በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አይን ጃሉት—የዓለም ታሪክ የተለወጠበት ቦታ

አይን ጃሉት—የዓለም ታሪክ የተለወጠበት ቦታ

አይን ጃሉት—የዓለም ታሪክ የተለወጠበት ቦታ

ከሞንጎሊያ እየተመሙ የወጡት ምሕረት የለሽ ጦረኞች፣ እጅ ለመስጠት አሻፈረኝ ያላቸውን ከተማ በሙሉ የፍርስራሽ ክምር እያደረጉ ነው። እነዚህ ጋላቢዎች የካቲት 1258 በባግዳድ ላይ በመዝመት የቁጣቸው ገፈት ቀማሽ ያደረጓት ሲሆን የከተማዋን ቅጥሮችም አፈራረሱ። በዚያም ለአንድ ሳምንት ያህል ሕዝቡን ሲጨፈጭፉና ንብረታቸውን ሲዘርፉ ሰነበቱ። ሞንጎሊያውያን መላውን የሙስሊም ማኅበረሰብ በፍርሃት አርበደበዱት። *

ጥር 1260 ላይ ደግሞ ሞንጎሊያውያን ወደ ምዕራብ በመገስገስ የሶርያዋ አሌፖ የባግዳድን ዓይነት ጽዋ እንድትጎነጭ አደረጉ። መጋቢት ላይ ደማስቆ በሮቿን ወለል አድርጋ በመክፈት ለሞንጎሊያውያን እጅ ሰጠች። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሞንጎሊያውያን የፓለስቲና ከተሞች የነበሩትን ናብለስን (በጥንቷ ሴኬም አቅራቢያ) እና ጋዛን ተቆጣጠሩ።

የሞንጎሊያውያኑ የጦር ጄኔራል ሁሌጉ፣ ሙስሊም የሆነውን የግብፅ መሪ ሱልጣን አል ሙዛፈር ሰይፍ አል ዲን ኩቱስን እጅ እንዲሰጥ ጠየቀው። ሱልጣኑ እጅ ካልሰጠ ግብፅ የከፋ መዘዝ እንደሚከተላት ሁሌጉ ዛተ። የሁሌጉ ሠራዊት 20,000 ከሚያህለው የግብፅ ሠራዊት በ15 እጥፍ ይበልጥ ነበር። የእስልምና የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ናዚር አኽመድ “የሙስሊሙ ዓለም ለመጥፋት ተቃርቦ ነበር” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ሱልጣን ኩቱስ ምን ያደርግ ይሆን?

ኩቱስ እና ማምሉኮች

ኩቱስ፣ ማምሉክ ማለትም የቱርክ ዝርያ የሆነ ባሪያ ነበር። ማምሉኮች፣ መቀመጫቸውን በካይሮ ላደረጉት አዩቢድ ተብለው የሚጠሩ የግብፅ ሱልጣኖች በወታደርነት የሚያገለግሉ ባሪያዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ በ1250 እነዚህ ባሪያዎች ጌቶቻቸውን በመገልበጥ የግብፅ መሪዎች ሆኑ። በውትድርና የሚያገለግል ባሪያ የነበረው ኩቱስም የኋላ ኋላ ሥልጣን ያዘና በ1259 ሱልጣን ሆነ። ኩቱስ ብቃት ያለው ጦረኛ በመሆኑ ያለ ምንም ውጊያ እጅ የሚሰጥ ዓይነት ሰው አልነበረም። ይሁንና ሞንጎሊያውያንን ድል የማድረግ አጋጣሚው የመነመነ ነበር። ልክ በዚህ ጊዜ በተከታታይ የተከሰቱት ሁኔታዎች ግን የዓለምን ታሪክ ቀየሩት።

ሁሌጉ፣ ታላቁ የሞንጎሊያ ካን የነበረው ሞንግኬ እንዳረፈ የሚገልጽ ዜና ርቃ ከምትገኘው ከሞንጎሊያ ደረሰው። ሁሌጉ በዚህ ጊዜ በአገሩ የሥልጣን ሽኩቻ ሊነሳ እንደሚችል በመገመት አብዛኛውን ሠራዊቱን ይዞ ወደ ሞንጎሊያ ተመለሰ። ግብፅን ድል ለማድረግ ብዙ ተዋጊዎች እንደሚያስፈልጉ ስላልተሰማው በዚያ ያስቀረው ከ10,000 እስከ 20,000 የሚያህሉ ወታደሮችን ብቻ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ኩቱስ ሁኔታዎች በዚህ መንገድ መለወጣቸውን ሲያይ በለስ እንደሚቀናው ተሰማው። ወራሪዎቹን ድል ለማድረግ ከፈለገ ይህ አጋጣሚ ፈጽሞ ሊያመልጠው እንደማይገባ ተገነዘበ።

ይሁን እንጂ በግብፅና በሞንጎሊያውያን መካከል የሙስሊሞች ጠላት የሆነ ሌላ ሠራዊት ነበረ፤ ይህ ሠራዊት “ቅድስቲቱን ምድር” የክርስቲያኖች ለማድረግ ወደ ፓለስቲና የመጡ የመስቀል ጦረኞችን ያቀፈ ነበር። ኩቱስ የመስቀል ጦረኞቹ እንዲያሳልፉትና ሞንጎሊያውያንን በፓለስቲና በሚዋጋበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ነገር እንዲሸጡለት ጠየቃቸው። የመስቀል ጦረኞቹም በዚህ ተስማሙ። ደግሞም ሞንጎሊያውያኑ ስጋት የፈጠሩት ለሙስሊሞቹ ብቻ ሳይሆን ለመስቀል ጦረኞቹም ጭምር ነበር፤ በመሆኑም የመስቀል ጦረኞቹ ከሞንጎሊያውያኑ ለመገላገል የነበራቸው ብቸኛ ተስፋ ኩቱስ ነበር።

በዚህ መንገድ በማምሉኮችና በሞንጎሊያውያን መካከል ለሚደረገው ወሳኝ ጦርነት መድረኩ ተመቻቸ።

በፓለስቲና ያለው አይን ጃሉት

የማምሉኮችና የሞንጎሊያውያን ሠራዊት መስከረም 1260 በኤዝድራኢሎን ሜዳ በሚገኘው በአይን ጃሉት ተዋጋ። አይን ጃሉት በጥንታዊቷ የመጊዶ ከተማ አቅራቢያ ትገኝ እንደነበረ ይታመናል። *

የታሪክ ምሁር የሆኑት ራሺድ አል ዲን እንደሚናገሩት ማምሉኮች ሞንጎሊያውያንን በመጊዶ ሸምቀው ጠበቋቸው። ኩቱስ፣ አብዛኛው ፈረሰኛ ሠራዊቱ በሜዳው ዙሪያ ባሉት ኮረብቶች ውስጥ እንዲደበቅ ካደረገ በኋላ ሞንጎሊያውያኑን ለጦርነት ለማነሳሳት ሲል ጥቂት ወታደሮችን ብቻ ወደ ውጊያው አውድማ ላከ። ሞንጎሊያውያኑም መላውን የማምሉክ ሠራዊት ያገኙ ስለመሰላቸው ጥቃት ሰነዘሩባቸው። በዚህ ጊዜ ኩቱስ ካደፈጠበት በድንገት በመውጣት ሞንጎሊያውያኑን ወጥመዱ ውስጥ አስገባቸው። ኩቱስ፣ ወታደሮቹ ከተደበቁበት እየተፈተለኩ ወጥተው የሞንጎሊያውያንን ሠራዊት ከየአቅጣጫው እንዲያጠቁ አዘዘ። በዚህ መንገድ ወራሪዎቹ ድል ተነሱ።

ሞንጎሊያውያን ከ43 ዓመታት በፊት ከአገራቸው በስተምዕራብ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሽንፈት ሲገጥማቸው ይህ የመጀመሪያው ነበር። በአይን ጃሉት በተደረገው በዚህ ውጊያ የተካፈሉት ወታደሮች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም ጦርነቱ በታሪክ ውስጥ በጣም ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ውጊያዎች ተርታ ይመደባል። ይህ ጦርነት ሙስሊሞችን ከምድር ገጽ ከመጥፋት ከመታደጉም ሌላ ሞንጎሊያውያን ሊሸነፉ አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ ውድቅ አድርጓል፤ እንዲሁም የማምሉክ ሠራዊት የተወሰዱበትን የግዛት ክልሎች እንዲያስመልስ መንገድ ከፍቷል።

የአይን ጃሉት ጦርነት ያስከተለው ውጤት

ሞንጎሊያውያን ከዚያ በኋላ ወደ ሶርያና ፓለስቲና ብዙ ጊዜ ተመልሰው ቢመጡም ግብፅ ላይ ግን ዳግመኛ ስጋት አልፈጠሩም። የሁሌጉ ዝርያዎች በፋርስ የሰፈሩ ሲሆን እስልምናንም ተቀብለዋል፤ ከጊዜ በኋላም የእስልምና ባሕል ባለአደራዎች ሆነዋል። እነሱ የሚኖሩበት ክልል የፋርስ ኢልካኔት በመባል የሚጠራ ሲሆን ይህም “የበታች ካን ግዛት” ማለት ነው።

ኩቱስ ግን በሕይወት ቆይቶ ይህን ድል ለማጣጣም አልታደለም። ከአይን ጃሉት ጦርነት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተቀናቃኞቹ ተገደለ። ከተቀናቃኞቹ አንዱ ቀዳማዊ ባይባርስ ሲሆን እሱም ዳግም በተዋሃደው የግብፅና የሶርያ መንግሥት ላይ የገዛው የመጀመሪያው ሱልጣን ነበር። ብዙዎች ባይባርስን የማምሉክ አገዛዝ እውነተኛ መሥራች እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ጥሩ አስተዳደር የነበረውና ባለጸጋ የሆነው እሱ የመሠረተው አዲስ መንግሥት ለሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት ይኸውም እስከ 1517 ድረስ ቆይቷል።

ማምሉኮች ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ወደ 250 ገደማ የሚሆኑ ዓመታት ውስጥ የመስቀል ጦረኞችን ከቅድስቲቱ ምድር ያስወጡ ከመሆኑም ሌላ ንግድና ኢንዱስትሪን ያበረታቱ እንዲሁም የኪነ ጥበብ እድገትን ይደግፉ ነበር፤ ከዚህም በላይ ሆስፒታሎችን፣ መስጊዶችንና ትምህርት ቤቶችን ገንብተዋል። በእነሱ አገዛዝ ሥር ግብፅ የሙስሊሙ ዓለም ዋነኛ ማዕከል ሆና ነበር።

በአይን ጃሉት የተደረገው ጦርነት ከመካከለኛው ምሥራቅ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። በምዕራቡ ዓለም ለነበረው ሥልጣኔም መንገድ ጠርጓል። ሳውዲ አራምኮ ዎርልድ የተሰኘው መጽሔት “ሞንጎሊያውያን ተሳክቶላቸው ግብፅን ድል ቢያደርጉ ኖሮ ሁሌጉ ከተመለሰ በኋላ በሰሜን አፍሪካ አቋርጠው ወደ ጂብራልተር የባሕር ወሽመጥ ማቅናት ይችሉ ነበር” ብሏል። ሞንጎሊያውያን በዚህ ጊዜ ፖላንድንም መያዛቸው ስለማይቀር አውሮፓን ከሁሉም አቅጣጫ በመቆጣጠር የባሕር በር እንዳይኖራት ማድረግ ይችሉ ነበር።

“እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ የአውሮፓ ሕዳሴ ሊከሰት ይችላል?” በማለት ከላይ የተጠቀሰው መጽሔት ይጠይቃል። “ዓለማችን አሁን ካላት እጅግ የተለየ መልክ ይኖራት ነበር።”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ስለ ሞንጎሊያውያን እና በጦርነት ድል አድርገው ስለያዟቸው ግዛቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 2008 ንቁ! እትምን ተመልከት።

^ አን.11 “በመጊዶ” ብዙ ወሳኝ ጦርነቶች ስለተካሄዱ ይህ ቃል አርማጌዶን ወይም በዕብራይስጥ ሐር ማጌዶን ተብሎ ከሚጠራው በብዙዎች ዘንድ ከሚታወቅ ጦርነት ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አርማጌዶን “ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን [የሚሆን] ጦርነት” እንደሆነ ይገልጻል።​—ራእይ 16:14, 16 አ.መ.ት

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ደማስቆ

ሶሪያ

የታቦር ተራራ

የኤዝድራኢሎን ሜዳ

አይን ጃሉት (መጊዶ አቅራቢያ)

ናብለስ (ሴኬም)

ኢየሩሳሌም

ጋዛ

ግብፅ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቷ መጊዶ ከተማ የነበረችበት ስፍራ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማምሉኮችና የሞንጎሊያውያን ሠራዊት መስከረም 1260 በኤዝድራኢሎን ሜዳ በምትገኘው በአይን ጃሉት ተዋጉ

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቷ ሴኬም ከተማ ፍርስራሽ፤ ዘመናዊው የናብለስ ከተማ በከፊል ከበስተጀርባዋ ይታያል