በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተወዳጅ የሆኑት ለምንድን ነው?

ተወዳጅ የሆኑት ለምንድን ነው?

ተወዳጅ የሆኑት ለምንድን ነው?

ከታች ከተዘረዘሩት መካከል ባለፈው ወር በየትኞቹ የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቅመሃል?

በአካል ተገናኝቶ መነጋገር

ደብዳቤ መጻፍ ወይም ካርድ መላክ

ስልክ

ኢ-ሜይል

የሞባይል የጽሑፍ መልዕክት

በቪዲዮ እየተያዩ ቻት ማድረግ

ቻት

ማኅበራዊ ድረ ገጾች

የአሁኑን ዘመን ያህል በርካታ የመገናኛ ዘዴዎች ኖረው አያውቁም፤ እያንዳንዱ ዘዴ ደግሞ የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በአካል ተገናኝቶ መነጋገር

ጠንካራ ጎን፦ በግለሰቡ ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት፣ የድምፁን ቃና እንዲሁም አካላዊ መግለጫዎቹን ለማስተዋል ያስችላል።

ደካማ ጎን፦ ሁለቱም ግለሰቦች በአካል መገናኘት ይጠበቅባቸዋል።

ደብዳቤ መጻፍ ወይም ካርድ መላክ

ጠንካራ ጎን፦ ፍቅርንና አሳቢነትን ለመግለጽ ያስችላል።

ደካማ ጎን፦ መልእክቱ እስኪጻፍ ብቻ ሳይሆን ግለሰቡ እጅ እስኪደርስ ድረስ ጊዜ ይወስዳል።

ኢ-ሜይል

ጠንካራ ጎን፦ በፍጥነት የሚጻፍ ከመሆኑም ሌላ ተቀባዩ ጋ ቶሎ ይደርሳል።

ደካማ ጎን፦ ብዙውን ጊዜ የጸሐፊውን ስሜት ጥሩ አድርጎ አይገልጽም፤ ወይም ደግሞ ተቀባዩ መልእክቱን በተሳሳተ መንገድ ሊረዳው ይችላል።

ሌላው አማራጭ ደግሞ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ነው፤ አንዳንዶች ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ይህ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ይገኛሉ፤ ከእነዚህ መካከል በጣም ተወዳጅ የሆነው ፌስቡክ ሲሆን ከ800 ሚሊዮን የሚበልጡ አባላት አሉት! ታይም መጽሔት እንደተናገረው “ፌስቡክ አገር ቢሆን ኖሮ ከቻይናና ከሕንድ ቀጥሎ በሕዝብ ብዛት ሦስተኛ ይሆን ነበር።” ይሁንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ምንድን ናቸው? ይህን ያህል ተወዳጅ የሆኑትስ ለምንድን ነው?

ማኅበራዊ ድረ ገጽ፣ ከምትፈልጋቸው ሰዎች ጋር የመረጃ ልውውጥ ማድረግ የምትችልበት ድረ ገጽ ነው። የ21 ዓመቷ ጂን “ከሰዎች ጋር ለመገናኘት የሚያስችል ግሩም ዘዴ ነው” ብላለች። “ማኅበራዊ ድረ ገጾች፣ በጉዞ ወይም በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የተነሳችኋቸውን ፎቶግራፎች በቀላሉ ለሌሎች ለማሳየትም ያስችላሉ።”

ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ደብዳቤ መጻፍ አይሻልም? አንዳንዶች ‘ደብዳቤ መጻፍማ ጊዜ ይወስዳል’ ይላሉ፤ በተጨማሪም ፎቶግራፎችን አሳጥቦ መላክ ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ስልክ መደወልስ? ይህም ቢሆን ብዙ ጊዜ ይወስዳል፤ ደግሞም በስልክ በአንድ ጊዜ ማነጋገር የምትችለው አንድ ሰው ብቻ ከመሆኑም ሌላ አንተ በፈለግኸው ጊዜ ሰዎቹ ቤት ላይኖሩ ወይም ከአንተ ጋር ለማውራት ላይመቻቸው ይችላል። ኢ-ሜይል መላክስ? የ20 ዓመቷ ዳንዬል “አሁን አሁን ሰዎች ለኢ-ሜይል መልስ መስጠት አቁመዋል፤ መልስ ቢሰጡ እንኳ ሳምንታት ቆይተው ነው” ስትል ቅሬታዋን ገልጻለች፤ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ግን ስለማደርጋቸው ነገሮች የሚገልጽ ሐሳብ አሰፍራለሁ፤ ጓደኞቼም ስለ ውሏቸው ይጽፋሉ። ልክ ድረ ገጻችንን ስንከፍት አንዳችን ስለሌላው ማወቅ እንችላለን። ቀላል ዘዴ ነው!”

ይህ ሲባል ግን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚሰፍረው ነገር ሁሉ ዝም ብሎ ፍሬ ከርስኪ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ መጋቢት 11 ቀን 2011 በጃፓን የተወሰኑ አካባቢዎችን ያወደመውን የመሬት መናወጥና ሱናሚ የመሳሰሉ አደጋዎች ሲከሰቱ ብዙዎች የወዳጅ ዘመዶቻቸውን ደኅንነት ለማወቅ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ይጠቀማሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ቤንጃሚን ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ ብሏል፦ “ጃፓን በሱናሚ በተመታች ጊዜ የስልክ መስመሮች ተቋርጠው ነበር። አንድ የማውቀው ሰው፣ በቶኪዮ ለምትኖር አንዲት ወዳጃችን ኢ-ሜይል ቢልክላትም መልስ እንዳላገኘ ነገረኝ። በዚህ ጊዜ በሞባይል ስልኬ አማካኝነት ኢንተርኔት ከፍቼ ወደ ድረ ገጿ ገባሁ። ወዳጃችን ደህና እንደሆነችና ወደፊት ዝርዝር ጉዳዮችን እንደምትጽፍ የሚገልጽ አጭር ሐሳብ ድረ ገጿ ላይ አስቀምጣ ነበር።”

ቤንጃሚን ቀጥሎ እንዲህ ብሏል፦ “ይህችን ሴት ለሚያውቋትና ማኅበራዊ ድረ ገጽ ለማይጠቀሙ ጓደኞቻችን ግን በግለሰብ ደረጃ ኢ-ሜይል መላክ ነበረብኝ። የእያንዳንዳቸውን አድራሻ ማግኘትና ለእነሱ መጻፍ ጊዜ ወስዶብኛል። ብዙዎቹ መልስ የሰጡኝ ከቀናት በኋላ ነበር። እንዲያውም አንድ ሰው መልስ የሰጠኝ ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ነበር! እነዚያ ሰዎች ከተለያየ ሰው በጣም ብዙ መልእክት ስለሚደርሳቸው ለሁሉም መልስ መስጠት ከብዷቸው ነበር። በማኅበራዊ ድረ ገጽ ቢጠቀሙ ኖሮ ግን ብዙ ጊዜ መቆጠብ ይቻል ነበር። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሁሉም ሰው ምን እየተከናወነ እንዳለ ማወቅ ይችል ነበር!”

በእርግጥም ማኅበራዊ ድረ ገጾች ጥቅም እንዳላቸው ማንም ሊክድ አይችልም። ይሁንና የሚያስከትሉት አደጋስ ይኖር ይሆን? ከሆነ አደጋው ምንድን ነው? አንተስ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የሚሠራው እንዴት ነው?

1. የምትፈልገውን ሐሳብ በየጊዜው ድረ ገጽህ ላይ ታስቀምጣለህ።

2. በጓደኛ ዝርዝርህ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ የራሳቸውን ድረ ገጽ ሲከፍቱ አንተ ያሰፈርከውን ሐሳብ መመልከት ይችላሉ፤ አንተም የራስህን ድረ ገጽ ስትከፍት የእነሱን ሐሳብ መመልከት ትችላለህ።