በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ጥሩ ገንዘብ ያስገኝልኝ የነበረውን ሥራዬን የተውኩበት ምክንያት (ሰኔ 2010) በዚህ ርዕስ ሥር ላወጣችሁት ሐሳብ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንኩ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል! ዕድሜዬ 39 ዓመት ሲሆን ብቻዬን ሦስት ልጆች እያሳደግኩ ነው። ሩሲያ ውስጥ እኔ በምኖርበት አካባቢ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሆኖም የማርታ ቴሬሳ ማርከስ ተሞክሮ አንዳንድ እርምጃዎችን እንድወስድ አነሳስቶኛል። ማርታ ቤቷ ያዘጋጀችውን ተማሊ መንገድ ላይ በመሸጥ ቤተሰቧን እንደምታስተዳድርና ይህም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድትካፈል የረዳት መሆኑን ተሞክሮው ይናገራል። ስለዚህ እኔም የእሷን ምሳሌ በመከተል ፒሮሽኪ የሚባለውን የሩሲያ ብስኩት አዘጋጅቼ ለመሸጥ ወሰንኩ። እናም ተሳካልኝ! በአሁኑ ወቅት ይህን ሥራ በቤተሰብ ሆነን እየሠራን እንገኛለን። ይህም ልጆቼ ለወደፊት ሕይወታቸው የሚጠቅማቸውን ችሎታ እንዲያዳብሩ የረዳቸው ከመሆኑም በላይ ከበፊቱ የበለጠ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሆነዋል።

ጂ. ኤም.፣ ሩሲያ

የመንተባተብን ችግር ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው? (ግንቦት 2010) የመንተባተብን ችግር በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን። የመንተባተብ ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ ሊጠቅሟቸው የሚችሉ ብዙ ውጤታማ ዘዴዎች መኖራቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ተግተን እየሠራን ነው።

ጄ. ኤፍ.፣ የመንተባተብ ችግር ያለባቸውን ሰዎች የሚረዳ ድርጅት ፕሬዚዳንት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የወጣቶች ጥያቄ . . . መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን እንደሚል እንዴት ማስረዳት እችላለሁ? (ታኅሣሥ 2010) ለአሥር ዓመታት በትዳር ዓለም ያሳለፍኩ ሲሆን አንድ ልጅም አለኝ። ግብረ ሰዶም የመፈጸም ፍላጎት ያለኝ በመሆኑ ከዚህ “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ጋር በየቀኑ እየታገልኩ ነው። ትዳር መያዜ ይህን ስሜት ሊያጠፋው አልቻለም። እንዲህ ያለውን ምኞት መቆጣጠር እንደማልችል ስለሚሰማኝ በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እዋጥ ነበር። ይህን ርዕስ ካነበብኩ በኋላ ግን ምንም የማይሳካልኝ ሰው እንደሆንኩ አድርጌ ራሴን መመልከቴን አቆምኩ። አሁን በዚህ ስሜት ላለመሸነፍ የማደርገው ትግል ተሳክቶልኛል፤ እንዲህ ያለው ግብ ላይ መድረስ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር አይደለም።​—2 ቆሮንቶስ 12:7

ስም አልተጠቀሰም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ግብረ ሰዶም የመፈጸም ፍላጎት ያደረብኝ ገና የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። አሁን 61 ዓመቴ ሲሆን ይህ ስሜት እስካሁን ከውስጤ አልጠፋም። ለተቃራኒ ፆታ የፍቅር ስሜት ያላቸው ሰዎችም እንኳ ከዝሙት መሸሽ እንዳለባቸው እንዲሁም “የማግባት አጋጣሚያቸው የመነመነ በነጠላነት የሚኖሩ በርካታ ሰዎችና በደረሰበት የአካል ጉዳት የተነሳ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የማይችል የትዳር ጓደኛ ያላቸው ብዙ ያገቡ ሰዎች” የፆታ ስሜታቸውን ማርካት ባይችሉም በደስታ መኖር እንደሚችሉ የተገለጸው ሐሳብ አስደስቶኛል። ይህም ለተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ስሜት የሚያድርባቸው ሰዎችም አምላክን ለማስደሰት እስከፈለጉ ድረስ የእሱን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ጠብቀው መኖር እንደሚችሉ ያሳያል። ከዚህ ዓይነቱ ስሜት ጋር እየታገልን የምንኖር ሰዎችን የሚያበረታታ ሐሳብ ስላወጣችሁ አመሰግናችኋለሁ።

ስም አልተጠቀሰም፣ ዩናይትድ ስቴትስ