በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰላም መፍጠር የምትችለው እንዴት ነው?

ሰላም መፍጠር የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች ሲናገር “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ይላል። (ሮም 3:23) በምድር ላይ ያሉት ከሰባት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ፍጹማን ባለመሆናቸው በግለሰቦች መካከል ግጭቶች መፈጠራቸው አይቀርም። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ሰላም መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በሚመለከት ጥሩ ምክር ይሰጣል። ፈጣሪያችን “የሰላም አምላክ” እንደሆነና ስሙም ይሖዋ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዕብራውያን 13:20፤ ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) አምላክ በምድር ባሉ ልጆቹ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ይፈልጋል። ደግሞም በዚህ ረገድ እሱ ቅድሚያውን ወስዷል። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በአምላክ ላይ በማመፃቸው ከእሱ ጋር ያላቸው ሰላማዊ ዝምድና በተበላሸ ጊዜ፣ አምላክ ከሰብዓዊ ፍጥረታቱ ጋር ለመታረቅ የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች ወዲያውኑ ወስዷል። (2 ቆሮንቶስ 5:19) አንተም ከሌሎች ጋር ሰላም ለመፍጠር ልታደርግ የምትችላቸውን ሦስት ነገሮች እስቲ እንመልከት።

በነፃ ይቅር በል

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”​—ቆላስይስ 3:13

ፈታኝ የሚያደርገው ምንድን ነው? ምናልባት ‘ቅር ለመሰኘት’ በቂ ምክንያት ስላለህ ካስቀየመህ ሰው ጋር ያለህን ግንኙነት ማቋረጥህ ተገቢ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። በተጨማሪም ያስቀየመህ ግለሰብ በቅድሚያ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ ጥፋቱን ካላወቀ ወይም በደለኛው አንተ እንደሆንክ የሚያምን ከሆነ አለመግባባቱ ሳይፈታ ሊቀር ይችላል።

ምን ብታደርግ ይሻላል? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጥህን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ግለሰቡን በነፃ ይቅር ብትለው የተሻለ ነው፤ በተለይ ደግሞ ቅሬታ የፈጠረው ጉዳይ ቀላል ከሆነ እንዲህ ማድረግህ ተገቢ ነው። አምላክ ስህተቶቻችንን የሚቆጣጠር ቢሆን ኖሮ መቼም ቢሆን በፊቱ መቆም እንደማንችል አስታውስ። (መዝሙር 130:3) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።”​—መዝሙር 103:8, 14

በተጨማሪም “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ አስታውስ። (ምሳሌ 19:11) ጥበብ ወይም ማስተዋል ነገሮችን እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ከማየት አልፈን ሰዎች አንድን ነገር የተናገሩበትን ወይም ያደረጉበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። ስለዚህ ‘የበደለኝ ግለሰብ ደክሞት፣ አሞት ወይም የሚያስጨንቅ ነገር ገጥሞት ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሰዎች አንድን ነገር ለመናገር ወይም ለማድረግ የተነሳሱበትን ምክንያት እንዲሁም ስሜታቸውንና ያሉበትን ሁኔታ ማስተዋልህ ንዴትህን ሊያበርደውና ስህተታቸውን ችላ ብለህ እንድታልፍ ሊረዳህ ይችላል።

በግልጽ ተነጋገሩበት

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ወንድምህ አንድ በደል ቢፈጽም አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን መልሰህ የራስህ ታደርገዋለህ።”​—ማቴዎስ 18:15

ፈታኝ የሚያደርገው ምንድን ነው? እንደ ፍርሃት፣ ንዴትና ኀፍረት ያሉት አሉታዊ ስሜቶች ግለሰቡን ቀርበህ በማነጋገር ችግሩን እንዳትፈታ ሊያግዱህ ይችላሉ። በተጨማሪም ደጋፊ ለማግኘት ስትል የተፈጠረውን ችግር ለሌሎች ለመናገር ልትፈተን ትችላለህ፤ ይህ ደግሞ ወሬው እንዲዛመትና አለመግባባቱ ጭራሹኑ እንዲባባስ ያደርጋል።

ምን ብታደርግ ይሻላል? የተፈጠረው ችግር ከባድ ከሆነና ችላ ብለህ ልታልፈው የማትችል እንደሆነ ከተሰማህ ከግለሰቡ ጋር በግልጽ ተነጋገርበት። ጉዳዩን ከዚህ በታች በተገለጸው መንገድ ለመፍታት ሞክር፦

(1) በአፋጣኝ፦ ጉዳዩን ዛሬ ነገ እያልክ አታዘግየው። ካዘገየኸው አለመግባባቱ ሊከርር ይችላል። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጣር፦ “መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር እርቅ ፍጠር፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”​—ማቴዎስ 5:23, 24

(2) ብቻችሁን፦ የበደለህን ግለሰብ ለማማት ብትፈተንም ይህን ከማድረግ ተቆጠብ። “ስለ ራስህ ጕዳይ ከባልንጀራህ ጋር በምትከራከርበት ጊዜ፣ የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ።”​—ምሳሌ 25:9

(3) በሰላም፦ በምትነጋገሩበት ጊዜ ‘ጥፋተኛው ማን ነው?’ የሚለው ነጥብ ላይ ትኩረት አታድርግ። ግብህ ሰላም መፍጠር እንጂ በክርክሩ መርታት አይደለም። ስለዚህ ከግለሰቡ ጋር በምትነጋገርበት ጊዜ “አንተ” ከማለት ይልቅ “እኔ” የሚለውን ቃል ለመጠቀም ጥረት አድርግ። ከግለሰቡ ጋር ስትነጋገር “አንተ አስቀይመኸኛል!” ከማለት ይልቅ “. . . ምክንያት እኔ ስሜቴ ተጎድቷል!” ማለት የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ማድረግ የሚገባንን ነገር ሲገልጽ “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ” ይላል።​—ሮም 14:19

ታጋሽ ሁን

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ [አትመልስ]። . . . ነገር ግን ‘ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው።’”​—ሮም 12:17, 20

ፈታኝ የሚያደርገው ምንድን ነው? ሰላም ለመፍጠር ያደረግኸው የመጀመሪያ ሙከራ ቢከሽፍ ጥረትህን እርግፍ አድርገህ ለመተው ልትፈተን ትችላለህ።

ምን ብታደርግ ይሻላል? ታጋሽ ሁን። የሰዎች ተፈጥሮና የብስለት ደረጃቸው የተለያየ ነው። አንዳንዶች ንዴታቸው እስኪበርድ ረዘም ያለ ጊዜ ይፈጅባቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ አምላካዊ ባሕርያትን ማሳየትን ገና እየተማሩ ነው። በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች ደግነትና ፍቅር ማሳየትህን ቀጥል። መጽሐፍ ቅዱስ “በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” ይላል።​—ሮም 12:21

ሰላም መፍጠር እንድንችል እንደ ትሕትና፣ ማስተዋል፣ ትዕግሥትና ፍቅር ያሉትን ባሕርያት ለማንጸባረቅ መጣር ያስፈልገናል። ሆኖም ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ስንል የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ አይደለም!

ይህን አስተውለኸዋል?

● አንድን ሰው በነፃ ይቅር እንድትል ምን ሊረዳህ ይችላል?​—ቆላስይስ 3:13

● ስለተፈጠረው ችግር ግለሰቡን ቀርበህ ለማነጋገር ምን ሊረዳህ ይችላል?​—ማቴዎስ 5:23, 24

● ሰላም ለመፍጠር ያደረግኸው ጥረት ቢከሽፍ ምን ማድረግ ትችላለህ?​—ሮም 12:17-21

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው።”​—ምሳሌ 19:11