በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከምድር ገጽ ከመጥፋት ሊተርፉ ይችሉ ይሆን?

ከምድር ገጽ ከመጥፋት ሊተርፉ ይችሉ ይሆን?

ከምድር ገጽ ከመጥፋት ሊተርፉ ይችሉ ይሆን?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2002 እንዳስታወቀው በዚያ አሥር ዓመት ውስጥ ዝርያዎች ከምድር ገጽ የሚጠፉበትንና በሥነ ምሕዳሩ ላይ ጉዳት የሚደርስበትን ፍጥነት የመቀነስ ግብ ነበረው። በዚሁ ግብ መሠረት 2010 ዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ዓመት ተብሎ ተሰየመ።

የሚያሳዝነው ግን በ2010 እዚህ ግብ ላይ መድረስ ቀርቶ ወደዚያ መቃረብ እንኳ አልተቻለም። ቢቢሲ እንደዘገበው “የሰው ልጆች በሚያደርጓቸው ነገሮች የተነሳ ዝርያዎች የሚጠፉበት ፍጥነት፣ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ከሚጠፉበት ፍጥነት በ1,000 ጊዜ ይበልጣል።” ኒው ዚላንድ ሄራልድ ያወጣው ዘገባ ሁኔታውን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፤ ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት ዕፅዋት አንዱ፣ ከአምስት አጥቢ እንስሳት አንዱ፣ ከሰባት አእዋፍ አንዱ እንዲሁም በውኃ ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ ከሚኖሩ ሦስት እንስሳት መካከል አንዱ ከምድር ገጽ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።” ባለፉት መቶ ዘመናት በኒው ዚላንድ የታየው ሁኔታ የዚህን ችግር አንድ ገጽታ በግልጽ ለመገንዘብ ያስችለናል።

የኒው ዚላንድ ብዝሃ ሕይወት

በኒው ዚላንድ ሰዎች ከመስፈራቸው በፊት አገሪቷ ለበርካታ ሕያዋን ፍጥረታት ምቹ መኖሪያ ነበረች። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች የአካባቢውን እንስሳት የሚጎዱ ዝርያዎች ይዘው መጡ። ለምሳሌ ፓስፊክን አቋርጠው የመጡት የማውሪ ጎሣዎች፣ ውሾችንና ምናልባትም ለምግብነት ያገለግሉ የነበሩትን ኪኦሪዎች (ወይም የፖሊኔዥያ አይጦች) ወደ ኒው ዚላንድ አመጡ።

ከዚያ በኋላ ደግሞ በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን አውሮፓውያን ሲመጡ አይጦችን፣ አይጠ መጎጦችንና ድመቶችን (ብዙም ሳይቆይ የዱር ድመት ሆነዋል) አመጡ። በተጨማሪም አውሮፓውያኑ ለምግብነት እንዲያገለግሏቸው ፍየሎችን፣ አሳሞችንና ርኤሞችን አምጥተው ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን ደግሞ ብራሽ ቴይልድ ፖሰም የሚባለውን እንስሳና ጥንቸልን ለምግብነትና ለቆዳቸው ሲሉ ያመጡ ሲሆን ይህን ሲያደርጉ እንስሳቱ በአካባቢው ዛፎች፣ አእዋፍና ዕፅዋት ላይ ስለሚያስከትሉት ተጽዕኖ አላሰቡም ነበር።

በ1860ዎቹ ዓመታት የጥንቸሎቹ ብዛት ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ነዋሪዎቹ፣ እነሱን እንዲያድኑላቸው ስቶት የሚባሉትን እንስሳት አመጡ። ይሁን እንጂ እነዚህ እንስሳት ከጥንቸሎቹ ይልቅ ቀርፋፋ የሆኑትንና በቀላሉ የሚያዙትን የአገሬውን አእዋፍ መብላት መረጡ። በዚህም ምክንያት የጥንቸሎቹን ቁጥር መቆጣጠር ሳይቻል ቀረ።

በዛሬው ጊዜ፣ አጥቢ የሆኑ እንስሳት በሚያስከትሉት ጉዳት የተነሳ በዱር ከሚቀፈቀፉት 10 የቡናማ ኪዊ ጫጩቶች መካከል 9ኙ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው እንደሚሞቱ የኒው ዚላንድ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሪፖርት አድርጓል። እስከ አሁን ከ40 የሚበልጡ የአእዋፍ፣ 3 የእንቁራሪት፣ ቢያንስ 3 የእንሽላሊት ዝርያዎችንና 1 የሌሊት ወፍ ዝርያን እንዲሁም በርካታ ነፍሳትን ጨምሮ ብዙ ዝርያዎች ጨርሶ ጠፍተዋል። አገር በቀል ከሆኑት 5,819 የኒው ዚላንድ ዕፅዋትና እንስሳት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጨርሶ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፤ በዚህም ምክንያት በፕላኔታችን ላይ ከፍተኛ አደጋ ከተጋረጠባቸው ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ሊመደቡ ችለዋል።

ውጤት ያስገኙ ጥረቶች

በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጎጂ የሆኑ የዕፅዋት እና የእንስሳት ዝርያዎች ወደ ኒው ዚላንድ እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ናቸው። በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተለይ ከደሴቶች ላይ ጎጂ የሆኑ ዝርያዎችን ለማጥፋት ብዙ ጥረት አድርጓል፤ እንዲሁም እንስሳቱንና ዕፅዋቱን ለመጠበቅ የተከለሉ ቦታዎች አዘጋጅቷል።

ከተከለሉት ደሴቶች መካከል አንዱ ከኦክላንድ የዋንጋፓራኦዋ ባሕረ ገብ መሬት ባሻገር የሚገኘው ቲሪቲሪ ማታንጊ ነው። በ1993 ከደሴቱ ላይ አይጦች ሙሉ በሙሉ የተወገዱና 280,000 የሚያህሉ አገር በቀል ዛፎች የተተከሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይህ የተከለለ አካባቢ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል። ጎብኚዎች እንደገና በአካባቢው በድጋሚ እንዲራቡ የተደረጉትን የአእዋፍ ዝርያዎች ማየትና ዝማሬያቸውን ማዳመጥ ይችላሉ፤ ከእነዚህም መካከል እንደ ሳድልባክ፣ ታካሄ፣ ኮካኮ፣ ራይፍልማን እና ስቲችበርድ ያሉት ብርቅዬ አእዋፍ ይገኙበታል። እነዚህ ውብ ፍጥረታት ከአዳኝ እንስሳት ነፃ በሆነ አካባቢ በጣም ተመችቷቸው ስለሚኖሩ ጎብኚዎች ቀረብ ብለው ቢያዩአቸውም አይደነብሩም።

ወደ አንታርክቲክ ክልል በተጠጋው በካምፕቤል ደሴት ላይ ሁለት ዓመት የፈጀ አይጦችን የማጥፋት ዘመቻ ከተከናወነ በኋላ በ2003 ደሴቱ ከአይጥ ነፃ ሊሆን ችሏል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ አገር በቀል የሆኑ ዕፅዋት እንደገና ማቆጥቆጥ የጀመሩ ሲሆን የባሕር አእዋፍም እየተመለሱ ነው። ካምፕቤል አይላንድ ቲል የተባለው እጅግ ብርቅዬ የሆነ የዳክዬ ዝርያ እንኳ እንደገና በደሴቱ ላይ እንዲረባ ተደርጓል።

በቅርቡ ደግሞ በራንጊቶቶ እና በሞቱታፑ ደሴቶች እንዲሁም በኦክላንድ ሃውራኪ ባሕረ ሰላጤ ላይ ሥነ ምሕዳሩን ወደነበረበት ለመመለስ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ተካሂዷል። የዚህ እንቅስቃሴ ዓላማ በስፋቱ ከዓለም አንደኛ የሆነውን የፖሁቱካዋ ዛፍ ደን መጠበቅ እንዲሁም በድጋሚ ወደ ደሴቶቹ የመጡትን ዕፅዋትና እንስሳት መንከባከብ ነው። ጥንቸሎች፣ ጃርቶች፣ የዱር ድመቶች፣ የተለያዩ የአይጥ ዝርያዎች፣ አይጠ መጎጦችና ስቶት የሚባለውን እንስሳ ጨምሮ ለሥነ ምሕዳሩ ጎጂ የሆኑ በርካታ እንስሳት ከደሴቶቹ ላይ እንዲጠፉ ከተደረገ በኋላ ሬድ ክራውንድ ፓራኪት እና ቤልበርድ የተባሉት የአእዋፍ ዝርያዎች በደሴቶቹ ላይ እንደገና ብቅ ብለዋል፤ እነዚህ ወፎች ለአንድ ምዕተ ዓመት ያህል በደሴቶቹ ላይ አልታዩም ነበር!

እነዚህ ምሳሌዎች፣ ለመጥፋት የተቃረቡ ፍጥረታትን ለመታደግና ሰዎች አርቀው ባለማሰባቸው በተፈጥሮ ላይ ያደረሱትን ጉዳት ለማስተካከል ምን ማድረግ እንደሚቻል ያሳያሉ። በመላው ዓለም የሚኖሩ ተፈጥሮን የሚወዱ ሰዎች ‘ሰማይንና ምድርን የፈጠረው’ ይሖዋ አምላክ በዕፅዋት፣ በእንስሳትና በአጠቃላይ በሥነ ምሕዳሩ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ጎጂ ተግባራትን በሙሉ እንደሚያስወግድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የገባውን ቃል ፍጻሜ በጉጉት ይጠባበቃሉ።—መዝሙር 115:15፤ ራእይ 21:5

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በአሁኑ ጊዜ ከ10 የኪዊ ጫጩቶች መካከል 9ኙ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ይሞታሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሀብትን በጥበብ መጠቀም

በመላው ዓለም የሚገኙ ስለ አካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆሩ ሰዎች፣ ለጥፋት የተቃረቡ ዝርያዎች መብዛትና በአንጻሩ ደግሞ እነዚህን ዝርያዎች ለማዳን የሚያስችል አቅም ውስን መሆን ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። ይህን ችግር ለመቋቋም የተቀየሰው አንዱ መንገድ፣ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሆስፒታሎች በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ታካሚዎች ከሚመረጡበት ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ዘዴ ሀብትን ከሁሉ የተሻለ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ ለመጠቀም የሚረዳ ሲሆን ይህንንም ለማድረግ የሚከተሉትን ነጥቦች ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፦ (1) አንድ ዝርያ ወይም ሥነ ምሕዳር ያለው ጥቅም፣ (2) የታሰበው እርምጃ የተሳካ ውጤት የማስገኘት አጋጣሚው እንዲሁም (3) የሚጠይቀው ወጪ። በዚህ ዘዴ የሚስማማው ሁሉም ሰው ባይሆንም ይህን ዘዴ የሚደግፉት ሰዎች፣ በዚህ መንገድ በመጠቀም ያለውን ውስን ሀብት የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ በሚችል ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ይናገራሉ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኒው ዚላንድ

ሃውራኪ ባሕረ ሰላጤ

ቲሪቲሪ ማታንጊ ደሴት

ራንጊቶቶ እና ሞቱታፑ

ካምፕቤል ደሴት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቡናማ ኪዊ

[የሥዕሉ ምንጭ]

© S Sailer/A Sailer/age fotostock

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቲሪቲሪ ማታንጊ ደሴት የሚኖር ታካሄ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካምፕቤል ደሴት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Takahe: © FLPA/Terry Whittaker/age fotostock; Campbell Island: © Frans Lanting/CORBIS