በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቢትል ነት ማኘክ ምን ጉዳት አለው?

ቢትል ነት ማኘክ ምን ጉዳት አለው?

ቢትል ነት ማኘክ ምን ጉዳት አለው?

በደቡብ እስያ በሚገኝ አንድ አገር በጎዳና ላይ እየተጓዝክ ነው እንበል፤ መንገድ ላይ ያገኘኸው ሰው ሲያይህ ፈገግ ይላል። በዚህ ጊዜ ጥቀርሻ የመሰሉት ጥርሶቹ ይታዩሃል፤ አፉ ደም በሚመስል ምራቅ ተሞልቷል። ሰውየው ምራቁን ጢቅ ሲል መሬቱ ላይ የሚታየው ደም የመሰለ ነገር ደግሞ ይበልጥ ይዘገንንሃል። ሰውየው ቢትል ነት እያኘከ ነው።

በምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም ከፓኪስታንና ሕንድ አንስቶ በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ የሚገኙ አገራትን አካትቶ እስከ ፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ማይክሮኔዥያ በሚል የወል መጠሪያ እስከሚታወቁት ደሴቶች ድረስ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቢትል ነት ይጠቀማሉ፤ ይህም ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 10 በመቶ ገደማ የሚሆነው ማለት ነው። የቢትል ነት ነጋዴዎች አንዳንድ ጊዜ ልጆቻቸውንም ይዘው በገበያ ቦታዎችና በየጎዳናዎች ላይ ጠረጴዛቸውን ዘርግተው ሲቸረችሩ ይታያሉ። ሌሎች ሻጮች ደግሞ ደንበኞችን ለመሳብ የሚያብረቀርቁ መብራቶችንና “የቢትል ነት ቆነጃጅት” እያሉ የሚጠሯቸውን የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ ልብስ የለበሱ ሴቶች ይጠቀማሉ።

በመላው ዓለም የቢትል ነት ንግድ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ ያስገኛል። ይሁን እንጂ ቢትል ነት ምንድን ነው? ይህን ያህል ብዙ ሰዎች የሚያኝኩትስ ለምንድን ነው? ይህ ልማድ በጤና ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ልማድ ምን ይላል? ከዚህ ሱስ መላቀቅ የሚቻለውስ እንዴት ነው?

ቢትል ነት ምንድን ነው?

በተለምዶ ቢትል ነት ተብሎ የሚጠራው ነገር በፓስፊክ ደሴቶችና በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ የሚገኘው አሪካ ፓልም የሚባለው ዘንባባ መሰል ዛፍ ፍሬ ነው። ቢትል የሚለው ስም የመጣው ከዚህ ፍሬ ጋር ምንም ዓይነት ተዛማጅነት ከሌለው ቢትል ፔፐር ከተባለው ተክል ነው። ቢትል ነትን የሚያኝኩ ሰዎች ከአሪካ ዛፍ ፍሬ ላይ ትንሽ ቆርጠው በቢትል ፔፐር ቅጠል ከጠቀለሉት በኋላ ካልሲየም ሃይድሮክሳይድ የተባለውን ማዕድን ይጨምሩበታል። ይህ ማዕድን የሚያነቃቁ ንጥረ ነገሮች ከፍሬው እንዲወጡ ያደርጋል። ቢትል ነት የሚያኝኩ አንዳንድ ሰዎች የተሻለ ጣዕም እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ ቅመሞች፣ ትንባሆ ወይም ማጣፈጫዎች ይጨምሩበታል።

በዚህ መንገድ የተዘጋጀውን ቢትል ነት የሚያኝኩ ሰዎች አፋቸው ደም በሚመስል ምራቅ ይሞላል። በመሆኑም አሁንም አሁንም ምራቃቸውን ይተፋሉ፤ ሌላው ቀርቶ እየተንቀሳቀሰ ባለ መኪና ውስጥ ሆነው እንኳ ምራቃቸውን ስለሚተፉ ይብላኝ ለእግረኞች ያስብላል!

በራስ ላይ መከራ ማምጣት!

ኦራል ሄልዝ የተባለው መጽሔት ያቀረበው ሪፖርት እንደሚገልጸው “የአሪካ ፍሬ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በማኅበራዊ፣ በባሕላዊና ሌላው ቀርቶ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ ትልቅ ሚና ነበረው።” “ተጠቃሚዎቹ ምንም ጉዳት እንደሌለው የሚያስቡ ሲሆን ጥሩ ስሜት እንደሚፈጥርላቸውና ከፍተኛ ደስታና ሞቅታ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ። . . . ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን [ቢትል ነት] በጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል።” እንዴት?

የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣናት በቢትል ነት ውስጥ ከሚገኙት ንጥረ ነገሮች አንዱ ሱስ የሚያስይዝ እንደሆነ ያምናሉ። እንዲያውም አንዳንድ ተጠቃሚዎች በቀን ውስጥ እስከ 50 የሚደርሱ ቢትል ነቶችን ያኝካሉ! እነዚህ ሰዎች ብዙም ሳይቆይ ጥርሳቸው የሚበልዝ ሲሆን ለድድ በሽታም ይጋለጣሉ። ኦራል ሄልዝ እንደሚለው ከሆነ አዘውትረው ቢትል ነትን የሚያኝኩ ሰዎች የአፋቸው ውስጠኛ ክፍል የተጨማደደና የቀይ ቡኒ ቀለም ያለው ይሆናል። በተጨማሪም ቢተል ነት ማኘክ ኦራል ሰብሚውከስ ፋይብሮሲስ የሚባል የአፍ ውስጠኛ ክፍል ቀስ በቀስ እየተበላ እንዲሄድና እንዲቆስል የሚያደርግ ሥር የሰደደ በሽታ ሊያስከትል እንደሚችል ኦራል ሄልዝ ገልጿል።

ከዚህም ሌላ ቢትል ነት ማላመጥ ኦራል ስኩዌመስ ሴል ካርስኖማ ለሚባለው የአፍ ካንሰር መንስኤ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ካንሰር በጉሮሮ ላይም ሊከሰት ይችላል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዋቂዎች በአፍ ካንሰር የሚጠቁ መሆኑ ይህንኑ የሚያሳይ ነው። በታይዋን አካባቢ 85 በመቶ ገደማ የሚሆኑት የአፍ ካንሰር በሽተኞች ቢትል ነት የሚያላምጡ ሰዎች ናቸው። ከዚህም በላይ ዘ ቻይና ፖስት እንደሚለው “በታይዋን በዋነኝነት ለሰዎች ሞት መንስኤ ከሚሆኑት 10 ነገሮች መካከል የሚመደበው የአፍ ካንሰር ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በአራት እጥፍ ጨምሯል።”

በሌሎች አካባቢዎችም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ፓፑዋ ኒው ጊኒ ፖስት-ኩርየር እንዲህ ይላል፦ “የፓፑዋ ኒው ጊኒ ተወዳጅ ዕፅ የሆነው ቢትል ነት በየዓመቱ ቢያንስ ለ2,000 ሰዎች ሞት ምክንያት ከመሆኑም በላይ ብዙ የጤና ችግሮችን እንደሚያስከትል የፓፑዋ ኒው ጊኒ የሕክምና ማኅበር አስታውቋል።” አንድ ሐኪም በጽሑፋቸው ላይ እንደገለጹት “ቢትል ነትን ለረጅም ጊዜ መጠቀም የማጨስን ያህል የተለያዩ ችግሮች ያስከትላል።” ከዚህም ሌላ በልብና በደም ዝውውር ሥርዓት ላይ የሚደርሱ እክሎችን ያመጣል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ልማድ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ አይደለም፤ ቢትል ነትን ስለማኘክም የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ንጹሕ፣ ጤናማና የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚረዱንን በርካታ መመሪያዎች ይዟል። በሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ እስቲ ቆም ብለህ አስብ።

“የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ . . . ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት በማሳየት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) “ሰውነታችሁን . . . ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]።” (ሮም 12:1) አንድ ሰው ቢትል ነት በማኘክ ሰውነቱን እየበከለ በአምላክ ዓይን ቅዱስ ወይም ንጹሕ ሊሆን ይችላል?

‘ሕይወት ያገኘነው በአምላክ ነው።’ (የሐዋርያት ሥራ 17:28) “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው።” (ያዕቆብ 1:17) ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ውድ ስጦታ ነው። ታዲያ ለበሽታ ሊዳርገው በሚችል ሱስ የተጠመደ ሰው ለዚህ ስጦታ አድናቆት እንዳለው እያሳየ ነው ማለት ይቻላል?

“ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም።” (ማቴዎስ 6:24) “ለምንም ነገር ተገዢ መሆን አልሻም።” (1 ቆሮንቶስ 6:12) አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ሰው ንጹሕ ላልሆነ ልማድ ባሪያ መሆን ወይም ይህ ልማድ ሕይወቱን እንዲቆጣጠረው መፍቀድ ይኖርበታል?

“ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማርቆስ 12:31) “ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም።” (ሮም 13:10) በእግረኛ መተላለፊያዎች ወይም በሌሎች ቦታዎች ላይ ደም የመሰለ ምራቅ በመትፋት ለማየት የሚያስጠላና ንጽሕና የጎደለው ድርጊት የምንፈጽም ከሆነ ለሌሎች እውነተኛ ፍቅር እያሳየን ነው ሊባል ይችላል?

ይዋል ይደር እንጂ ‘የዘራነውን መልሰን ማጨዳችን’ አይቀርም። (ገላትያ 6:7, 8) ይህ መሠረታዊ የሆነ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ስለሆነም መጥፎ ልማድ ከዘራን መጥፎ የሆነ ነገር እናጭዳለን። አምላክ ለእኛ ባሰበው መንገድ የምንኖር ከሆን ግን ጥሩ ልማዶች የምናዳብር ሲሆን የተሻለ ጤንነት ብቻ ሳይሆን እውነተኛና ዘላቂ ደስታም እናገኛለን። ይሁንና ቢትል ነት የማላመጥ ሱስ ይኖርብህ ይሆናል፤ ታዲያ በአምላክ ዓይን ጥሩ የሆነውን በማድረግ የተሻለ ብሎም ይበልጥ የሚያረካ ሕይወት መምራት የምትፈልግ ከሆነ ከዚህ ሱስ እንዴት መላቀቅ ትችላለህ? ከዚህ በታች የቀረቡትን ውጤታማ የሆኑ ሦስት እርምጃዎች ለምን አትሞክራቸውም?

ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሚረዱ ሦስት እርምጃዎች

1. ተነሳሽነት ይኑርህ። አንድን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ ከፈለግህ በጤንነትህ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ከማወቅ ባለፈ ይህን ልማድ ለማስወገድ ከፍተኛ ተነሳሽነት ሊኖርህ ይገባል። ቢትል ነት ማላመጥ፣ ትንባሆ ማጨስ ወይም ዕፅ መወሰድ በጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ቢያውቁም ይህን ማድረጋቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ይበልጥ እንድትነሳሳ መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር ስለ ፈጣሪህና ለአንተ ስላለው ጥልቅ ፍቅር ለምን አትማርም? ዕብራውያን 4:12 “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” ይላል።

2. አምላክ እንዲረዳህ ጠይቀው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ የሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።” (ሉቃስ 11:9, 10) እውነተኛው አምላክ ይሖዋ፣ እርዳታና ብርታት እንዲሰጥህ የምታቀርበውን ልባዊ ጸሎት ሰምቶ ዝም አይልም። አንደኛ ዮሐንስ 4:8 “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የአምላክ ፍቅር ከቀመሱ ሰዎች አንዱ ነበር። “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” ሲል ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:13

3. የሌሎችን እርዳታና ድጋፍ ጠይቅ። አብረውህ የሚሆኑት ሰዎች በአንተ ላይ በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ምሳሌ 13:20 “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” ይላል። ስለዚህ ጓደኞችህን በጥንቃቄ ምረጥ! በይሖዋ ምሥክሮች መካከል በአንድ ወቅት ቢትል ነት ሲጠቀሙ የነበሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አብረው መሆናቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው መጥፎ ልማዳቸውን ለማሸነፍ የሚያስችል ብርታት ሰጥቷቸዋል።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ከዚህ መጥፎ ልማድ ተላቅቀዋል

ንቁ! በአንድ ወቅት ቢትል ነት የማላመጥ ልማድ ከነበራቸውና አሁን ግን ከሱሱ ሙሉ በሙሉ ከተላቀቁ አምስት ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። እስቲ የሚናገሩትን እንስማ፦

ቢትል ነት ማኘክ የጀመራችሁት እንዴት ነው?

ፖሊን፦ ወላጆቼ ቢትል ነት ማኘክ ያስለመዱኝ ገና ሕፃን ሳለሁ ነው። በፓፑዋ ኒው ጊኒ ደሴት በሚገኘው በምኖርበት መንደር እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነበር።

ቤቲ፦ ገና የሁለት ዓመት ሕፃን ሳለሁ አባቴ ቢትል ነት ይሰጠኝ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለሁ በጣም ብዙ ቢትል ነት ስለምይዝ የቢትል ነት ዛፍ የሆንኩ ይመስል ነበር! በጣም ከባድ ሱስ ስለነበረብኝ ጠዋት እንደተነሳሁ የመጀመሪያ ሥራዬ ቢትል ነት ማኘክ ነበር።

ዌን-ጁንግ፦ ቢትል ነት ማኘክ የጀመርኩት በ16 ዓመቴ ነው። ይህን ማድረግ አሪፍ እንደ መሆንና የማደግ ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር፤ በተጨማሪም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ፈልጌ ነበር።

ጂዬል-ሊያን፦ የምተዳደረው ቢትል ነት በመሸጥ ነበር። ንግዴ የተሳካ እንዲሆን የምሸጠው ሸቀጥ ከፍተኛ ጥራት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለብኝ ተሰማኝ፤ ስለዚህም መቅመስ ጀመርኩ። ከዚያም ቀስ በቀስ ሱሰኛ ሆንኩ።

ሱሱ በጤንነታችሁ ላይ ምን ጉዳት አስከትሏል?

ጂዬል-ሊያን፦ አፌ፣ ከንፈሬና ጥርሶቼ ደም ይመስሉ ነበር። በዚያ ጊዜ የተነሳሁትን ፎቶግራፍ ማየት ያሳፍረኛል። አሁንም ቢሆን የከንፈር ቁስለት ያሠቃየኛል።

ፖሊን፦ አፌ ይቆስል እንዲሁም የማቅለሽለሽ ስሜትና ተቅማጥ ያስቸግረኝ ነበር።

ቤቲ፦ ክብደቴ 35 ኪሎ ግራም ነበር፤ ከዕድሜዬና ከቁመቴ አንጻር ይህ በጣም ዝቅተኛ ነው። ከዚህም ሌላ ጥርሴ ስለሚያስቀይም ብዙ ጊዜ በሽቦ እየፈገፈግሁ አጸዳው ነበር።

ሳም፦ የድድ ሕመምና ተቅማጥ ያስቸግረኝ ነበር። አሁን የቀረኝ አንድ ጥርስ ብቻ ነው! ጥርሴን በሽቦ እየፈገፈግሁ ማጽዳቴ ያን ያህል የጠቀመኝ አይመስለኝም።

ይህን ልማድ የተዋችሁት ለምንድን ነው?

ፖሊን፦ አምላክ ‘ሥጋን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እንድናነጻ’ እንደሚፈልግ የሚናገረውን በ⁠2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አነበብኩ። በመሆኑም ፈጣሪዬን ለማስደሰት የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ወሰንኩ።

ሳም፦ የይሖዋ አምላክ መንፈስ በሕይወቴ ውስጥ እንዲሠራ ፈለግሁ፤ ስለዚህም ቢትል ነት እንዳኝክ የሚገፋፋኝን ስሜት መቋቋም እንድችል እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። እሱም ጸሎቴን መለሰልኝ። አሁን ቢትል ነት ከተጠቀምኩ 30 ዓመት ገደማ ሆኖኛል።

ጂዬል-ሊያን፦ መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ “እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ” የሚል ሐሳብ አገኘሁ። (ያዕቆብ 4:8) ይህ ጥቅስ በጥልቅ ነካኝ። ቢትል ነት ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት እያወቅሁ ይህን ዕፅ መጠቀሜና መሸጤ ተገቢ ነው? አካልንም ሆነ መንፈስን ከሚያረክሰው ከዚህ ልማድ ‘እጆቼን ለማንጻት’ ወዲያውኑ ወሰንኩ።

ከዚህ ልማድ በመላቀቃችሁ ምን ጥቅሞች አግኝታችኋል?

ዌን-ጁንግ፦ ቢትል ነት ማላመጥ የጀመርኩት በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስል ነበር። አሁን ግን ከጓደኞቼ ጋር ከነበረኝ የሚበልጥ ወዳጅነት መመሥረት ይኸውም የይሖዋ እንዲሁም የመንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ወዳጅ መሆን ችያለሁ።

ሳም፦ አሁን በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ በጣም ጤነኛ ነኝ። በተጨማሪም ገንዘቤን በመጥፎ ልማዶች ላይ ስለማላባክን ቤተሰቤን በተሻለ ሁኔታ ማስተዳደር ችያለሁ።

ፖሊን፦ ነፃና ንጹሕ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ጥርሶቼ ነጭና ጠንካራ ናቸው። ቤቴና ጓሮዬም ቢሆን ከቢትል ነት ልጣጮችና አስቀያሚ ከሆኑ ቀይ ምልክቶች ጸድተዋል።

ቤቲ፦ ንጹሕ ሕሊናና በጣም የተሻለ ጤንነት አለኝ። እንዲያውም የትምህርት ቤት አስተማሪና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ማገልገል ችያለሁ።

[ሥዕሎች]

ቤቲ

ፖሊን

ዌን-ጁንግ

ጂዬል-ሊያን

ሳም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቢትል ነትን አዘውትሮ ማኘክ ከባድ የጤና እክሎች ሊያስከትል ይችላል

የበለዘ ጥርስና የድድ በሽታ

ኦራል ሰብሚውከስ ፋይብሮሲስ

ኦራል ስኩዌመስ ሴል ካርስኖማ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቢትል ፔፐር ቅጠል የተጠቀለሉ የቢትል ፍሬዎች