በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አረብኛ የምሁራን ቋንቋ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

አረብኛ የምሁራን ቋንቋ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

አረብኛ የምሁራን ቋንቋ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

ለበርካታ ዘመናት ምሁራን የሚጠቀሙበት ዋነኛ ቋንቋ አረብኛ ነበር። ከስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች የነበሩ አረብኛ ተናጋሪ ምሁራን ከቶሌሚና ከአርስቶትል ዘመን አንስቶ የተጻፉ የሳይንስና የፍልስፍና ጽሑፎችን ተርጉመዋል እንዲሁም አርመዋል። በዚህ መንገድ አረብኛ ተናጋሪ የሆኑ ምሁራን የጥንት ተመራማሪዎች ያዘጋጇቸው ጽሑፎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ከማድረጋቸውም በላይ ሥራዎቻቸውን አዳብረዋቸዋል።

የተለያዩ ሐሳቦች መናኸሪያ

ሰባተኛውና ስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በመካከለኛው ምሥራቅ ሁለት አዳዲስ ሥርወ መንግሥታት የተነሱበት ዘመን ሲሆን እነሱም በመጀመሪያ የኡማያድ ቀጥሎ ደግሞ የአባሲድ ሥርወ መንግሥታት ነበሩ። በትንሿ እስያ፣ በአረቢያ፣ በኢራቅ፣ በግብፅ፣ በፋርስና በፓለስቲና የነበሩት ተገዢዎቻቸው የግሪክና የሕንድ ሥልጣኔ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው አዳዲሶቹ መሪዎች የዳበረ የእውቀት ክምችት ማግኘት ችለው ነበር። አባሲዶች መዲናቸውን በባግዳድ ያደረጉ ሲሆን ከተማዋ የተለያዩ ሐሳቦች መናኸሪያ ሆነች። በዚያም አረቦች ከሕንዶች፣ ከበርበሮች፣ ከቱርኮች፣ ከቻይናውያን፣ ከአርመኖች፣ ከአይሁዶች፣ ከኮፕት ሕዝቦች፣ ከግሪኮች፣ ከፋርሶች እንዲሁም አሁን አሙ ዳርያ እየተባለ ከሚጠራው ከኦክሰስ ወንዝ በስተምሥራቅ ርቀው ከሚኖሩት የሶግዲየን ሕዝቦች ጋር ተቀላቀሉ። እነዚህ ሕዝቦች በአንድነት ሆነው ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት ያካሂዱና ይከራከሩ ስለነበር ከተለያዩ ባሕሎች የመጣውን ምሁራዊ አስተሳሰባቸውን ሊወራረሱና ሊያሳድጉ ችለዋል።

መቀመጫቸውን በባግዳድ ያደረጉት የአባሲድ ገዢዎች፣ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የመጡ ተሰጥኦ ያላቸው ተመራማሪዎችን በግዛታቸው ውስጥ በትምህርት ዘርፍ ለሚኖረው እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያበረታቱ ነበር። በሒሳብ፣ በሕክምና፣ በሙዚቃ፣ በአልክሚ (የመካከለኛው ዘመን ኬሚስትሪ)፣ በጂኦሜትሪ፣ በፊዚክስና በፍልስፍና መስክ የተጻፉትን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተዘጋጁ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን ለመሰብሰብና ወደ አረብኛ ለመተርጎም የታሰበበት ጥረት ይደረግ ነበር።

ከ754 እስከ 775 ዓ.ም. ድረስ የገዛው አል ማንሱር የተባለው ከሊፋ በግሪክኛ የተዘጋጁ የሒሳብ መጻሕፍትን እንዲያመጡለት አምባሳደሮችን ወደ ባይዛንታይን ቤተ መንግሥት ልኮ ነበር። አል ማሙን (ከ813 እስከ 833 ዓ.ም.) የተባለው ከሊፋ ደግሞ የከሊፋ አል ማንሱርን ምሳሌ በመከተል የግሪክኛ ጽሑፎችን ወደ አረብኛ የመተርጎሙ ሥራ እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ይህ እንቅስቃሴ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቆይቷል። በመሆኑም በአሥረኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በዘመኑ የነበሩት በግሪክኛ የተዘጋጁ የፍልስፍናና የሳይንስ መጻሕፍት በሙሉ ማለት ይቻላል ወደ አረብኛ ተተርጉመው ነበር። ይሁን እንጂ አረብኛ ተናጋሪ የሆኑ ምሁራን ከመተርጎም ያለፈ ሥራ አከናውነዋል። ከግሪክኛ በተተረጎሙት ሥራዎች ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦም አበርክተዋል።

የአረቦች አስተዋጽኦ

ብዙ የአረብኛ ተርጓሚዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በጥራትና በሚያስደንቅ ፍጥነት ነበር። በመሆኑም አንዳንድ የታሪክ ምሁራን፣ እነዚያ ተርጓሚዎች የሚተረጉሙትን ርዕሰ ጉዳይ በደንብ የሚያውቁ እንደነበሩ ይናገራሉ። ከዚህም በላይ በርካታ ምሁራን ወደ አረብኛ የተተረጎሙትን ጽሑፎች ተንተርሰው የራሳቸውን ምርምር አድርገዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ ሁናይን ኢብን ኢሻቅ የሚባለው (ከ808 እስከ 873 ዓ.ም.) ሶሪያዊ ክርስቲያን የሆነ ሐኪምና ተርጓሚ ስለ ዓይን ይበልጥ ለመረዳት የሚያግዝ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ስለ ዓይን አቀማመጥ የሚያሳይ ትክክለኛ ሥዕል ያካተተው ሥራው በአረቡ ዓለምም ሆነ በአውሮፓ ከዓይን ጋር ለተያያዙ ጥናቶች ማመሳከሪያ ጽሑፍ ሆኖ አገልግሏል። በምዕራቡ ዓለም አቨሴና በመባል የሚታወቀው ፈላስፋና ሐኪም የነበረው ኢብን ሲናም (980 እስከ 1037 ዓ.ም.) እንዲሁ በርካታ መጻሕፍትን የጻፈ ሲሆን ሥራዎቹም ሥነ ምግባርንና ፍልስፍናን እንዲሁም ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ። ካኖን ኦፍ ሜዲሲን የተሰኘው እሱ ያዘጋጀው ትልቅ ጥራዝ፣ ጌለን እና አርስቶትል የተባሉትን ታዋቂ የግሪክ ምሁራን ሐሳቦች ጨምሮ በዚያን ጊዜ የነበረውን የሕክምና እውቀት መሠረት ያደረገ ነበር። ይህ ጥራዝ 400 ለሚያህሉ ዓመታት የሕክምና መማሪያ መጽሐፍ ሆኖ አገልግሏል።

የአረብ ተመራማሪዎች ለሳይንሳዊ እድገት መነሻ የሆነውን በሳይንሳዊ ቤተ ሙከራ የመጠቀም ዘዴ ይሠሩበት ነበር። ይህም የምድርን መጠነ ዙሪያ እንደገና ለማስላትና በቶለሚ ጽሑፍ ላይ የቀረበውን ጂኦግራፊያዊ መረጃ ለማረም አስችሏቸዋል። ፖል ሉንዴ የተባሉት የታሪክ ምሁር “የአርስቶትልን ሥራ እንኳ አርመዋል” በማለት ተናግረዋል።

በአረቡ ዓለም በትምህርት ረገድ የታየው እድገት ጠቃሚ በሆኑ በርካታ መስኮች ላይ የተንጸባረቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የውኃ ማከማቻዎችን፣ የውኃ መውረጃ ቦዮችንና በውኃ ኃይል የሚሠሩ መሣሪያዎችን መገንባት ይገኙበታል፤ ከሠሯቸው ነገሮች መካከል የተወሰኑት ዛሬም ድረስ ይገኛሉ። በእርሻ፣ በዕፅዋት ጥናት እንዲሁም በሰብል ምርትና አፈር አያያዝ ጥናት ላይ አዳዲስ ጽሑፎች መዘጋጀታቸው ገበሬዎች ለተወሰነ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ ዘሮችን መምረጥ እንዲችሉና በዚህም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ረድቷቸዋል።

በ805 ዓ.ም. ከሊፋ ሐሩን አር ራሺድ ሰፊ በሆነው ግዛቱ ውስጥ የመጀመሪያውን ሆስፒታል አቋቋመ። ብዙም ሳይቆይ በግዛቱ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ትልቅ ከተማ አንድ ሆስፒታል እንዲኖረው አደረገ።

አዳዲስ የትምህርት ማዕከሎች

በአረቡ ዓለም የነበሩ በርካታ ከተሞች፣ ቤተ መጻሕፍትና በተለያዩ መስኮች ልዩ ሥልጠና የሚሰጥባቸው ማዕከሎች ነበሯቸው። ከሊፋ አል ማሙን፣ ቤት አል ሂክማ (“ቤተ ጥበብ” ማለት ነው) ተብሎ የሚጠራ የትርጉምና የምርምር ተቋም በባግዳድ ከፈተ። ከተቋሙ ሠራተኞች መካከል ደመወዝ የሚከፈላቸው ምሁራን ይገኙ ነበር። በካይሮ የነበረው ዋናው ቤተ መጻሕፍት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ጥራዞች እንደነበሩት ይነገራል። በዚሁ ጊዜ በኡማያድ ሥርወ መንግሥት ሥር በነበረችው በስፔን ዋና ከተማ በኮርዶባ 70 ቤተ መጻሕፍት የነበሩ ሲሆን እነዚህም ከመላው የአረብ ዓለም ምሁራንንና ተማሪዎችን መሳብ ችለው ነበር። ከሁለት መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ኮርዶባ ዋነኛ የምሁራን ማዕከል ሆና አገልግላለች።

ፋርስ ውስጥ የግሪክ ሒሳብ አሠራር ልማዶች በሕንድ ከነበሩት ጋር ተዋሕደው ነበር፤ የሕንድ የሒሳብ ሊቃውንት ዜሮ ቁጥር ጥቅም ላይ የሚውልበትን ዘዴ ፈጥረዋል። በዚህ ዘዴ መሠረት አንድ ቁጥር ይህን ያህል ነው የሚባለው የእያንዳንዱን ቁጥር አቀማመጥና በቁጥሮች መካከል ዜሮ የሚገባበትን ቦታ በመመልከት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዜሮ ቁጥርን በመጠቀም ብቻ በ11፣ በ101፣ በ1001 እና ወዘተ መካከል ያለውን ልዩነት በቀላሉ ማሳየት ይቻላል። በዚህ ዘዴ መሠረት የትኛውንም ቁጥር ከ1 እስከ 9 ያሉትን አኃዞችና ዜሮን በመጠቀም ብቻ መጻፍ ይቻላል። ፖል ሉንዴ፣ ይህ ዘዴ “ማንኛውንም ዓይነት ስሌት መሥራት ቀላል እንዲሆን ከማድረጉም በላይ አልጀብራ [የሚባለው የሒሳብ ዘርፍ] እንዲዳብር አስችሏል” በማለት ጽፈዋል። በተጨማሪም የአረብ ምሁራን በጂኦሜትሪ፣ በትሪጎኖሜትሪና አቅጣጫን በመለየት መስክ ከፍተኛ እድገት አድርገው ነበር።

አረቦች በሳይንስና በሒሳብ መስክ የላቀ ደረጃ ላይ በደረሱበት ወቅት ሌላው ዓለም ለትምህርት ያን ያህል ትኩረት አልሰጠም። በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ውስጥ በተለይም በገዳማት ውስጥ የጥንት ምሁራንን ሥራዎች ጠብቆ ለማቆየት ተመሳሳይ ጥረቶች እየተደረጉ ነበር። ይሁንና በአረቡ ዓለም ይደረግ ከነበረው እንቅስቃሴ ጋር ሲነጻጸር የተገኘው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ይሁን እንጂ በአሥረኛው መቶ ዘመን ገደማ የአረብ ምሁራን የተረጎሟቸው ሥራዎች ቀስ በቀስ ወደ ምዕራቡ ዓለም ሲገቡ ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ወደ ምዕራቡ ዓለም የሚገቡት ጽሑፎች እየተበራከቱ መምጣታቸው በአውሮፓ ለተካሄደው ሳይንሳዊ ሕዳሴ መሠረት ሆኗል።

አዎን፣ ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየው በዛሬው ጊዜ በሳይንስና በሌሎች ተዛማጅ መስኮች ላለው የእውቀት ደረጃ ሊመሰገን የሚገባው አንድ አገር ወይም ሕዝብ ብቻ አይደለም። ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩት ሕዝቦች ምርምር ያደርጉ እንዲሁም ከእነሱ በፊት በነበሩት ምሁራን ሥራዎች ላይ ጥያቄ ያነሱና ተሰጥኦ ያላቸውን ምሁራን ያበረታቱ ነበር። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት ሕዝቦች የእነዚያ ምሁራን ውለታ አለባቸው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

▪የኡማያዶች ግዛት

□የአባሲዶች ግዛት

ስፔን

ኮርዶባ

ባይዛንቲየም

ሮም

ኮንስታንቲኖፕል

ኦክሰስ ወንዝ

ፋርስ

ባግዳድ

ኢየሩሳሌም

ካይሮ

አረቢያ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁናይን ኢብን ኢሻቅ ያዘጋጀው የዓይን ሥዕል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቨሴና ባዘጋጀው “ካኖን ኦፍ ሜዲሲን” ላይ የሚገኝ ገጽ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአረብ ምሁራን በ1237 ዓ.ም. በባስራ በሚገኝ ቤተ መጻሕፍት

[የሥዕል ምንጭ]

© Scala/White Images/Art Resource, NY

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Eye diagram: © SSPL/Science Museum/Art Resource, NY; Canon of Medicine: © The Art Gallery Collection/Alamy