በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በእንግሊዝና በዌልስ የሚጋቡ ሰዎች ቁጥር በጣም ያሽቆለቆለ ሲሆን መዝገብ መያዝ ከተጀመረበት ጊዜ [1862] ወዲህ የመጨረሻው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።”​—ብሔራዊ የስታትስቲክስ ቢሮ፣ ብሪታንያ

በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ትናንሽ የግል ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት “ሠራተኞቻቸው በቀጣዩ ዓመት ውስጥ [ከኩባንያው] ዋጋማ የሆነ ንብረት ሊሰርቁ እንደሚችሉ ይጠብቃሉ።”​—ሮይተርስ ዜና አገልግሎት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የቻይና ባለሥልጣናት የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የሚገኙባቸውን ድረ ገጾች ለመዝጋት ዘመቻ በጀመሩ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ “60,000 የሚያህሉ [እንዲህ ዓይነት] ድረ ገጾችን ዘግተዋል” በማለት የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን እንዲሁም ሕገ ወጥ ጽሑፎችን የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ተቋም ዘግቧል።​—ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና

“ከ215 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ይኸውም ከዓለማችን ሕዝብ ሦስት በመቶ የሚሆኑት፣ በአሁኑ ጊዜ [የሚኖሩት] ከትውልድ አገራቸው ውጭ ነው።”​—የተባበሩት መንግሥታት የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ ጣሊያን

“በሕንድ በየቀኑ 19 ተማሪዎች ራሳቸውን የሚገድሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስቱ [ራሳቸውን የሚገድሉት] ፈተና መውደቅ ስለሚያስፈራቸው ነው።”​—ኢንድያ ቱዴይ ኢንተርናሽናል፣ ሕንድ

የቁማር ኢንዱስትሪ የሚጠቀምባቸው የንግድ ዘዴዎች

ጀርመን ውስጥ የቁማር ሱስ ያለበት አንድ ሰው፣ ሱስ ከሌለበት ቁማርተኛ አንጻር በአማካይ ከአሥር እጥፍ በላይ ገንዘብ ያጠፋል። በመሆኑም “የዚህ ኢንዱስትሪ አትራፊነት” በሱሰኛ ቁማርተኞች ላይ የተመካ እንደሆነ ዕለታዊው ሱትዶይቸ ጻይቱንግ ገልጿል። የቁማር ኢንዱስትሪ፣ ትርፋማነትን ለማሳደግ ሲል ጨዋታዎችንና የቁማር ማሽኖችን የሚያዘጋጀው ሱስ በሚያስይዝና ሱሰኞችን በሚበዘብዝ መልኩ ነው። ማሽኖቹ ይበልጥ ፈጣን በሆኑ መጠን ተጫዋቹም ይበልጥ ራሱን መቆጣጠር እያቃተው የሚሄድ ከመሆኑም ሌላ ሱሰኛ ይሆናል። እንዲህ ያሉት የንግድ ዘዴዎች ውጤታማ ናቸው፤ የቁማር ማሽኖች ከሚያስገቡት ገቢ 56 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ሱሰኛ ከሆኑ ቁማርተኞች ነው። በተመሳሳይም ቁማር የሚያጫውቱ ቤቶች ከሚኖራቸው ገቢ 38 በመቶ የሚሆነው እንዲሁም በኢንተርኔት አማካኝነት ቁማር የሚያጫውቱ ድርጅቶች ከሚኖራቸው ገቢ 60 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከሱሰኞች ነው።

ወደ ዳኛ ለመሄድ ጥሩ ሰዓት አለ?

ጥቃቅን ነገሮች ዳኞች በሚያደርጉት የፍርድ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ? አንድ ጥናት ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ያሳያል። ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች በእስራኤል የሚገኙ ተሞክሮ ያላቸው ዳኞች ያስተላለፏቸውን 1,000 የሚያህሉ የአመክሮ ውሳኔዎች መርምረው ነበር። ጥናቱ እንዳሳየው ዳኞቹ ከሻይ ሰዓታቸው እንዲሁም ከምሳ ሰዓታቸው እንደተመለሱ ችሎቱ ፊት የሚቀርበው እስረኛ በአመክሮ እንዲፈታ የመወሰናቸው አጋጣሚ ከፍ ያለ (65 በመቶ ገደማ) ሲሆን ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ግን እንዲህ ያለ ውሳኔ የመስጠት አጋጣሚያቸው እያሽቆለቆለ ሄዶ ዜሮ ይደርሳል፤ እረፍት ካደረጉ በኋላ ደግሞ ይህ አኃዝ እንደገና ወደ 65 በመቶ ይመለሳል። ተመራማሪዎቹ የፍርድ ሂደቱ ሁልጊዜ በሕጉ ላይ ብቻ የተመካ እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን “በሕግ ነክ ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የማይገባቸው ሌሎች ነገሮችም የፍርዱን አቅጣጫ ሊያስቀይሩት ይችላሉ” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።