በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁጡ የሆኑ ሰዎች የበዙት ለምንድን ነው?

ቁጡ የሆኑ ሰዎች የበዙት ለምንድን ነው?

ቁጡ የሆኑ ሰዎች የበዙት ለምንድን ነው?

ለቁጣ መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ውስብስብ ናቸው። የሳይንስ ሊቃውንትም እንኳ ስለ ቁጣ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ አይሸሽጉም። ይሁን እንጂ ሁላችንም “የሚያስቆጣ ነገር” ሲያጋጥመን ልንበሳጭ እንደምንችል በአእምሮ ጤንነት መስክ የተሰማሩ አብዛኞቹ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነገር ነው።

የሚያስቆጣ ነገር የሚባለው አንድን ሰው የሚያናድድ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ የምንናደደው የፍትሕ መጓደል ወይም መድልዎ ሲፈጸም ስንመለከት ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌሎች እንደናቁን ሆኖ ሲሰማን ለምሳሌ ስንሰደብ ወይም ክብራችንን ዝቅ የሚያደርግ ነገር ሲያጋጥመን ልንቆጣ እንችላለን። ሥልጣናችን ወይም መልካም ስማችን እንደተነካ ሲሰማንም በቁጣ ልንገነፍል እንችላለን።

እርግጥ ነው፣ ሰዎችን የሚያስቆጧቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው። ዕድሜና ፆታ ሌላው ቀርቶ ባሕል እንኳ ሰዎችን የሚያስቆጧቸው ነገሮች እንዲለያዩ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ሰዎች የሚያስቆጡ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድም ይለያያል። አንዳንድ ሰዎች ብዙም የማይቆጡ ሲሆን ከተቆጡም ነገሩን ቶሎ ይረሱታል፤ ሌሎች ግን በቀላሉ የሚቆጡ ከመሆናቸውም በላይ ቁጣቸው እስኪበርድ ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።

በዓለም ላይ ሊያስቆጡን የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ሰዎች ከበፊቱ የበለጠ በቀላሉ የሚቆጡ እየሆኑ መጥተዋል። ለምን? አንዱ ምክንያት በዘመናችን የተስፋፋው ለሰዎች አሳቢነት አለማሳየትና እኔ ልቅደም የሚል መንፈስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ” እንደሚሆኑ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአብዛኞቹን ሰዎች ዝንባሌ በትክክል የሚገልጹ አይደሉም?

በእርግጥም ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ማግኘት ካልቻሉ ብዙውን ጊዜ ውጤቱ ቁጣ ነው። ቁጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ችግር እንዲሆን ያደረጉ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

የወላጆች ምሳሌነት

ወላጆች፣ ልጆቻቸው በልጅነትና በጉርምስና ዕድሜያቸው በሚያዳብሩት ባሕርይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የሥነ ልቦና ተመራማሪ የሆኑት ሃሪ ሚልዝ “ሰዎች ቁጣቸውን መግለጽ የሚማሩት ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ በአካባቢያቸው ሌሎች ቁጣቸውን የሚገልጹበትን መንገድ በመኮረጅ ነው” በማለት ተናግረዋል።

አንድ ሕፃን ብስጩ ሰዎች በበዙበት አካባቢ ካደገ በሌላ አባባል ሰዎች በትንሽ በትልቁ በቁጣ ሲገነፍሉ የሚያይ ከሆነ በሕይወቱ ውስጥ ችግር ባጋጠመው ቁጥር በቁጣ ምላሽ እንዲሰጥ እየሠለጠነ ነው ሊባል ይችላል። የልጁን ሁኔታ የተበከለ ውኃ ከሚጠጣ ተክል ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ተክል ቢያድግም እድገቱ ሊቀጭጭና ምናልባትም ዘላቂ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ቁጣም እንደተበከለ ውኃ ነው፤ እንዲህ ባለ አካባቢ ያደጉ ልጆች ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ ቁጡ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።

በሕዝብ የተጨናነቁ ከተሞች

በ1800 ከዓለም ሕዝብ መካከል በከተሞች ውስጥ የሚኖረው 3 በመቶ ገደማ ነበር። በ2008 ግን ይህ ቁጥር አድጎ 50 በመቶ የደረሰ ሲሆን በ2050 ደግሞ 70 በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል። ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች በተጨናነቁ ከተሞች ውስጥ ተፋፍገው መኖር በቀጠሉ መጠን ቁጡና ብስጩ የሆኑ ሰዎች እየበዙ መሄዳቸው የማይቀር ነው። ሜክሲኮ ሲቲን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በምድር ላይ ካሉት ትልቅና እጅግ የተጨናነቁ ከተሞች አንዷ በሆነችው በዚህች ከተማ ዋነኛው የውጥረት መንስኤ የትራፊክ መጨናነቅ ነው። አንድ ጋዜጠኛ እንደዘገበው ሜክሲኮ ሲቲ 18 ሚሊዮን የሚያህል ሕዝብና ስድስት ሚሊዮን መኪኖች ያሉባት ከተማ በመሆኗ “በዓለም ላይ ካሉት ዋና ከተሞች ሁሉ ይበልጥ ውጥረት የነገሠባት ሳትሆን አትቀርም።” ይኸው ጋዜጠኛ አክሎም “ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመኖሩ ሰዎች በቁጣ የመገንፈላቸው አጋጣሚ በጣም ከፍ ያለ ነው” ብሏል።

በሕዝብ የተጨናነቁ ከተሞች በሌሎች መንገዶችም ውጥረት ያስከትላሉ፤ ከእነዚህም መካከል የአየር ብክለት፣ ከፍተኛ መጠን ያላቸውና የሚረብሹ ድምፆች መበራከት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ የባሕል ልዩነትና የወንጀል ድርጊቶች መበራከት ይገኙበታል። ውጥረት የሚያስከትሉ ነገሮች በበዙ ቁጥር ሰዎች የመበሳጨት፣ የመቆጣትና ትዕግሥት የማጣት አዝማሚያቸው እየጨመረ ይሄዳል።

ኢኮኖሚው የሚያስከትለው ውጥረት

በዓለም ላይ የሚታየው የኢኮኖሚ ውድቀት በየትኛውም ቦታ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ውጥረትና ጭንቀት አስከትሏል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) በ2010 በጋራ ያወጡት አንድ መግለጫ እንደሚያሳየው “በመላው ዓለም ከ210 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሥራ አጥ እንደሆኑ ይገመታል።” የሚያሳዝነው ነገር፣ ከሥራ ከተቀነሱት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ተቀማጭ ገንዘብ የሌላቸው ሲሆን ለሥራ አጦች የሚሰጥ እርዳታም አያገኙም።

ሥራ ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ መጨነቃቸው አይቀርም። አይ ኤል ኦ እንደገለጸው ከሥራ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ውጥረት “ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ” ሆኗል። በኦንታሪዮ፣ ካናዳ የአስተዳደር አማካሪ የሆኑት ሎርን ከርቲስ “ሰዎች ሥራቸውን እንዳያጡ የሚፈሩ ሲሆን የሚታያቸው መጥፎ መጥፎው ነገር ነው” በማለት ይናገራሉ፤ “እንዲህ ዓይነት ስጋት ስላላቸው ከአለቆቻቸው ወይም ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ሙግት መግጠም ይቀናቸዋል” በማለት አክለው ተናግረዋል።

መድልዎና የፍትሕ መጓደል

የሩጫ ውድድር ላይ እንደሆንክና የምትሮጠው እግሮችህ በሰንሰለት ታስረው እንደሆነ አድርገህ አስብ፤ ይሁንና በሰንሰለት የታሰርከው አንተ ብቻ መሆንህን ብታውቅ ምን ይሰማሃል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘራቸው ወይም በሌላ ምክንያት መድልዎ ሲደርስባቸው የሚሰማቸው ስሜት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ሰዎች ሥራ፣ ትምህርት፣ መኖሪያ ቤትና ሌሎችም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዳያገኙ መድልዎ ሲደረግባቸው ይበሳጫሉ።

ሌሎች ኢፍትሐዊ ድርጊቶችም የአንድን ሰው መንፈስ ሊደቁሱና ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ሊያስከትሉበት ይችላሉ። የሚያሳዝነው ነገር አብዛኞቻችን በሕይወታችን ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ የፍትሕ መጓደል ደርሶብን ያውቃል። ከሦስት ሺህ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም” በማለት ተናግሮ ነበር። (መክብብ 4:1) የፍትሕ መጓደል ሲስፋፋና የሚያጽናና ሲጠፋ አንድ ሰው ልቡ በቁጣ ሊሞላ ይችላል።

የመዝናኛው ዓለም

በቴሌቪዥንና በሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን የሚታየው ዓመፅ በልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ እንዳለው ለማወቅ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ጥናቶች ተደርገዋል። በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡትን ነገሮች በተመለከተ ለሰዎች መረጃ የሚሰጥ አንድ ድርጅት መሥራች የሆኑት ጄምስ ስታየር እንዲህ ይላሉ፦ “እውነት የሚመስልና ዘግናኝ የሆነ የዓመፅ ድርጊት [በመገናኛ ብዙኃን] በተደጋጋሚ የሚመለከት ትውልድ፣ ጠበኝነትን ተቀባይነት እንዳለው ነገር አድርጎ የሚያይ ከመሆኑም ሌላ የጭካኔ ድርጊት እምብዛም የማይረብሸውና የርኅራኄ ስሜት የሌለው ይሆናል።”

እርግጥ ነው፣ በቴሌቪዥን አዘውትረው የዓመፅ ድርጊቶችን የሚያዩ አብዛኞቹ ወጣቶች ሲያድጉ ጨካኝ ወንጀለኞች ይሆናሉ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በቁጣ መገንፈል ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ ተደርጎ ብዙውን ጊዜ በመዝናኛው ዓለም ስለሚቀርብ የዓመፅ ድርጊቶች የማይዘገንኑት አዲስ ትውልድ ብቅ ብሏል።

ክፉ መናፍስት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ

በዛሬው ጊዜ ሰዎች ጎጂ በሆነ መንገድ ቁጣቸውን እንዲገልጹ የሚያደርጋቸው አንድ የማይታይ ኃይል ከበስተጀርባ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ ኃይል ምንድን ነው? ገና በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ አንድ ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ መቃወም ጀመረ። ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ሰይጣን ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስሙም በዕብራይስጥ “ተቃዋሚ” ወይም “ጠላት” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፍጥረት 3:1-13) ከጊዜ በኋላም ሰይጣን ሌሎች መላእክትን አግባብቶ በዓመፁ እንዲተባበሩት አደረጋቸው።

አጋንንት ወይም ክፉ መናፍስት በመባል የሚታወቁት እነዚያ ዓመፀኛ መላእክት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በምድር አካባቢ እንዲወሰን ተደርጓል። (ራእይ 12:9, 10, 12) በተጨማሪም አጭር ጊዜ እንደቀራቸው ስለሚያውቁ “በታላቅ ቁጣ” ተሞልተዋል። እነዚህን ክፉ መናፍስት በዓይናችን ልናያቸው ባንችልም የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መመልከት እንችላለን። እንዴት?

ሰይጣንና አጋንንታዊ ጭፍሮቹ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌያችንን ተጠቅመው እንደ “ጠላትነት፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ . . . ምቀኝነት” ባሉትና እነዚህን በመሳሰሉት ነገሮች እንድንካፈል ሊፈትኑን ይሞክራሉ።​—ገላትያ 5:19-21

ስሜቱን መቆጣጠር

በእርግጥም ከላይ ያየናቸውን ችግሮች፣ ተጽዕኖዎችና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ከግምት ካስገባን ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ብስጩ የሚሆኑት ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግተንም።

እንድንበሳጭና በቁጣ እንድንገነፍል የሚገፋፋን ስሜት በጣም ኃይለኛ ሊሆን ይችላል! በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ቁጣን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከባድ ችግር እንዳለብህ የሚጠቁሙ ምልክቶች፦

▶ ዕቃ ለመግዛት ተሰልፈህ መጠበቅ ያናድድሃል።

▶ ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር ብዙ ጊዜ ትጨቃጨቃለህ።

▶ አንዳንድ ጊዜ፣ ቀን አናደውህ ስለነበሩት ነገሮች እያሰብክ ስትብሰለሰል ሌሊት እንቅልፍ ታጣለህ።

▶ ያስቀየሙህን ሰዎች ይቅር ማለት ይከብድሃል።

▶ ብዙ ጊዜ ስሜትህን መቆጣጠር ያቅትሃል።

▶ ከተቆጣህ በኋላ ብዙውን ጊዜ የኃፍረት ወይም የጸጸት ስሜት ይሰማሃል። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.36 MentalHelp.net ከተባለው ድረ ገጽ በተገኘ መረጃ ላይ የተመሠረተ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቁጣ​አንዳንድ አኃዛዊ መረጃዎች

በለንደን፣ እንግሊዝ የሚገኝ የአእምሮ ጤና ተቋም፣ ቦይሊንግ ፖይንት​ፕሮብሌም አንገር ኤንድ ዋት ዊ ካን ዱ አባውት ኢት በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ አሳትሞ ነበር። ዘገባው ውስጥ ከተካተቱት ነጥቦች መካከል ቀጥሎ የቀረቡት አኃዛዊ መረጃዎች ይገኙበታል፦

84% የሚያህሉት ሰዎች ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን በሥራ ቦታቸው ላይ ውጥረት ይሰማቸዋል።

65% የሚያህሉት የቢሮ ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ ከሌሎች ጋር ከባድ ግጭት አጋጥሟቸዋል።

45% የሚያህሉት ሠራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ ብዙ ጊዜ በጣም ይቆጣሉ።

60% ገደማ የሚሆኑት ሰዎች ከሥራ የሚቀሩት በውጥረት ምክንያት ነው።

33% የሚያህሉት ብሪታንያውያን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስለተኮራረፉ አይነጋገሩም።

64% የሚያህሉት፣ ‘አብዛኞቹ ሰዎች ከዕለት ወደ ዕለት ይበልጥ ብስጩ እየሆኑ ነው ቢባል ትስማማላችሁ?’ ለሚለው ጥያቄ ‘እስማማለሁ’ ወይም ‘በጣም እስማማለሁ’ የሚል መልስ ሰጥተዋል።

32% የሚያህሉት ቁጣውን መቆጣጠር የማይችል የቅርብ ጓደኛ ወይም የቤተሰብ አባል እንዳላቸው ተናግረዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቁጣ መገንፈልህ በልጆችህ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመዝናኛው ዓለም ስለ ቁጣና ጠበኝነት ያለህን አመለካከት እየቀረጸው ነው?