በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ግብረ ሰዶማዊነት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ?

ግብረ ሰዶማዊነት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ?

ግብረ ሰዶማዊነት በብዙ አገሮች ውስጥ ተቀባይነት ማግኘቱን እንደቀጠለ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ አንድ ቡድን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት የሚናገረው ሐሳብ “ዘመናችን ከደረሰበት የእውቀት ብርሃን አንፃር” በአዲስ መልክ እንዲተረጎም ጥሪ በማቅረብ ላይ ነው። በተጨማሪም በቅርቡ ከወንድ ጋር ጋብቻ የፈጸመ በብራዚል የሚኖር አንድ ፓስተር የእሱ ቤተ ክርስቲያን የምታራምደውን ዘመናዊ አመለካከት የሚያስተናግድ እንዲሆን “መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መልክ መታየቱ አስፈላጊ” መሆኑን ተናግሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነትን የማይደግፉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የግብረ ሰዶማውያን ጠላት እንደሆኑ ወይም ለግለሰቦቹ ጭፍን ጥላቻ እንዳላቸው ተደርገው ይታያሉ። ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን በጭፍን መጥላትን አይደግፍም። ይሁን እንጂ ግብረ ሰዶም መፈጸምን አስመልክቶ የሚናገረው ሐሳብ ምንም የማያሻማ ነው።

“ከሴት ጋር እንደሚደረገው ሁሉ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ይህ አስጸያፊ ነው።”​ዘሌዋውያን 18:22

በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተካተቱት መመሪያዎች አንዱ የሆነው ይህ ትእዛዝ ለእስራኤል ብሔር ብቻ ከተሰጡት በርካታ የሥነ ምግባር ደንቦች መካከል አንዱ ነው። ያም ሆኖ፣ “አስጸያፊ ነው” የሚለው አባባል ግብረ ሰዶም የሚፈጽመው ግለሰብ አይሁዳዊ ሆነም አልሆነ አምላክ ለግብረ ሰዶም ያለውን አመለካከት የሚገልጽ ነው። በእስራኤል ዙሪያ የነበሩት ብሔራት ግብረ ሰዶማዊነትን፣ በቅርብ የሥጋ ዘመዶች መካከል የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነትንና ምንዝርን ጨምሮ ሌሎች በሕጉ የተከለከሉ ተግባሮችን ይፈጽሙ ነበር። በመሆኑም አምላክ እነዚህን ብሔራት ርኩስ እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 18:24, 25) መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ የሚናገረው ሐሳብ በክርስትና ዘመን ላይ ተለውጦ ይሆን? እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን ጥቅስ ተመልከት፦

“አምላክ አሳፋሪ ለሆነ የፆታ ፍላጎት አሳልፎ የሰጣቸው በዚህ ምክንያት ነው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሯዊ የሆነውን ግንኙነት ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ግንኙነት ለወጡ፤ ወንዶቹም ቢሆኑ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከሴቶች ጋር መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው ኃይለኛ በሆነ የፆታ ስሜት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር አስነዋሪ ነገር ፈጸሙ።”​ሮም 1:26, 27

መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነትን ከተፈጥሮ ውጪ ወይም አስነዋሪ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ፈጣሪያችን መጀመሪያ ካሰበው ውጪ በሆነ መንገድ የፆታ ግንኙነት መፈጸምን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። ግብረ ሰዶም በመፈጸም ዘር ማፍራት አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን፣ አጋንንት ተብለው የተጠሩት ዓመፀኛ መላእክት በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ በፊት ከሴቶች ጋር ከፈጸሙት የፆታ ግንኙነት ጋር ያመሳስለዋል። (ዘፍጥረት 6:4፤ 19:4, 5፤ ይሁዳ 6, 7) አምላክ በመላእክትና በሰዎች መካከልም ሆነ በተመሳሳይ ፆታዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት ከተፈጥሮ ውጭ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል።

ግብረ ሰዶማዊነት ተገቢ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ?

አንዳንዶች የሚከተለው ጥያቄ ወደ አእምሯቸው ይመጣ ይሆናል፦ ‘አንድ ሰው በአፈጣጠሩ፣ በአካባቢ ተጽዕኖ ወይም በሕይወቱ ውስጥ ባጋጠሙት መጥፎ ነገሮች (ለምሳሌ በፆታ በመነወሩ) የተነሳ ግብረ ሰዶማዊ ቢሆን ተገቢ አይሆንም? በፍጹም፣ እነዚህ ምክንያቶች ድርጊቱ ተቀባይነት እንዲኖረው አያደርጉም። እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን ምሳሌ ተመልከት፦ አንድ ሰው አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት በዘር ውርስ የተነሳ ከልክ በላይ የመጠጣት ዝንባሌ ይኖረው ይሆናል፤ አሊያም የአልኮል መጠጥ ያለልክ በሚጠጣበት ቤተሰብ ውስጥ አድጎ ይሆናል። ብዙ ሰዎች እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኝ ሰው ሊያዝኑለት እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ከመጠን በላይ የመጠጣት ዝንባሌን ስለወረሰ ወይም ከልክ በላይ በሚጠጣበት ቤተሰብ ውስጥ ስላደገ ብቻ በዚህ አመሉ እንዲገፋበት ወይም ከዚህ ልማዱ ለመላቀቅ የሚያደርገውን ትግል እንዲያቆም የሚያበረታታው ሰው እንደማይኖር ሳይታለም የተፈታ ነው።

በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ ከግብረ ሰዶማዊነት ምኞት ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ሰዎችን አያወግዝም፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ያለ ስሜት ያደረባቸው በተፈጥሮም ይሁን በሌላ ምክንያት፣ ለዚህ ዝንባሌ ተሸንፈው ግብረ ሰዶማዊ መሆናቸውን በፍጹም አይደግፍም። (ሮም 7:21-25፤ 1 ቆሮንቶስ 9:27) ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማውያን ከዚህ ልማዳቸው ለመላቀቅ የሚያደርጉትን ትግል ማሸነፍ እንዲችሉ ለመርዳት ጠቃሚ ምክሮችንና ማበረታቻዎችን ይሰጣል።

ከግብረ ሰዶማውያን ጋር በተያያዘ የአምላክ ፈቃድ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶም መፈጸምን ቢያወግዝም ግብረ ሰዶማዊ የሆኑ ሰዎችን እንድንጠላ አያበረታታም።

አምላክ ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ ያለውን አቋም በፍጹም ማለሳለስ አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ በግልጽ እንደሚናገረው ‘የአምላክን መንግሥት ከማይወርሱ’ ሰዎች መካከል “ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ” ግለሰቦችም ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ቁጥር 11 የሚከተለውን የሚያጽናና ሐሳብ ይዟል፦ “አንዳንዶቻችሁም እንደነዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችሁ ተጠርታችኋል።”

ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ፣ አምላክን እሱ ባወጣው መሥፈርት መሠረት ለማምለክ ከልብ የሚፈልጉ ሰዎችን ሁሉ በደስታ ተቀብሏቸው ነበር። በዛሬው ጊዜም ቢሆን የክርስቲያን ጉባኤ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በአዲስ መልክ በመተርጎም ሳይሆን ሕይወታቸውን መጽሐፉ ከሚናገረው ጋር በማስማማት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚሹ ልበ ቅኖችን ሁሉ በደስታ ይቀበላቸዋል።

ይህን አስተውለኸዋል?

● መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን ይላል?​—ሮም 1:26, 27

● መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶም የመፈጸም ስሜት ያላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርገን እንድንመለከት ያበረታታል?​—1 ጢሞቴዎስ 2:4

● ከግብረ ሰዶማዊነት መላቀቅ ይቻላል?​—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ለግብረ ሰዶማዊነት ያለው አመለካከት በተለየ መንገድ ሊተረጎም ይገባል?