መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ወደ አምላክ መጸለይ የሚኖርብን እንዴት ነው?
ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ፊት ቀርበን የልባችንን አውጥተን ለእሱ መናገር መቻል እጅግ ታላቅ መብት ነው። ሆኖም ብዙ ሰዎች ምን ብለው መጸለይ እንዳለባቸው ግራ የሚገባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ የጸሎታቸውን ይዘት ማሻሻል ይፈልጋሉ። ከኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ተከታዮች መካከል አንዳንዶቹ የጸሎታቸው ይዘት አሳስቧቸው እንደነበረ በግልጽ ማየት ይቻላል። ከመካከላቸው አንዱ “ጌታ ሆይ፣ . . . እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 11:1) ኢየሱስም በምላሹ የጸሎት ናሙና ሰጣቸው፤ ይህ ጸሎት ብዙውን ጊዜ የጌታ ጸሎት ወይም አቡነ ዘበሰማያት እየተባለ ይጠራል። ቅልብጭ ያለው ይህ ጸሎት ተቀባይነት ባለው መንገድ ወደ አምላክ መቅረብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና መልእክት ለመገንዘብ ያስችለናል።
ኢየሱስ ያስተማረው የጸሎት ናሙና
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን። የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን፣ የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን። ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’”—ማቴዎስ 6:9-13
ኢየሱስ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ” በማለት መናገሩን ልብ በል። እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እሱ የተናገራቸውን ቃላት እንደ በቀቀን እንዲደግሟቸው ወይም ሸምድደው በቃላቸው እንዲወጡት አልፈለገም። እንዲያውም የጸሎት ናሙና ከመስጠቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንዲህ ዓይነቱን ልማድ አውግዞታል። (ማቴዎስ 6:7) ኢየሱስ ያስተማረው ጸሎት በራሳችን ሳይሆን በአምላክ ዓይን ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን በተመለከተ ጥሩ ትምህርት ያዘለ ነው። እነዚህ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ምን እንደሆኑ ለመረዳት ኢየሱስ ባስተማረው ጸሎት ውስጥ ያሉት ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው መገንዘብ ያስፈልገናል። እስቲ በጸሎቱ ውስጥ የተካተቱትን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምር።
የጸሎት ናሙናው ሲብራራ
“በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ።” አምላክ እንደ አንድ ሰብዓዊ አባት ስለሚወደንና ስለሚንከባከበን ኢየሱስ፣ አምላክን “አባታችን” ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው። አምላክ፣ ይሖዋ የሚባል የግል ስም ያለው ሲሆን ይህ ስም ሁሉን ቻይ፣ አምላክ እና ጌታ እንደሚሉት ከመሳሰሉ የማዕረግ ስሞቹ ጋር እኩል እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም። * (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) ይሁንና የአምላክ ስም መቀደስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ስሙ ነቀፋና ስድብ ስለደረሰበት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ለሚደርስባቸው ችግር ሁሉ አምላክን ተጠያቂ ያደርጉታል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የችግሩ መንስኤ የሰዎች ሥራ አሊያም ግለሰቦቹ በአጉል ጊዜ አጉል ቦታ መገኘታቸው ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 19:3፤ መክብብ 9:11 NW) ሌሎች ደግሞ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚያመጣው አምላክ ነው እያሉ ይወነጅሉታል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም” በማለት ይናገራል። (ያዕቆብ 1:13) በተጨማሪም ብዙ ሃይማኖቶች፣ አምላክ መጥፎ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ለዘላለም በማሠቃየት እንደሚቀጣቸው ያስተምራሉ፤ ይህ ትምህርት ፍቅር የሆነውን አምላክ እንደሚያሳዝነው ጥርጥር የለውም። (ኤርምያስ 19:5፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ሮም 6:23 እንደሚለው “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት” እንጂ ዘላለማዊ ሥቃይ አይደለም! *
“መንግሥትህ ይምጣ።” የአምላክ መንግሥት፣ በሰማይ የሚገኝ መስተዳደር ሲሆን ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ በቅርቡ መላዋን ምድር ያስተዳድራል። ዳንኤል 7:14 (የ1954 እትም) ለኢየሱስ “ግዛትና ክብር መንግሥትም” እንደተሰጠው ይናገራል። የአምላክ መንግሥት ‘ሲመጣ’ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ እርምጃ ይወስዳል፤ የእሱ ተቃዋሚ የሆኑ አገዛዞችን በሙሉ ዳግም እንዳያንሰራሩ አድርጎ ከደመሰሰ በኋላ ምድርን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል።—ዳንኤል 2:44
“ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰው ዘር ለአምላክ ፈቃድ ይገዛል። በዚህም የተነሳ እውነተኛ ሰላም የሚሰፍን ሲሆን ሁሉም ሰው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ያመልከዋል። ሰዎችን የሚከፋፍሉ የፖለቲካ ሥርዓቶችም ሆነ የሐሰት ሃይማኖት አይኖሩም። ራእይ 21:3, 4 እንደሚለው በምሳሌያዊ አገላለጽ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር” ይሆናል፤ አምላክም “እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
“የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን።” ኢየሱስ ለአምላክ ስምና መንግሥት ቅድሚያ ከሰጠ በኋላ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ቀጥሎ ጠቅሷል። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ‘ለዛሬ’ ከሚያስፈልገን አልፈን ብዙ ነገሮችን ለማግኘት ጥረት ከማድረግ መቆጠብ እንዳለብን ይጠቁማሉ። በምሳሌ 30:8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ልብ ማለት ይኖርብናል፤ ጥቅሱ “ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ፤ ብቻ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ” ይላል።
“የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን።” እዚህ ላይ ‘በደል’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ በቀጥታ ሲፈታ “ዕዳ” ማለት ነው። * ሁላችንም አምላክን የመታዘዝ ዕዳ አለብን። ስለዚህ እሱን ሳንታዘዘው በምንቀርበት ወይም በእሱ ላይ ኃጢአት በምንፈጽምበት ጊዜ ዕዳ እየተጠራቀመብን ነው ሊባል ይችላል። ይሁንና እኛ የበደሉንን በደግነት ይቅር ስንል ይሖዋም ዕዳችንን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው።—ማቴዎስ 18:21-35
“ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።” እዚህ ላይ “ክፉው” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን “ፈታኙ” ተብሎም ተጠርቷል። (ማቴዎስ 4:3) ፍጽምና የሚጎድለን ደካማ ሰዎች በመሆናችን ምክንያት ሰይጣንንና ሰብዓዊ ወኪሎቹን ለመቋቋም የአምላክ እርዳታ ያስፈልገናል።—ማርቆስ 14:38
ኢየሱስ ያስተማረው የጸሎት ናሙና፣ ቅድሚያ ልትሰጣቸው በሚገቡ ነገሮች ረገድ ማስተካከያ በማድረግ የጸሎትህን ይዘት ለማሻሻል እንዲረዳህ ምኞታችን ነው። ይሁንና ኢየሱስ ያስተማረው የጸሎት ናሙና የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና መልእክት ለመገንዘብ የሚያስችለን እንዴት ነው? ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እንደሚጠቁሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ፣ የአምላክ ስም ከመቀደሱ፣ ክፋት ሙሉ በሙሉ ከመወገዱና የአምላክ መንግሥት ለምድር ሰላማዊ አገዛዝ ከማምጣቱ ጋር የተያያዘ ነው። በእርግጥም ኢየሱስ ያስተማረው የጸሎት ናሙና በርካታ መንፈሳዊ ዕንቁዎችን የያዘ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች (በዋነኝነት ዕብራይስጥና ግሪክኛ) መለኮታዊው ስም በቅዱስ ጽሑፉ ላይ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኝ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ዘመናዊ ትርጉሞች በአምላክ ቅዱስ ስም ፈንታ በማዕረግ ስሞቹ ይጠቀማሉ።
^ አን.9 ሙታን በሌላ መልክ መኖራቸውን አይቀጥሉም፤ ከዚህ ይልቅ ‘አንቀላፍተው’ ወይም ‘ምንም የማያውቁ’ ሆነው ወደፊት ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ ይጠባበቃሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:11-13፤ መክብብ 9:5
ይህን አስተውለኸዋል?
● ኢየሱስ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?—ማቴዎስ 6:9
● አብዛኛውን ጊዜ በጸሎታችን ውስጥ በቅድሚያ መጠቀስ ያለባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?—ማቴዎስ 6:9, 10
● “ዕዳችን” የተባለው ምንድን ነው? የበደሉንን ሰዎች ይቅር ማለት የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?—ማቴዎስ 6:12 የግርጌ ማስታወሻ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ያስተማረው የጸሎት ናሙና በራስህ ሳይሆን በአምላክ ዓይን አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ እንድትሰጥ ሊረዳህ ይችላል