በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቴክኖሎጂ መገናኘት!

በቴክኖሎጂ መገናኘት!

በቴክኖሎጂ መገናኘት!

● እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሳም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ጋር እኩል ስለማይሄድ ሰዎች ኋላቀር እንደሆነ በመግለጽ ይቀልዱበት ነበር። ሳም ከቤተሰቡና ከወዳጆቹ ጋር ለመገናኘት በሚያስችለው ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ለበርካታ ዓመታት ፈቃደኛ አልነበረም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙትን የሳም ልጆች ጨምሮ ሁሉም ሰው በአዲሱ ቴክኖሎጂ መጠቀም ይፈልጋል። ሳም 16 ዓመት ለሆናት ልጁ “ሰዎች በአካል ተገናኝተው ይጫወቱ የነበረበት ዘመን ይናፍቀኛል” ይላት ነበር።

ከጊዜ በኋላ ግን ሳም አቋሙን መልሶ ማጤን ጀመረ። አንዳንድ ሰዎችን ሳያያቸውም ሆነ ሳያናግራቸው ዓመታት አልፈዋል። በሥራ ከመወጠራቸው የተነሳ ከእሱ ጋር የተራራቁ የቤተሰቡ አባላት ትዝ አሉት። ሳም ‘ከእነዚህ ሁሉ ሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ጨርሶ እንዳይቋረጥ በአዲሱ ቴክኖሎጂ መጠቀም ሳይኖርብኝ አይቀርም’ ብሎ አሰበ። ሰዎች እንደ ኋላቀር የሚያዩት ሳም በመጨረሻ ስልክ ለማስገባት ወሰነ። ይህ የሆነው በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ሲሆን ጊዜው የ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ነበር።

እስቲ ይህን ሁኔታ በአእምሯችን ይዘን ወደ 2012 እንምጣ። የሳም የልጅ ልጅ የሆነው ናታን፣ ወደ ሌላ አገር ከሄዱት ሮቤርቶ እና አንጀላ የተባሉ የቅርብ ጓደኞቹ ጋር በስልክ እያወራ ነው። ናታን ስልኩን ከዘጋ በኋላ ጓደኞቹ ከሄዱ አሥር ዓመት እንዳለፈ ሲያስታውስ ‘አቤት፣ ጊዜው እንዴት ይነጉዳል!’ ብሎ አሰበ።

ቀደም ባሉት ዓመታት ናታን፣ ሩቅ ወደ ሆነ አካባቢ ከተዛወሩ የቤተሰቡ አባላትና ጓደኞቹ ጋር አልፎ አልፎ በስልክ መገናኘት መቻሉ በራሱ ያስደስተው ነበር። አሁን አሁን ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙትን የናታንን ልጆች ጨምሮ ሁሉም ሰው ከሌሎች ጋር ለመገናኘት ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ይጠቀማል።

ናታን ግን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ጋር እኩል ስለማይሄድ ሰዎች ኋላቀር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። እሱ ደግሞ “ከሰዎች ጋር በስልክ በማውራት ድምፃቸውን መስማት እችል የነበረበት ዘመን ይናፍቀኛል” ይላል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን አቋሙን እንደገና ማጤን ጀምሯል። ናታን ‘ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት እንዳይቋረጥ በአዲሱ ቴክኖሎጂ መጠቀም ሳይኖርብኝ አይቀርም’ የሚል ስሜት አለው።

አንተስ እንደ ናታን ተሰምቶህ ያውቃል? ሰዎች በተፈጥሯቸው ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ያስደስታቸዋል። (ዘፍጥረት 2:18፤ ምሳሌ 17:17) በዛሬው ጊዜ ደግሞ ብዙዎች ይህን ለማድረግ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተጠቀሙ ነው፤ ታዲያ አንተስ ስለዚህ ቴክኖሎጂ ማወቅ የሚኖርብህ ነገር ምንድን ነው?