ንድፍ አውጪ አለው?
የወረቀት ሠሪ ተርብ በደመነፍስ የተገኘ የምሕንድስና ችሎታ
● ወረቀት ሠሪ ተርቦች የተራቀቀ የምሕንድስና ችሎታ እንዳላቸው ምሁራን ይናገራሉ። እንዲህ ማለታቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ወረቀት ሠሪ ተርቦች ስማቸው እንደሚያመለክተው ተደራራቢ ቀፏቸውን የሚሠሩትና የሚጠግኑት ራሳቸው በሚያመርቱት ልዩ ዓይነት ወረቀት ነው። * እነዚህ ነፍሳት ከግንድ፣ ከእንጨት አጥር፣ ከስልክ ምሰሶ እንዲሁም ከሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶች ላይ የዕፅዋትንና የደረቁ እንጨቶችን ጭረቶች ይሰበስባሉ። ከዚያም ሴሊውለስ በተባለው ንጥረ ነገር የዳበረውን ጭረት ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ካለውና ከሚያጣብቀው ምራቃቸው ጋር እያዋሃዱ ያላምጡታል። በዚህ መንገድ የተላቆጠው ሊጥ የሚመስል ነገር ሲደርቅ ቀላል ግን ጠንካራ የሆነ ወረቀት ያስገኛል። ከዚህም በላይ ምራቃቸው፣ ወረቀቱ ሙቀት የመሳብና የተከማቸውን ሙቀት የማስወጣት ልዩ ችሎታ እንዲኖረው ያደርጋል፤ በመሆኑም እንቁላሎቹ የሚቀመጡበት የቀፎው ክፍል በቀዝቃዛ ቀናት እንኳ ሳይቀር ተስማሚ የሙቀት መጠን ይኖረዋል።
ተርቦቹ ያመረቱትን ወረቀት ከሥር ከሥሩ ቀፏቸውን ይሠሩበታል። በዚህ መንገድ ተርቦቹ ውኃ በማያስገባ የወረቀት ዣንጥላ የተሸፈኑ፣ ስድስት ማዕዘን ያላቸውና ጥቅጥቅ ያሉ ክፍሎች ይሠራሉ፤ ቅርጻቸው ባለ ስድስት ማዕዘን መሆኑ ለጥንካሬ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ያለውን ቦታ በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል። እርጥበት አዘል በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ተርቦች ወረቀቱን ሲያመርቱ በርከት ያለ ምራቅ ይጠቀማሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ምራቃቸው ወረቀቱ ውኃ የማያስገባ እንዲሆን ስለሚረዳው ነው። ተርቦቹ ቀፏቸውን የሚያንጠለጥሉት ውኃ የማይደርስበት ቦታ ላይ ነው። መግቢያው ከታች የሆነውን ቀፏቸውን እንዲህ ባለው ቦታ ላይ ቁልቁል ያንጠለጥሉታል። የሚገርመው ደግሞ ከወረቀት ፋብሪካዎች በተቃራኒ እነዚህ ተርቦች ወረቀት ሲሠሩ አየርን፣ ውኃንና ምድርን አይበክሉም።
በእርግጥም፣ ተመራማሪዎችና የሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች የእነዚህን ተርቦች ምርት በማጥናት ቀላል፣ ጠንካራና ይበልጥ መተጣጠፍ የሚችሉ እንዲሁም በቀላሉ በስብሰው ወደ አፈር የሚመለሱ የላቀ ደረጃ ያላቸው የግንባታ ቁሳቁሶችን ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸው ምንም አያስገርምም።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከሁለት የአሸዋ ቅንጣቶች የማይበልጥ አንጎል ያላቸው ነፍሳት ስለ ወረቀትና ስለ ቀፎ አሠራር ያወቁት በራሳቸው ነው? ወይስ እነዚህ ነፍሳት የኬሚካልና የመካኒካል ምሕንድስና ጥበብ ያላቸው መሆኑ ንድፍ አውጪ እንዳላቸው የሚጠቁም ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 በርከት ያሉ የተርብ ዝርያዎች የወረቀት ቀፎ ይሠራሉ። በቀፎው ውስጥ የሚገኙት ትናንሽ ክፍሎች የእንቁላል ማስቀመጫዎች ሲሆኑ እጮቻቸው በዚያ ውስጥ ያድጋሉ።