የከዋክብት “ክብር”
የከዋክብት “ክብር”
ጥርት ባለው ሰማይ ላይ ተረጭተው የሚታዩትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት በምሽት ስትመለከት የአድናቆት ስሜት አድሮብህ ያውቃል? ከዋክብት፣ በሚፈነጥቁት ብርሃን ድምቀት ብቻ ሳይሆን በቀለማቸውም አንዳቸው ከሌላው እንደሚለዩ አስተውለህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል እንደሚገልጸው “የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል።”—1 ቆሮንቶስ 15:41
የከዋክብት ክብር ወይም የብርሃናቸው ድምቀት የሚለያየው ለምንድን ነው? ለምሳሌ አንዳንዶቹ ከዋክብት ነጭ ሌሎቹ ሰማያዊ፣ ቢጫ ወይም ቀይ ቀለም እንዳላቸው ሆነው የሚታዩን ለምንድን ነው? ብልጭ ድርግም የሚሉ የሚመስሉትስ ለምንድን ነው?
ከዋክብት፣ በውስጣቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል የሚያመነጭ የኑክሌር ማብለያ አላቸው ማለት ይቻላል። ይህ ኃይል ወደ ኮከቡ ውጨኛ ክፍል ይሄድና በአብዛኛው በኢንፍራሬድ ጨረርና በዓይን በሚታይ ብርሃን መልክ ወደ ሕዋ ይሰራጫል። የሚገርመው ነገር በጣም ከፍተኛ ሙቀት ያላቸው ከዋክብት ሰማያዊ ሲሆኑ ቀዝቀዝ የሚሉት ደግሞ ቀይ ቀለም አላቸው። እንዲህ ያለ የቀለም ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
ብርሃንን ፎቶን የሚባሉ ቅንጣቶች ጅረት እንደሆነ አድርገን ልናስበው እንችላለን፤ እነዚህ ቅንጣቶች የኃይል ሞገድ የሚያሳየው ዓይነት ባሕርይ አላቸው። ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸው ከዋክብት ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ፎቶኖች የሚለቁ ሲሆን እነዚህ ደግሞ አጭር የሞገድ ርዝመት አላቸው፤ አጭር የሞገድ ርዝመት ያለው የብርሃን ክፍል ሰማያዊ ቀለም አለው። በአንጻሩ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚሉት ከዋክብት አነስተኛ ኃይል ያላቸውን ፎቶኖች የሚለቁ ሲሆን እነዚህ ፎቶኖች ደግሞ ቀይ ቀለም ካላቸው ሞገዶች ይመደባሉ። ለእኛ ብርሃን የምትሰጠን ኮከብ ማለትም ፀሐይ የምትፈነጥቀው ብርሃን ከአረንጓዴ እስከ ቢጫ ባለው ክልል ውስጥ ይገኛል። ታዲያ ፀሐይ አረንጓዴ ሆና የማትታየው ለምንድን ነው? በዓይን መታየት በሚችለው የብርሃን ክልል ውስጥ ባሉት የሞገድ ርዝመቶች ሁሉ ከፍተኛ ብርሃን ስለምታመነጭ ነው። በመሆኑም ፀሐይ ከሕዋ ስትታይ ነጭ ትመስላለች።
የምድር ከባቢ አየር የፀሐይን ቀለም “ይለውጠዋል”
የፀሐይ ብርሃን ወደ እኛ የሚደርሰው በከባቢ አየር በኩል አልፎ ነው፤ ይህም የፀሐይን መልክ በተወሰነ መጠን ስለሚለውጠው ፀሐይ በቀን ውስጥ በተለያየ ሰዓት የተለያየ ቀለም ያላት ትመስላለች። ለምሳሌ እኩለ ቀን ላይ ፀሐይ በአብዛኛው ደማቅ ቢጫ ሆና ትታያለች። ይሁንና ፀሐይ በምትወጣበትና በምትጠልቅበት ጊዜ ብርቱካንማ ወይም ቀይ ሆና ትታያለች። እንዲህ ያለ የቀለም ለውጥ ሊኖር የቻለው በምድር ከባቢ አየር ውስጥ በሚገኘው ተን፣ የጋዝ ሞለኪውሎች እንዲሁም በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን ቅንጣቶች ምክንያት ነው።
ከባቢ አየር በውስጡ ባሉት ነገሮች የተነሳ ወደ ምድር ከሚመጣው የፀሐይ ብርሃን ውስጥ ሰማያዊና ሐምራዊ የሆነውን ቀለም ስለሚበትነው ደመና በሌለበት ቀን ሰማዩ ውብ የሆነ ሰማያዊ ቀለም ይኖረዋል። ፀሐይ ከምትፈነጥቀው ብርሃን ውስጥ ሰማያዊውና ሐምራዊው ቀለም በዚህ መንገድ ስለሚቀነስ እኩለ ቀን ላይ ፀሐይ ቢጫ ቀለም ይኖራታል። ጀምበሯ ወደ አድማስ በምትጠጋበት ጊዜ ግን ብርሃኗ ከባቢ አየሩን በአግድሞሽ ስለሚያቋርጥ በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ረጅም ርቀት ይጓዛል፤ በዚህ ጊዜ የምድር ከባቢ አየር ሰማያዊውንና አረንጓዴውን ብርሃን ይበልጥ ይበትነዋል። ስለሆነም የምትጠልቀው ፀሐይ በጣም የምታምር ቀይ ኳስ ሆና ትታያለች።
ውብ የሆነው የምሽት ሰማይ
የዓይናችን ብርሃን የማየት ችሎታ የምሽቱን ሰማይ በምናይበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ዓይናችን ብርሃን የሚቀበለው ኮን እና ሮድ በሚባሉ ሁለት ዓይነት ብርሃን ተቀባይ ሴሎች አማካኝነት ነው። ኮን የሚባሉት ሴሎች ቀለም የመለየት ችሎታ ያላቸው ሲሆን ብርሃኑ ደብዛዛ በሚሆንበት ጊዜ ግን ሥራቸውን ያቆማሉ። ሮድ የሚባሉት ሴሎች ግን ቀለም የመለየት
ችሎታ ባይኖራቸውም በጣም አነስተኛ በሆነ ብርሃን እንኳ ለማየት ያስችሉናል። እንዲያውም እነዚህ ሴሎች በደንብ መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ አንድ ሮድ የአንድን ፎቶን ብርሃን እንኳ መለየት ይችላል! ይሁን እንጂ ሮድ የተባሉት ሴሎች ይበልጥ መለየት የሚችሉት አጭር የሞገድ ርዝመት ያላቸውን ቀለማት ሲሆን እነዚህም ወደ ሰማያዊ የብርሃን ክልል ይጠጋሉ። በዚህ ምክንያት ተመሳሳይ ድምቀት ያላቸውን ርቀው የሚገኙ ከዋክብት በዓይናችን ብቻ በምናይበት ጊዜ ሰማያዊዎቹን እንጂ ቀዮቹን ከዋክብት ማየት ሊያቅተን ይችላል። ደግነቱ ግን በዓይናችን ብቻ ከምናየው ይበልጥ ለማየት የሚረዱን መሣሪያዎች አሉ።ቴሌስኮፖችና አቅርበው የሚያሳዩ ሌሎች መነጽሮች በምሽት ሰማይ ላይ የሚታዩትን እንደ ከዋክብት፣ ጋላክሲዎች፣ ጅራታማ ኮከቦችና ኔቡላዎች (በከዋክብት መካከል የሚታዩ የአቧራ ደመናዎችና የጋዝ ሞለኪውሎች ናቸው) የመሳሰሉ ርቀው የሚገኙ የሰማይ አካላትን በተሻለ ሁኔታ ለመመልከት ያስችሉናል። እንዲያም ሆኖ የምድር ከባቢ አየር እይታችንን በተወሰነ መጠን ይገድበዋል። ሃብል የጠፈር ቴሌስኮፕ ለዚህ መፍትሔ አስገኝቷል፤ ይህ ቴሌስኮፕ በሕዋ ውስጥ ምድርን ይዞራል። ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው ይህ ቴሌስኮፕ በዓይናችን ብቻ ልናየው ከምንችለው በጣም ደብዛዛ ኮከብ አንድ አስር ቢሊዮንኛ ጊዜ የሚደበዝዙ የጠፈር አካላትን ለማየት ያስችላል! ሃብል የጠፈር ቴሌስኮፕ፣ ጋላክሲዎችንና ኔቡላዎችን ጨምሮ በጥልቁ ሕዋ ውስጥ የሚገኙ የጠፈር አካላትን የሚያሳዩ አስደናቂ ምስሎችን ለመመልከት አስችሏል።
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ከሃብል የጠፈር ቴሌስኮፕ ጋር ሊወዳደሩ እንዲያውም በአንዳንድ መንገዶች ሊበልጡት የሚችሉ አዳዲስ ቴሌስኮፖች ተሠርተዋል፤ እነዚህ ቴሌስኮፖች ሥራቸውን የሚያከናውኑት
ከምድር ሆነው ነው። እነዚህ ቴሌስኮፖች ከባቢ አየር የሚያስከትላቸውን ተጽዕኖዎች የሚያርሙ የረቀቁ ዘዴዎችን ስለሚጠቀሙ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በሃብል የጠፈር ቴሌስኮፕ ሊያዩ ከሚችሉት የተሻለ ጥራት ያለውና ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚያሳይ ምስል ማግኘት ችለዋል። ለዚህ አንድ ምሳሌ የሚሆነን በሐዋይ ደሴት በደብልዩ ኤም ኬክ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው ኬክ 1 የተባለ ቴሌስኮፕ ነው፤ ይህ ቴሌስኮፕ በዓለም ላይ ከሚገኙ በብርሃን የሚጠቀሙ እጅግ ትላልቅ ቴሌስኮፖች አንዱ ነው። የሲድኒ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ፒተር ተትሂል የተባሉ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ፣ በዚህ ቴሌስኮፕ በመጠቀም አንድ ግኝት ላይ ደርሰዋል፤ እኚህ ተመራማሪ፣ ከምድር ሲታይ በእኛ ጋላክሲ (ፍኖተ ሐሊብ) እምብርት አካባቢ የሚገኝ በሚመስለው ሳጂቴሪየስ የተባለ ሕብረ ከዋክብት ውስጥ ያሉት አንዳቸው ሌላውን የሚዞሩ ሁለት ከዋክብት የአቧራ ደመና እንደሚለቁ መገንዘብ ችለዋል።የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ጠፈርን በጥልቀት በመረመሩ መጠን ብዙ ከዋክብትና ጋላክሲዎች ያገኛሉ። ጠቅላላ ቁጥራቸው ምን ያህል ይሆናል? የሰው ልጆች ከግምት ያለፈ መልስ መስጠት አንችልም። ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ግን መገመት አያስፈልገውም። መዝሙር 147:4 ስለ አምላክ ሲናገር “የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል” ይላል።
ነቢዩ ኢሳይያስም ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል። እንዲያውም ኢሳይያስ፣ ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ገደብ የሌለው ኃይል ውጤት እንደሆነ በመግለጽ ከሳይንስ አንጻር ትክክል የሆነ አስደናቂ ሐሳብ ተናግሯል። ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።”—ኢሳይያስ 40:26
ከ2,700 ዓመታት በፊት የኖረው ኢሳይያስ አጽናፈ ዓለም፣ ገደብ የሌለው የአምላክ ኃይል ውጤት መሆኑን እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ይህንን በራሱ መርምሮ እንዳልደረሰበት ጥያቄ የለውም። ከዚህ ይልቅ ይህን ሐሳብ የጻፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመሆኑም ኢሳይያስና ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ማንኛውም የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ ወይም ቴሌስኮፕ ሊያደርግ ያልቻለውን አድርገዋል። ለከዋክብት እንዲህ ያለውን ውበትና ክብር ያጎናጸፈው ማን እንደሆነ አሳውቀዋል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከዋክብት ብልጭ ድርግም የሚሉ የሚመስሉት ለምንድን ነው?
ከዋክብት ብልጭ ድርግም የሚሉ ወይም ድምቀታቸውንና ቦታቸውን የሚለዋውጡ የሚመስሉት በምድር ከባቢ አየር ውስጥ በሚፈጠር ነውጥ ምክንያት ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት በአንድ የመዋኛ ገንዳ ወለል ላይ የተቀመጡ አነስተኛ መብራቶች አሉ እንበል። የውኃ ሞገድ በሚያልፍበት ጊዜ መብራቶቹ ምን ይሆናሉ? አዎ፣ ልክ እንደ ከዋክብቱ ብልጭ ድርግም የሚሉ ይመስላሉ። ትላልቅ መብራቶች ግን እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ አይረበሹም። ፕላኔቶች እንደነዚህ ትላልቅ መብራቶች ስለሆኑ ስናያቸው ብልጭ ድርግም የሚሉ አይመስሉም። እርግጥ ነው፣ ትልቅ መስለው የሚታዩት በመጠናቸው ከከዋክብቱ በልጠው ሳይሆን ለምድር በጣም ቅርብ በመሆናቸው ነው።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ትክክለኛ ቀለማቸው ይህ ነው?
በሃብል የጠፈር ቴሌስኮፕ አማካኝነት የተነሱ ውብና የተለያየ ቀለም ያላቸው የጋላክሲዎች፣ የኔቡላዎች እንዲሁም የከዋክብት ፎቶግራፎችን ተመልክተህ ይሆናል። ይሁንና በፎቶግራፎቹ ላይ የሚታየው ትክክለኛ ቀለማቸው ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ፎቶግራፎቹ እንዲህ ዓይነት ቀለም ሊኖራቸው የቻለው ሥነ ጥበብንና ሳይንስን በመጠቀም በድጋሚ ስለተሠሩ ነው። በሃብል ቴሌስኮፕ የሚነሱት ፎቶግራፎች ጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ያላቸው ናቸው፤ ሆኖም ፎቶግራፎቹ በሚነሱበት ጊዜ ባለሞያዎች የተለያዩ ቀለሞችን የሚያጎላ መሣሪያ ይጠቀማሉ። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችና የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂንና የተለያዩ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን የሚጠቀሙ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ የእነዚህ የሰማይ አካላት ትክክለኛ ቀለም ነው ብለው የሚያስቡትን ቀለም የሚያንጸባርቅ ምስል ያትማሉ። * በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አንዳንድ ነገሮችን ለማጉላት (ምናልባትም ለሳይንሳዊ ምርምር ሲባል) ሆነ ብለው ከትክክለኛ ቀለማቸው የተለየ መልክ የሚያሳይ ምስል ያትማሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.21 ምሽት ላይ በቴሌስኮፕ ተጠቅመን ርቀው የሚገኙ የሰማይ አካላትን በምንመለከትበት ጊዜ የምንጠቀመው ኮን የተባሉትን ሴሎች ሳይሆን ቀለም መለየት የማይችሉትን ሮድ የተባሉ ሴሎች ነው።
[ሥዕሎች]
ጥቁርና ነጭ
ቀይ
አረንጓዴ
ሰማያዊ
ሦስቱ ቀለሞች ሲዋሃዱ የሚፈጠረው ምስል
[የሥዕል ምንጭ]
J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቪ838 ሞኖሴሮቲስ የተባለው ኮከብ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስበት ኃይል የተሳሰሩ ጋላክሲዎች አርፕ 273
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
NASA, ESA, and the Hubble Heritage (STScI/AURA) -ESA/Hubble Collaboration
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
V838: NASA, ESA, and H. Bond (STScI); Arp 273: NASA, ESA, and the Hubble Heritage Team (STScI/AURA)