሆነ አላወቀም ነበር። በማግስቱ ሺቫ በዊልያም የክሬዲት ካርድ ቁጥር በመጠቀም የሐሰት ሰነድ ለመሥራት የሚያገለግል ማተሚያ ገዛ። ለዊልያም የደረሰው መልእክት ሺቫ ከላካቸው 100,000 ኢሜይሎች አንዱ ነበር። መርማሪዎች እንደገለጹት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ለኢሜይሉ ምላሽ በመስጠታቸው ተጭበርብረዋል።

በኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ የምትኖር የ56 ዓመት ሴት ብሪታንያዊ መሐንዲስ ከመሰላት ሰው ጋር በኢንተርኔት የፍቅር ግንኙነት ትጀምራለች። ግለሰቡ በናይጄሪያ የሚኖር የ27 ዓመት ሰው እንደሆነና እያጭበረበራት እንዳለ የታወቀው ይህች ሴት 47,000 የአሜሪካ ዶላር ካወጣች በኋላ ነበር። *

የሚያሳዝነው ነገር በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈጸም ማጭበርበር እየተስፋፋ መጥቷል። ኮንስዩመር ሪፖርትስ የተባለው ድርጅት ስለ ኢንተርኔት ባወጣው የ2010 ዘገባ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በኢንተርኔት የሚፈጸም ማጭበርበር በሚያስደነግጥ መጠን እየጨመረ ከመሄዱም በላይ በሸማቾች ላይ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ኪሣራ እያስከተለ ነው። በኮምፒውተር ቫይረስ አማካኝነት የሚሰነዘረው ጥቃት ካለፈው ዓመት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መካከል 40 በመቶ በሚሆኑት ላይ ጉዳት አድርሷል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በተደጋጋሚ የኮምፒውተር ቫይረስ እንዳጋጠማቸው ሪፖርት አድርገዋል።” እንዲህ ካለው አደጋ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ከማየታችን በፊት አጭበርባሪዎች ከሚጠቀሙባቸው በርካታ ዘዴዎች እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

የሚያጭበረብሩት እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ከሰዎች ጋር የሚገናኙት በኢሜይል አማካኝነት ነው። ለዊልያም የደረሰው ዓይነት ከገንዘብ ጋር የተያያዙ የግል መረጃዎችን የሚጠይቅ መልእክት ፊሺንግ ኢሜይል ይባላል። አንድ ዓሣ አጥማጅ፣ ዓሣዎቹን ለመሳብ መንጠቆው ጫፍ ላይ ምግብ እንደሚያስቀምጥ ሁሉ በዚህ ዓይነቱ ኢሜይል የሚጠቀሙ አጭበርባሪዎችም ሕጋዊ የሚመስል ድረ ገጽ ተጠቅመው ሰዎችን በማታለል የይለፍ ቃላቸውን (ፓስወርድ)፣ የክሬዲት ካርድ ቁጥራቸውን ወይም የባንክ ሒሳብ መረጃቸውን እንዲሰጧቸው ያደርጋሉ። ኢሜይል ኤክስትራክተር የተባለ የኮምፒውተር ፕሮግራም በመጠቀም የኢሜይል አድራሻህን ሊያገኙ ይችላሉ።

እንደነዚህ ካሉት ፊሺንግ ኢሜይሎች መካከል አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት መረጃ ባትሰጥ እንኳ አጭበርባሪዎች የፈለጉትን ነገር እንዲያገኙ ይረዷቸዋል። አንድን ኢሜይል መክፈትህ ብቻ ስፓይ ሶፍትዌር የሚባል ፕሮግራም ወደ ኮምፒውተርህ እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ፕሮግራሞች በኮምፒውተርህ የምታከናውናቸውን ነገሮች ሊመዘግቡ ይችላሉ። ከእነዚህ ፕሮግራሞች አንዳንዶቹ የምትጫናቸውን የኮምፒውተር ቁልፎች የሚመዘግቡ ሲሆን አጭበርባሪዎቹ በዚህ ተጠቅመው የይለፍ ቃልህን እና የግል መረጃዎችህን መስረቅ ይችላሉ። ሌሎች ፕሮግራሞች ደግሞ አጭበርባሪ ወደሆኑ ድረ ገጾች ይመሩሃል። ታዲያ ራስህን ለመጠበቅ ማድረግ የምትችለው ነገር ይኖር ይሆን?

ማድረግ የምትችለው ነገር

አጠራጣሪ ወደሆኑ ድረ ገጾች የሚመሩ ኢሜይሎች ሲደርሱህ ጥንቃቄ አድርግ። እንዲህ ያሉ ኢሜይሎችን ስትከፍት አጭበርባሪዎች ትሮጃን ሆርስ ወይም ትሮጃን በሚባለው ፕሮግራም አማካኝነት አንተ ሳታውቅ ኮምፒውተርህ ውስጥ ያሉ የግል መረጃዎችህን ሊያገኙ ይችላሉ። አጭበርባሪዎች ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘትና መረጃዎችን ለመስረቅ የሚያግዟቸውን ስፓይ ሶፍትዌሮች ኮምፒውተርህ ላይ ለመጫን ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉ ድረ ገጾች፣ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የሚገኙባቸው ድረ ገጾች፣ ምንጫቸው የማይታወቅ ሶፍትዌሮችን የሚያቀርቡ ድረ ገጾች እና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ይገኙባቸዋል። በተጨማሪም ለማመን የሚያዳግት ትርፍ እንደሚያስገኙ ለሚገልጹ የኢሜይሎች መልእክቶች መልስ አትስጥ።

“ኮምፒውተርህ አደጋ ላይ ነው! ኮምፒውተርህን ከአደጋ ለማዳን እዚህ ጋ ተጫን!” ወይም “ነፃ ስክሪንሴቨሮች ትፈልጋለህ? እዚህ ጋ ተጫን” የሚል የኢንተርኔት መልእክት ደርሶህ ያውቅ ይሆናል። ይህን ብታደርግ ኮምፒውተርህ ውስጥ ስፓይ ሶፍትዌር ሊገባ ይችላል።

በኢንተርኔት አማካኝነት ሥራ የምትፈልግ ከሆነም ተጠንቀቅ። አጭበርባሪዎች፣ የማታለያ ድረ ገጾችን በመጠቀም “የመመዝገቢያ ክፍያ” እና ሌላው ቀርቶ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ የግል መረጃዎችን ይሰበስባሉ።

ሌቦች በአሁኑ ጊዜ እጅግ በመራቀቃቸው ወደ ትላልቅ ኩባንያዎች ወይም ገንዘብ ነክ ተቋማት መሄድ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው የድርጅቶቹን የመረጃ ማዕከል ጥሰው በመግባት መረጃዎችን መስረቅ ችለዋል። በጥር 2007 በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት አንድ ትልቅ የገበያ ማዕከል በኮምፒውተር ላይ ያስቀመጠውን መረጃ ወንጀለኞች መጥለፍ ቻሉ፤ በዚህ መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የድርጅቱን ደንበኞች የክሬዲት ካርድና ሌሎች መረጃዎች ማግኘት ችለዋል። በናይጄሪያ ወንጀለኞች የበርካታ ባንኮችን የመረጃ ማዕከሎች ጥሰው በመግባት የ1.5 ሚሊዮን ሰዎችን የግል መታወቂያ ቁጥሮች የሰረቁ ሲሆን በእነዚህ ቁጥሮች በመጠቀም ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች የሰዎቹን ገንዘብ ወስደዋል። በአሁኑ ጊዜ አጭበርባሪ ሠራተኞችና የኮምፒውተር መረጃ ጠላፊዎች የሰረቋቸውን የክሬዲት ካርድ መረጃዎችንና የግለሰቦችን ሙሉ መረጃዎች በኢንተርኔት ላይ የሚሸጡበት የደራ ገበያ አለ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ከዚህ ቀደም በወጡ የንቁ! መጽሔት እትሞች ላይ በኢንተርኔት አማካኝነት መጠናናት ያሉትን አደጋዎች የሚጠቁም ሐሳብ ቀርቧል። ንቁ! ግንቦት 2005 ከገጽ 26-28⁠ን እና ሰኔ 2005 ከገጽ 18-20⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ፊሺንግ ኢሜይል፦ አጭበርባሪዎች ሕጋዊ የሚመስል ድረ ገጽ ተጠቅመው ሰዎችን በማታለል የይለፍ ቃላቸውን፣ የክሬዲት ካርድ ቁጥራቸውን ወይም የባንክ ሒሳብ መረጃቸውን እንዲሰጧቸው የሚያደርጉበት ኢሜይል

ስፓይ ሶፍትዌር፦ በኮምፒውተርህ ላይ የምታከናውናቸውን ነገሮች የሚመዘግብ ፕሮግራም

ትሮጃን ሆርስ፦ ምንም ጉዳት የሌለው ሥራ የሚያከናውን እያስመሰለ በኮምፒውተርህ ላይ ያለውን መረጃ ሌሎች እንዲያገኙት የሚያደርግ ፕሮግራም

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

እንዳትጭበረበር ተጠንቀቅ

በኢንተርኔት እንዳትጭበረበር የሚከተሉትን እርምጃዎች ውሰድ፦

1 የኮምፒውተርህ መከላከያ (ፋየርዎል) ሁልጊዜ የሚሠራ መሆኑን እንዲሁም ኮምፒውተርህን የሚያሠራውን ፕሮግራም ጨምሮ የቫይረስ መከላከያ ፕሮግራሞች (አንቲቫይረስ) እና ሌሎች ፕሮግራሞች ጊዜ ያለፈባቸው አለመሆናቸውን አዘውትረህ አረጋግጥ።

2 በኮምፒውተርህ ላይ የሚገኙ ፋይሎችህን በየጊዜው እንደ ዲቪዲ ባሉ ነገሮች ላይ ገልብጠህ ቅጂዎቹን ደህና ቦታ አስቀምጥ።

3 አስተዋይ ሁን። በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ መረጃዎችን ለማመን አትቸኩል። ምሳሌ 14:15 “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል።

4 ስግብግብ አትሁን። (ሉቃስ 12:15) አንዳንድ ነገሮች “በነፃ” እንደሚገኙ ወይም በጣም አነስተኛ በሆነ ዋጋ እንደሚሸጡ የሚገልጹ ማስታወቂያዎችን የያዙ ድረ ገጾችን አትመን። ፊሺንግ ኢሜይል ሊሆኑ ይችላሉ።

5 ከማታውቃቸው ግለሰቦች የተላኩ ኢሜይሎች ወይም አጭር መልእክቶች ከደረሱህ በተለይ ደግሞ ወደ ሌላ ድረ ገጽ የሚመሩ ወይም የግል መረጃዎችን (ለምሳሌ የይለፍ ቃልህን እንድታረጋግጥላቸው) የሚጠይቁ ከሆኑ ተጠንቀቅ።​ምሳሌ 11:15

6 ሌሎች ሰዎች በግምት ሊደርሱባቸው የማይችሉ የይለፍ ቃሎችን ምረጥ። የኢንተርኔት የይለፍ ቃልህን በየጊዜው ቀይር፤ የተለያዩ የኢንተርኔት አድራሻዎች ካሉህ ተመሳሳይ የሆነ የይለፍ ቃል አትጠቀም።

7 የክሬዲት ካርድ ወይም የባንክ ሒሳብ መረጃህን አስተማማኝ ለሆኑ ድረ ገጾች ብቻ ስጥ።

8 የድረ ገጽ አድራሻዎችን፣ በተለይ ደግሞ የገንዘብ ተቋማትን አድራሻ በምትጽፍበት ጊዜ በትክክል መጻፍህን አረጋግጥ። አንድ ፊደል ብትሳሳት ወደ አጭበርባሪዎች ድረ ገጽ ልትገባ ትችላለህ።

9 እንደ ክሬዲት ካርድ ቁጥር የመሳሰሉትን ጥንቃቄ የሚያሻቸው መረጃዎች በምትልክበት ጊዜ ሁሉም ሰው ሊያየው በማይችል መንገድ ጻፈው፤ ልከህ እንደጨረስክም ድረ ገጹን በትክክል ዝጋው።

10 በክሬዲት ካርድ አማካኝነት ያደረግኸውን ግብይትና የባንክ ሒሳብ መግለጫህን በየጊዜው በጥንቃቄ መርምር። እንግዳ የሆነብህ ነገር ካለ ዛሬ ነገ ሳትል ኩባንያውን አነጋግር።

11 ለማንም ሰው ክፍት በሆኑ ገመድ አልባ መገናኛዎች (ዋይ-ፋይ) በምትጠቀምበት ጊዜ ሌቦች መረጃዎችህን ሰርቀው አጭበርባሪ ወደሆኑ ድረ ገጾች ሊመሩህ ስለሚችሉ ጥንቃቄ አድርግ።

12 “ይህን የይለፍ ቃል ሌላ ጊዜ እንዳስታውስህ ትፈልጋለህ?” ለሚለው ጥያቄ ‘አዎ’ የሚል መልስ አትስጥ። ምክንያቱም ትሮጃን የሚባሉት ፕሮግራሞች የመዘገብካቸውን የይለፍ ቃሎች ሊሰርቁብህ ይችላሉ።