በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥነ ፈለክና የመካከለኛው ዘመን ሊቃውንት

ሥነ ፈለክና የመካከለኛው ዘመን ሊቃውንት

ሥነ ፈለክና የመካከለኛው ዘመን ሊቃውንት

በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት ላይ ያደረጉት ጥናት በአድናቆት እንዲደመሙ አድርጓቸዋል። የሰው ልጅ የእነዚህን የጠፈር አካላት አቀማመጥና እንቅስቃሴ በማጥናት ቀናትን፣ ወራትንና ዓመታትን መቁጠር ችሏል።

ምሽት ላይ የሚታዩትን የሰማይ አካላት ያጠኑ ከነበሩ ምሁራን መካከል አረቦች ይገኙበታል። በመካከለኛው ምሥራቅ ሳይንሳዊ እውቀት ማበብ የጀመረው በዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሲሆን በዚያ ወቅት የነበሩት አረብኛ ተናጋሪ የሥነ ፈለክ ምሁራን በዚህ መስክ እንደ ሊቃውንት ይቆጠሩ ነበር። የእነዚህ ሊቃውንት ግኝቶች አስደናቂ በሆነው በዚህ መስክ ለታየው እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ፈር ቀዳጅ ምሁራን

በሰባተኛውና በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እስልምና ከአረብ ምድር ተነስቶ በስተምዕራብ እስከ ሰሜን አፍሪካና ስፔን፣ በስተምሥራቅ ደግሞ እስከ አፍጋኒስታን ድረስ ተስፋፋ። ፋርሳውያንና ግሪኮች በባቢሎናውያንና በግብፃውያን ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ተመሥርተው የደረሱባቸውን ግኝቶች በጣም ሰፊ በሆነው የአረቦች ክልል ውስጥ የሚኖሩት ምሁራን ተጠቅመውባቸዋል።

ከዚያም በዘጠነኛው መቶ ዘመን፣ የግሪካዊውን የሥነ ፈለክ ምሁር የቶለሚን ሥራዎች ጨምሮ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሳይንሳዊ ጽሑፎች ወደ አረብኛ ተተረጎሙ። * ከአፍጋኒስታን አንስቶ እስከ አትላንቲክ ውቅያኖስ ያሉትን አካባቢዎች ይገዙ የነበሩት አባሲዶች፣ ሳንስክሪት በተባለው ጥንታዊ የሕንድ ቋንቋ የተዘጋጁና በሒሳብ፣ በሥነ ፈለክ እንዲሁም በሌሎች የሳይንስ ዘርፎች በርካታ መረጃዎችን የያዙ ጽሑፎችን ከሕንድ ማግኘት ችለው ነበር።

በእስልምና እምነት ለሥነ ፈለክ እውቀት ከፍተኛ ቦታ ይሰጥ ነበር። ለምን? አንደኛው ምክንያት ከአምልኳቸው ጋር የተያያዘ ነው። ሙስሊሞች በሚሰግዱበት ወቅት ፊታቸውን መካ ወዳለበት አቅጣጫ ማዞር እንዳለባቸው ያምናሉ፤ የሥነ ፈለክ ምሁራን ደግሞ ከየትኛውም ቦታ የመካን አቅጣጫ ማወቅ ይችላሉ። በ13ኛው መቶ ዘመን አንዳንድ መስጊዶች፣ ምዕመናኑ የሚሰግዱበትን ትክክለኛ ሰዓት የሚነግራቸው የሥነ ፈለክ ምሁር ወይም ሙዋቂት ይቀጥሩ ነበር። በተጨማሪም የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ያላቸውን መረጃ መሠረት በማድረግ በረመዳን ወር እንደሚከናወነው ጾም ያሉ ሃይማኖታዊ በዓሎችና ሥነ ሥርዓቶች የሚውሉበትን ቀን ማወቅ ችለው ነበር። ከዚህም ሌላ የመካ ተጓዦች፣ መካ ምን ያህል ርቆ እንደሚገኝ ለማወቅና የተሻለውን መንገድ ለመምረጥ እንዲችሉ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችን ያማክሩ ነበር።

የመንግሥት ድጋፍ

በዘጠነኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በባግዳድ፣ ማንኛውም ምሑር ሥነ ፈለክን እንዲያጠና ይደረግ ነበር። ከሊፋ አል ማሙን መጀመሪያ በባግዳድ ከዚያም በደማስቆ አቅራቢያ የጠፈር ምርምር ጣቢያ አቋቁሞ ነበር። የጂኦግራፊና የሒሳብ ሊቃውንትን ያካተተው የአል ማሙን ምሁራን ከፋርስ፣ ከሕንድና ከግሪክ የተገኙ የሥነ ፈለክ ትውፊቶችን ይመረምሩ፣ ያነጻጽሩና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማስታረቅ ይሞክሩ ነበር። በተጨማሪም በሌሎች በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች የጠፈር ምርምር ጣቢያዎች ተገንብተዋል። *

በእነዚህ የምርምር ማዕከላት ይሠሩ የነበሩ ምሁራን ከኖሩበት ዘመን አንጻር አስደናቂ የሆነ ውጤት አግኝተዋል። ለምሳሌ በ1031 አቡ ሬሃን አል ቢሩኒ፣ ፕላኔቶች ፀሐይን የሚዞሩበት ምሕዋር ክብ ሳይሆን እንደ እንቁላል ሾጠጥ ያለ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

ምድርን መለካት

የእስልምና መስፋፋት የካርታ ሥራና አቅጣጫን የማወቅ ሳይንስ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል። ካርታ ሠሪዎች ከቀድሞው ይበልጥ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ ካርታ ለመሳል ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአብዛኛውም ተሳክቶላቸዋል። ከሊፋ አል ማሙን ያዘጋጅ የነበረው የዓለም ካርታ ትክክለኛና የኬክሮስ መስመሮችን የሚያሳይ እንዲሆን ስለፈለገ ሁለት የቀያሾች ቡድን ወደ ሶርያ ምድረ በዳ ልኮ ነበር። እነዚህ ቀያሽ ቡድኖች አስትሮሌብ (የሰማይ አካላት የሚገኙበትን ቦታ ለማወቅ የሚያስችል መሣሪያ) እንዲሁም የመለኪያ ዘንግና ገመድ ይዘው በተቃራኒ አቅጣጫዎች የተጓዙ ሲሆን የሰሜን ኮከብን ከምድር ሲያዩት የአንድ ዲግሪ ለውጥ እስኪታያቸው ድረስ ተጓዙ። ከዚያም የተጓዙበት ርቀት አንድ ዲግሪ ኬክሮስ እንደሆነ በሌላ አባባል የምድርን መጠነ ዙሪያ 1/360 እንደሚሆን አሰቡ። ከዚህ በመነሳት ከሰሜን ዋልታ እስከ ደቡብ ዋልታ ያለው የምድር መጠነ ዙሪያ 37,369 ኪሎ ሜትር እንደሚሆን ያሰሉ ሲሆን ይህም ከትክክለኛው አኃዝ (40,008 ኪሎ ሜትር) ጋር በጣም ተቀራራቢ ነው!

የመካከለኛው ምሥራቅ የጠፈር ምርምር ጣቢያዎች፣ የጠፈር አካላትን እንቅስቃሴ ለማጥናት የሚያስችሉ የተራቀቁ መሣሪያዎች ነበሯቸው፤ ከእነዚህም መካከል የሰማይ አካላት የሚገኙበትን ቦታ ለማወቅ የሚያስችሉት አስትሮሌብ፣ ኳድራንት እና ሴክስታንት የተባሉት መሣሪያዎች እንዲሁም የጥላ ሰዓት ይገኙበታል። ከእነዚህ መሣሪያዎች አንዳንዶቹ በጣም ትልልቅ ነበሩ። መሣሪያዎቹ ትልልቅ ከሆኑ የሚሰጡትም መረጃ የበለጠ ትክክለኛ እንደሚሆን ይታሰብ ነበር።

የመካከለኛው ዘመን የሥነ ፈለክ ሊቃውንት የተዉት ቅርስ

የመካከለኛው ዘመን የሥነ ፈለክ ሊቃውንት በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን አከናውነዋል። ለከዋክብትና ለኅብረ ከዋክብት ስም አውጥተው መዝግበዋቸዋል፣ ኅብረ ከዋክብትን በሥዕል አስቀምጠዋቸዋል፣ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ የቀን መቁጠሪያ አዘጋጅተዋል እንዲሁም የጠፈር አካላትን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ሠንጠረዦችን አሻሽለዋል። በቀንም ሆነ በማታ በማንኛውም ሰዓት ፀሐይ፣ ጨረቃና በዓይን ሊታዩ የሚችሉ አምስት ፕላኔቶች የሚገኙበትን ቦታ በትክክል መጠቆም ችለዋል፤ ይህም አቅጣጫን በማወቅ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ነበረው። በተጨማሪም የጠፈር አካላትን አቀማመጥ በመመልከት ሰዓትን ማወቅ እንዲሁም ቀንን እና ወርን መናገር ይችሉ ነበር።

አረብኛ ተናጋሪ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ስለ ፕላኔቶች እንቅስቃሴ ካቀረቡት ንድፈ ሐሳብ ማየት እንደሚቻለው፣ ቶለሚ በሠራው የሰማይ አካላትን የሚያሳይ ሞዴል ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በጣም ተቃርበው ነበር። ያላወቁት ነገር የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ምድር ሳትሆን ፀሐይ መሆኗን ነው። ያም ቢሆን የከዋክብትን እንቅስቃሴ በትክክል በመመዝገብ ረገድ ፈር ቀዳጅ ሆነዋል፤ እንዲሁም ግኝቶቻቸው ከዚያ በኋላ ለተነሱ በመላው ዓለም የሚገኙ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ውድ ቅርስ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 በዚህ ጊዜ ግሪካውያን ምድር ክብ መሆኗን አውቀው ነበር። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ‘ምድር ክብ ካልሆነች አንድ ሰው ወደ ደቡብ በሚጓዝበት ጊዜ የሰሜን ኮከብ ዝቅ ያለ ሆኖ የሚታየው ለምንድን ነው?’ ብለው ስላሰቡ ነው።

^ አን.9 አብዛኛውን ጊዜ ለእነዚህ የምርምር ጣቢያዎች መገንባት ምክንያት የሚሆነው አንድ ገዢ ስለ ኮከብ ቆጠራ ለማወቅ ያለው ፍላጎት ነበር።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ በርካታ ዓመታዊ መጻሕፍትን በአረብ አገሮች በሙሉ ያዘጋጁ ነበር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ጥንታዊ “የኪስ ኮምፒውተር”

ሴክስታንት በሚባለው መሣሪያ የተተካው አስትሮሌብ “ቴሌስኮፕ ከመፈልሰፉ በፊት የነበረ በጣም ጠቃሚ የሥነ ፈለክ መሣሪያ” እንደሆነ አንድ መጽሐፍ ይናገራል። በመካከለኛው ምሥራቅ የነበሩ የሳይንስ ሊቃውንት ይህን መሣሪያ ከጊዜና ከጠፈር አካላት አቀማመጥ ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይጠቀሙበት ነበር።

አስትሮሌብ፣ የጠፈር አካላት ምስል በሚያብረቀርቅ የብረት ሳህን ላይ ባጌጠ ሁኔታ የተቀረጸበት መሣሪያ ነው። በሳህኑ ጠርዝ ዙሪያ ዲግሪዎች ወይም አንዳንድ ጊዜ በቀን ውስጥ ያሉት ሰዓቶች ይጻፉበታል። የአንድን ኮከብ አቀማመጥ ለማወቅ መሣሪያውን የእጅ ርዝመት ያህል አርቆ ማንጠልጠል ያስፈልጋል፤ በዚህ ጊዜ በላዩ ላይ ያለው ጠቋሚ መሣሪያ (አሊዴድ ይባላል) ጠርዙ ላይ ወደተጻፉት ቁጥሮች ያመለክታል። እነዚህን ቁጥሮች በማንበብ የተፈለገውን መረጃ ማግኘት ይቻላል።

ሁለገብ የሆነው አስትሮሌብ ብዙ ጥቅሞች ነበሩት፤ ይህ መሣሪያ ከዋክብትን ለመለየት፣ በማንኛውም ቀን ፀሐይ የምትወጣበትንና የምትጠልቅበትን ሰዓት ለማወቅ፣ የመካን አቅጣጫ ለማግኘት እንዲሁም መሬት ለመቀየስ፣ የነገሮችን ከፍታ ለመለካትና አቅጣጫን ለማወቅ ያገለግል ነበር። በእርግጥም አስትሮሌብ የዘመኑ “የኪስ ኮምፒውተር” ነበር።

[ሥዕሎች]

የ13ኛው መቶ ዘመን አስትሮሌብ

የ14ኛው መቶ ዘመን አስትሮሌብ ኳድራንት

[የሥዕል መግለጫ]

Astrolabe: Erich Lessing/Art Resource, NY; quadrant astrolabe: © New York Public Library/Photo Researchers, Inc.

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኦቶማን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አረብኛ ተናጋሪ ምሁራን ባቆዩላቸው ዘዴዎች ሲጠቀሙ የሚያሳይ የ16ኛው መቶ ዘመን ሥዕል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጠፈር ሉል፣ 1285 ዓ.ም.

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ965 ዓ.ም. አካባቢ አብድልራህማን አል ሱፊ የተባለ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የጻፈው ስለ ኅብረ ከዋክብት የሚገልጽ የአረብኛ መጽሐፍ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Pages 16 and 17: Art Resource, NY

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Manuscript: By permission of the British Library; globe: © The Bridgeman Art Library