በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልታነሳቸው የሚገቡ አራት ጥያቄዎች

ልታነሳቸው የሚገቡ አራት ጥያቄዎች

ልታነሳቸው የሚገቡ አራት ጥያቄዎች

እንደማንኛውም የኢንተርኔት አገልግሎት ሁሉ ማኅበራዊ ድረ ገጽም የራሱ የሆነ አደጋ አለው። * ይህን በአእምሮህ በመያዝ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች እንድታስብባቸው እንጋብዝሃለን።

1 ማኅበራዊ ድረ ገጾች የግል ሕይወቴን የሚነኩት እንዴት ነው?

“ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።”​ምሳሌ 10:19

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ ጥንቃቄ ካላደረግህ ስለ ራስህ የምታሰፍረው መረጃ፣ ፎቶግራፎችህ፣ በጓደኛ ዝርዝርህ ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዲመለከቱት ድረ ገጽህ ላይ በየጊዜው የምታሰፍረው አጭር ሐሳብ እንዲሁም ሌሎች ላሰፈሩት ሐሳብ የምትሰጠው ምላሽ ስለ አንተ በጣም ብዙ መረጃ ሊያስተላልፍ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ከእነዚህ መረጃዎች በመነሳት የመኖሪያ አድራሻህን፣ ቤት መሆንህን ወይም አለመሆንህን፣ የምትሠራበትን ቦታ ወይም ትምህርት ቤትህን ማወቅ ይችላል። በድረ ገጽህ ላይ አድራሻህ የሚገኝ ከሆነና “ነገ ሽርሽር እንሄዳለን!” እንደሚለው ያሉ አጭር ሐሳቦችን ካሰፈርክ ቤትህን ለመዝረፍ የሚረዳ በቂ መረጃ ለሌቦች ሰጠህ ማለት ነው።

የኢ-ሜይል አድራሻህን፣ የተወለድክበትን ቀን ወይም የስልክ ቁጥርህን የመሳሰሉ ዝርዝር መረጃዎችን ድረ ገጽህ ላይ ማስፈርህም ለጥቃት ሊያጋልጥህ ይችላል፤ ወይም ሌሎች በአንተ ስም ተጠቅመው የማጭበርበር ድርጊቶች ሊፈጽሙ ይችላሉ። ይሁንና ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለ አደጋ ሊከተል እንደሚችል ሳያስቡ ዝርዝር መረጃዎችን በድረ ገጾቻቸው ላይ ያሰፍራሉ።

ሰዎች ድረ ገጻቸው ላይ አንድ መረጃ ማስፈራቸው መረጃውን አደባባይ ላይ ከመለጠፍ ተለይቶ እንደማይታይ አያስተውሉም። ድረ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩትን ሐሳብ “ጓደኞቻቸው ብቻ” እንዲያዩት ቢያደርጉም እንኳ ጓደኛ የተባሉት ሰዎች በዚህ መረጃ የፈለጉትን ሊያደርጉ ይችላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የተቀመጠ ማንኛውም መረጃ አደባባይ ላይ እንደተሰቀለ ወይም በቀላሉ አደባባይ ሊወጣ እንደሚችል ተደርጎ መታየት አለበት።

ማድረግ የምትችለው ነገር፦ በምትጠቀምበት ድረ ገጽ ላይ የግል መረጃዎችህን ሁሉም ሰው እንዳያየው ማድረግ የምትችልበትን መንገድ (ፕራይቬሲ ሴቲንግ) በደንብ ለማወቅና በሚገባ ለመጠቀም ጥረት አድርግ። በየጊዜው የምታሰፍራቸውን ሐሳቦች ወይም ፎቶግራፎችህን የምታውቃቸውና የምትተማመንባቸው ሰዎች ብቻ እንዲያዩ አድርግ።

እንደዚህም አድርገህ ቢሆን ድረ ገጽህ ላይ ያስቀመጥከው መረጃ አንተ ካሰብከው ውጪ ለብዙ ሰዎች ሊዳረስ እንደሚችል አትዘንጋ። በድረ ገጽህ ላይ ያሰፈርከውን ሐሳብ በየጊዜው በመመርመር አታላዮች አንተን ለማግኘት ወይም በአንተ ስም ተጠቅመው ለማጭበርበር ሊጠቀሙበት የሚችሉ መረጃ አለመኖሩን አረጋግጥ። በጓደኛ ዝርዝርህ ውስጥ ላሉ ሰዎችም እንኳ የራስህንም ሆነ የሌሎችን ሚስጥር ከመናገር ተቆጠብ። (ምሳሌ 11:13) እንዲህ ያለውን መረጃ ለማስተላለፍ በሌላ የመገናኛ ዘዴ መጠቀም ትችላለህ። ካምረን የተባለች አንዲት ወጣት “በስልክ መጠቀም ስሜትን ይበልጥ ለመግለጽ የሚያስችል ከመሆኑም ሌላ ሚስጥርህን ለመጠበቅ ይረዳል” ብላለች።

ዋናው ነጥብ፦ ኪም የተባለች ሴት የተናገረችው ሐሳብ ነጥቡን ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል፦ “በማኅበራዊ ድረ ገጾች ስትጠቀም ጥንቃቄ የምታደርግ ከሆነ ሰዎች ስለ ግል ሕይወትህ አያውቁም። ማኅበራዊ ድረ ገጽ ለአደጋ የሚያጋልጥህ ጥንቃቄ ሳታደርግ ከቀረህ ነው።”

2 ማኅበራዊ ድረ ገጾች ጊዜዬን ይሻሙብኝ ይሆን?

“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”​—ፊልጵስዩስ 1:10

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ በማኅበራዊ ድረ ገጾች መጠቀም ጊዜህን ሊሻማብህና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ትኩረት እንዳትሰጥ ሊያደርግህ ይችላል። ኬ የተባለች አንዲት ሴት “በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ከበርካታ ሰዎች ጋር የምትገናኝ ከሆነ ብዙ ጊዜ የምታጠፋ ከመሆኑም ሌላ ሱስ ሊሆንብህ ይችላል” ብላለች። በዚህ ወጥመድ ተይዘው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የሰጧቸውን ሐሳቦች እንመልከት፦

“ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀምህን ማቆም ብትፈልግ እንኳ እንዲህ ማድረግ ከባድ ነው። ሱስ ይሆንብሃል ማለት ይቻላል።”​—ኢሊዝ

“በጓደኞችህ ድረ ገጽ ላይ ያሉትን ሐሳቦች መመልከቱ እንዳለ ሆኖ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ ጨዋታዎችን፣ አእምሮን የሚያሠሩ ጥያቄዎችን እንዲሁም የዘፋኞችንና የአድናቂዎቻቸውን ድረ ገጾች ታገኛለህ።”​—ብሌን

“ከባድ ሱስ ይሆንብሃል፤ በጣም ተመስጠህ ረጅም ሰዓት ማጥፋትህን የምትገነዘበው እናትህ መጥታ ዕቃዎቹን ለምን እንዳላጠብክ ስትጠይቅህ ነው።”​—አናሊስ

“በድረ ገጼ ላይ ለጻፍኳቸው ነገሮች ማን መልስ እንደሰጠ ለማወቅ ስለምጓጓ በተቻለ ፍጥነት ከትምህርት ቤት እመለሳለሁ። ከዚያም ለእነዚያ ሁሉ ሰዎች መልስ እሰጣለሁ፤ እንዲሁም በድረ ገጻቸው ላይ ያስቀመጧቸውን አዳዲስ ፎቶግራፎች እመለከታለሁ። ኢንተርኔት በምጠቀምበት ጊዜ ጠባዬ ሁሉ ይለዋወጣል፤ ሲያቋርጡኝ ብስጭትጭት እላለሁ። ከማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የማይጠፉ አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች አሉ፤ ሌላው ቀርቶ ሰው ቤት ተጋብዘው ሲሄዱ ወይም ሌሊት ላይ እንኳ እነዚህን ድረ ገጾች ይከፍታሉ!”​ሜገን

ማድረግ የምትችለው ነገር፦ ጊዜ ልታባክነው የማይገባ ሀብት ነው። ታዲያ ለገንዘብ እንደምታደርገው ሁሉ በጊዜ አጠቃቀምህ ረገድም ለምን ባጀት አታወጣም? በመጀመሪያ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ምን ያህል ጊዜ ብታሳልፍ ተገቢ እንደሚሆን ጻፍ። ከዚያም ለአንድ ወር ያህል ጊዜህን እንዴት እንደተጠቀምክበት በመመልከት ውሳኔህን ምን ያህል እንዳከበርክ ገምግም። አስፈላጊ ከሆነ ማስተካከያ አድርግ።

ወላጅ ከሆንክና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችህ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ረጅም ጊዜ የሚያጠፉ ከሆነ ይህን የሚያደርጉበትን ምክንያት ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ናንሲ ዊላርድ ሳይበር ሴፍ ኪድስ፣ ሳይበር ሳቪ ቲንስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደተናገሩት ልጆች ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ረጅም ጊዜ ማጥፋታቸው ጭንቀትና ውጥረት እንዳለባቸው እንዲሁም ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። እኚህ ሴት “በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ሌሎች ስለ እነሱ ያላቸው አመለካከት በጣም ያሳስባቸዋል” በማለት ጽፈዋል። “ወጣቶች በእኩዮቻቸው ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላቸው የሚለኩት ከጓደኞቻቸው ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት በሚያደርጉት የሐሳብ ልውውጥ መጠን ከሆነ ይህ ሱስ ሊሆንባቸው ይችላል።”

ማኅበራዊ ድረ ገጾችም ሆኑ ማንኛውም ዓይነት ድረ ገጽ ከቤተሰብህ አባላት ጋር ሊኖርህ በሚገባው ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ፈጽሞ አትፍቀድ። ዶን ታፕስኮት፣ ግሮውን አፕ ዲጂታል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የሚገርመው ነገር ኢንተርኔት በአካል የተራራቁ የቤተሰብ አባላትን የሚያቀራርብ ቢሆንም በአንድ ጣሪያ ሥር ያሉትን ግን ሊያራርቃቸው ይችላል።”

ዋናው ነጥብ፦ ኤመሊ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ማኅበራዊ ድረ ገጽ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት የሚያስችል ጥሩ ዘዴ ይመስለኛል። ይሁንና እንደማንኛውም ነገር ሁሉ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም የምታሳልፈውን ጊዜም ገደብ ልታበጅለት ይገባል።”

3 ማኅበራዊ ድረ ገጾች በሌሎች ዘንድ ባለኝ ስም ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

“መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል፤ መከበርም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።”​ምሳሌ 22:1

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የምታሰፍረው ሐሳብ ሰዎች ስለ አንተ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን ይህን ማስተካከልም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 20:11፤ ማቴዎስ 7:17) ብዙዎች እንዲህ ያለውን አደጋ ያስተዋሉት አይመስልም። ራኬል የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች በሚጠቀሙበት ጊዜ የማመዛዘን ችሎታቸውን የሚያጡ ይመስላል። ሌላ ጊዜ ቢሆን የማይሉትን ነገር በድረ ገጻቸው ላይ ያሰፍራሉ። አንዳንዶች ተገቢ ያልሆነ አንድ ሐሳብ ማስፈራቸው ብቻ ስማቸውን ሊያጎድፍ እንደሚችል አይገነዘቡም።”

በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በምታሰፍረው ነገር ምክንያት ስምህ መጉደፉ በወደፊት ሕይወትህም ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ግሮውን አፕ ዲጂታል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ነገር ምክንያት ከሥራ የተባረሩ ወይም ሌላ ሥራ መቀጠር ያልቻሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ የሚገልጹ ታሪኮችን መስማት የተለመደ ነው።”

ማድረግ የምትችለው ነገር፦ ድረ ገጽህን ከፍተህ እዚያ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ በሌሎች ዓይን ለማየት ሞክር። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በሌሎች ዘንድ መታወቅ የምፈልገው በዚህ መንገድ ነው? አንድ ሰው በድረ ገጼ ላይ ያስቀመጥኳቸውን ፎቶግራፎች ከተመለከተ በኋላ ስለ እኔ ምን ዓይነት አመለካከት ይኖረዋል? ሌሎችን ማሽኮርመም እንደምወድ፣ ለፆታ ብልግና የሚጋብዝ አለባበስ እንዳለኝ እንዲሁም ያለ ጭፈራ ሌላ ሥራ እንደሌለኝ ይሰማዋል? ከሆነ ሥራ ባመለክትና ቀጣሪዬ ድረ ገጼን ቢመለከት ስለ እኔ እንዲህ ዓይነት ግምት እንዲኖረው እፈልጋለሁ? እነዚህ ፎቶግራፎች የምመራበትን የሥነ ምግባር አቋም በትክክል ይገልጻሉ?’

ወጣት ከሆንክ ደግሞ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ወላጆቼ፣ አስተማሪዎቼ ወይም ሌሎች የማከብራቸው ሰዎች ድረ ገጼን ቢመለከቱትስ? እዚያ ላይ የሚያዩትና የሚያነቡት ነገር ያሳፍረኛል?’

ዋናው ነጥብ፦ በሌሎች ዘንድ የሚኖርህን ስም በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” በማለት የጻፈውን ሐሳብ አስታውስ።​—ገላትያ 6:7

4 ማኅበራዊ ድረ ገጾች በጓደኛ ምርጫዬ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

“ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”​ምሳሌ 13:20

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ ጓደኞችህ በአስተሳሰብህና በድርጊትህ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በመሆኑም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ጓደኛ የምታደርጋቸውን ሰዎች በተመለከተ መራጭ መሆንህ የተገባ ነው። አንዳንዶች እምብዛም ወይም ጨርሶ ከማያውቋቸው ሰዎች የሚላኩላቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የጓደኝነት ግብዣዎች ይቀበላሉ። ሌሎች ደግሞ በጓደኛ ዝርዝራቸው ላይ ካሉት ሰዎች መካከል ጥሩ ጓደኞች ያልሆኑ እንዳሉ ከጊዜ በኋላ ተገንዝበዋል። እስቲ አንዳንዶቹ ምን እንዳሉ እንመልከት፦

“አንድ ሰው እገሌ ከገሌ ሳይል ሁሉም ሰው የላከለትን የጓደኝነት ግብዣ የሚቀበል ከሆነ ውሎ አድሮ ችግር ውስጥ መግባቱ አይቀርም።”​—አናሊስ

“ብዙ የማውቃቸው ሰዎች፣ በጓደኛ ዝርዝራቸው ውስጥ ሊያስገቧቸው የማይፈልጓቸውን ሰዎች እንኳ ጓደኛ አድርገው ይቀበላሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የግለሰቡን ስሜት መጉዳት ስለማይፈልጉ እንደሆነ ይናገራሉ።”​—ሊአን

“በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት ጓደኝነት መመሥረት በአካል ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት ተለይቶ የሚታይ አይደለም። በጓደኛ ምርጫህ ረገድ ጠንቃቃ መሆን አለብህ።”​—አሌክሲስ

ማድረግ የምትችለው ነገር፦ ጓደኞችህን የምትመርጥበት መሥፈርት አውጣ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በጓደኛ ምርጫቸው ረገድ ገደብ አበጅተዋል፦

“ጓደኛ አድርጌ የምቀበለው እንዲያው በሩቅ የማውቃቸውን ሰዎች ሳይሆን ማንነታቸውን በደንብ የማውቃቸውን ሰዎች ብቻ ነው።”​—ጂን

“በጓደኛ ዝርዝሬ ውስጥ የማስገባው ለረጅም ጊዜ የማውቃቸውን ሰዎች ብቻ ነው። የማላውቃቸውን ሰዎች ፈጽሞ ጓደኛ አድርጌ አልቀበላቸውም።”​—ሞኒክ

“ጓደኛ አድርጌ የምቀበለው በደንብ የማውቃቸውንና ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው።”​—ሬ

“የማላውቀው ሰው ጓደኛው እንድሆን ቢጋብዘኝ ግብዣውን አልቀበልም። አቋሜ ይህ ነው። በጓደኛ ዝርዝሬ ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ በደንብ የማውቃቸውና በገሃዱ ዓለም ጓደኞቼ የሆኑ ግለሰቦች ናቸው።”​—መሪ

“ጓደኛዬ አድርጌ የተቀበልኩት ሰው ተገቢ ያልሆኑ ፎቶግራፎችን ወይም ሐሳቦችን በድረ ገጹ ላይ ቢያስቀምጥ ይህን ሰው ከጓደኛ ዝርዝሬ ላይ ለመሰረዝ ዓይኔን አላሽም። ሌሎች ያስቀመጡትን ነገር መመልከቱ በራሱ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ከመቀራረብ ተለይቶ አይታይም።”​—ኪም

“ማኅበራዊ ድረ ገጽ በነበረኝ ጊዜ መረጃዎቼን እንዲያዩ የምፈቅደው በጣም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነበር። የጓደኞቼ ጓደኞች የሆኑ ሰዎች የጻፍኳቸውን ሐሳቦችም ሆነ ፎቶግራፎቼን እንዲያዩ አልፈቅድም፤ ይህን ማድረግ የሚችሉት ጓደኞቼ ብቻ ነበሩ። እንዲህ የማደርገው የጓደኞቼ ጓደኞች ለእኔ ጥሩ ወዳጆች መሆናቸውን እርግጠኛ ስላልሆንኩ ነው። ማንነታቸውንም ሆነ ምን ዓይነት ስም እንዳላቸው አላውቅም።”​—ሄዘር

ዋናው ነጥብ፦ ዶክተር ግዌን ሹርገን ኦኪፍ፣ ሳይበርሴፍ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ከሁሉ የተሻለው መርሕ ከምታውቃቸውና በገሃዱ ዓለም ጓደኛህ ከሆኑ ሰዎች ውጪ ማንንም በጓደኛ ዝርዝርህ ውስጥ አለማስገባት ነው” ብለዋል። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ንቁ! የትኛውንም ዓይነት ማኅበራዊ ድረ ገጽ ለይቶ በመጥቀስ አይደግፍም አሊያም አያወግዝም። ክርስቲያኖች የኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንደማይቃረን ማረጋገጥ አለባቸው።​—1 ጢሞቴዎስ 1:5, 19

^ አን.42 ስለ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የንቁ! መጽሔትን የሐምሌ 2011 እትም ከገጽ 24-27 እና የነሐሴ 2011 እትም ከገጽ 10-13 ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዘግተህ ውጣ!

የምትጠቀምበትን ድረ ገጽ በአግባቡ ዘግተህ የማትወጣ ከሆነ ሌሎች በአንተ ድረ ገጽ ላይ የፈለጉትን ነገር ማስፈር ይችላሉ። ሮበርት ዊልሰን የተባሉት የሕግ ባለሞያ እንደተናገሩት ድረ ገጽህን ሳትዘጋ መውጣት “የገንዘብ ቦርሳህን ወይም ሞባይል ስልክህን በሕዝብ መዝናኛ ቦታ ትቶ የመሄድ ያህል ነው። ማንኛውም ሰው ድረ ገጽህ ላይ ሐሳቡን ማስፈር ይችላል።” እኚህ ሰው ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ “ዘግተህ መውጣትህን አትርሳ” የሚል ምክር ሰጥተዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ራስህን ለችግር እያጋለጥክ ይሆን?

ኮንሲዩመር ሪፖርትስ ያካሄደው ጥናት እንዳሳየው በማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚጠቀሙ በርካታ ሰዎች “ለዝርፊያና ለጥቃት እንዲሁም በስማቸው ለሚፈጸም የማጭበርበር ድርጊት ሊያጋልጣቸው የሚችል ነገር ያደርጋሉ። አሥራ አምስት በመቶ የሚሆኑት አድራሻቸውን ወይም የጉዞ እቅዳቸውን፣ 34 በመቶ የሚሆኑት የትውልድ ቀናቸውን እንዲሁም ልጆች ካሏቸው ሰዎች መካከል 21 በመቶ የሚሆኑት የልጆቻቸውን ስምና ፎቶግራፍ በድረ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።”