በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ያለብኝ ለምንድን ነው?

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያስደስትሃል?

አዎ → በዚሁ ቀጥል

አይ → ምን ማድረግ ትችላለህ?

ክርስቲያኖች አምላክን ለማምለክ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታዝዘዋል። (ዕብራውያን 10:25) ይሁን እንጂ ስብሰባ ላይ መገኘት ባያስደስትህስ? ስብሰባ ላይ ብትገኝም ‘ምነው ሌላ ቦታ በሄድኩ ኖሮ?’ እያልክ የምታስብ ቢሆንስ? ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ጠቃሚ ምክሮች በተግባር በማዋል ማስተካከያዎች እንድታደርግ እናበረታታሃለን።

1. አዘውታሪ ሁን

ቁልፍ ጥቅስ፦ “አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል።”​—ዕብራውያን 10:25

የማያስደስትህን ነገር አዘውትረህ ማድረግ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? በቀላል አነጋገር ልትወደው የምትችለው እንደዚህ ካደረግህ ብቻ ስለሆነ ነው! እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በአንድ ስፖርታዊ ጨዋታ እየተካፈልክ ነው እንበል፤ ለልምምድ አልፎ አልፎ ብቻ የምትሄድ ከሆነ በዚህ ስፖርት ጎበዝ ልትሆንና ጨዋታውን ልትወደው ትችላለህ? ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ በተገኘህ መጠን በመንፈሳዊ ይበልጥ የተስተካከለ አቋም ይኖርሃል። ይህ ደግሞ ወደ ስብሰባዎች አዘውትረህ ለመሄድ ያነሳሳሃል!​—ማቴዎስ 5:3

ጠቃሚ ምክር፦ ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ ቢያንስ ለአንዱ ተናጋሪ ካቀረበው ንግግር ውስጥ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘኸውን ነጥብ ንገረው። በስብሰባው ላይ ያገኘኸውን አንድ ጥቅም በማስታወሻህ ላይ ጻፍ። በስብሰባዎች ላይ ከሚቀርበው ትምህርት ውስጥ አብዛኛው ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን የሚመለከት በመሆኑ ስለ እምነትህ ለሌሎች የመናገር ችሎታህን የማሻሻል ግብ ይኑርህ። እንዲህ ያለ ግብ ማውጣትህ በስብሰባዎች ላይ የሚቀርበው ትምህርት ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆንልህ ያደርጋል።

“ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ ተምሬያለሁ። ትንሽ ልጅ እያለሁ እንኳ ከስብሰባዎች ዝም ብዬ መቅረት እንደምችል አስቤ አላውቅም። ይህ አመለካከቴ አሁንም አልተቀየረም።”​ኬልሲ

ዋናው ነጥብ፦ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው የሚገኙ ሰዎች በስብሰባው የሚደሰቱ ከመሆኑም ሌላ የበለጠ ጥቅም ያገኛሉ!

2. በጥሞና አዳምጥ

ቁልፍ ጥቅስ፦ “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ።”​—ሉቃስ 8:18

ብዙ ሰዎች፣ ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ ካዳመጡት ነገር መካከል 60 በመቶ የሚሆነውን እንደሚረሱት ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ገንዘብህ በዚህ ፍጥነት እየጠፋ እንደሆነ ብታውቅ ሁኔታውን ለማስተካከል አንድ ነገር አታደርግም?

ጠቃሚ ምክር፦ በስብሰባ ላይ ከወላጆችህ ጋር ሆነህ ፊት ተቀመጥ፤ እንዲህ ማድረግህ ትኩረትህ እንዳይከፋፈል ይረዳሃል። ንግግር ሲሰጥ ማስታወሻ ያዝ። ሰዎች ትምህርት የሚቀስሙበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም ማስታወሻ መያዝ ትኩረትህ በተናጋሪው ላይ እንዲሆን የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ነጥቦቹን ለመከለስ በጣም ይጠቅምሃል።

“በስብሰባዎች ላይ በጥሞና ማዳመጥ በጣም ያስቸግረኝ የነበረ ቢሆንም አሁን ተሻሽያለሁ። እዚያ የተገኘሁበትን ምክንያት ለማስታወስ ጥረት አደርጋለሁ። ስብሰባ መሄድ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ መሄድ ያለ በዘልማድ የሚከናወን የአምልኮ ሥርዓት አይደለም። ወደ ስብሰባዎች የምሄደው አምላክን ለማምለክና ለመማር ሲሆን እዚያም በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ የማደርገው ትምህርት አገኛለሁ።”​ካትሊን

ዋናው ነጥብ፦ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ በጥሞና አለማዳመጥ ድግስ ቤት ሄዶ ምንም ሳይቀምሱ እንደ መምጣት ነው።

3. ተሳትፎ አድርግ

ቁልፍ ጥቅስ፦ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም እርስ በእርሱ አንዱ ከሌላው ይማራል።”​—ምሳሌ 27:17 የ1980 ትርጉም

ወጣት እንደመሆንህ መጠን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጠቃሚ ድርሻ ልታበረክት ትችላለህ። በስብሰባዎች ላይ መገኘትህና ተሳትፎ ማድረግህ ያለውን ጠቀሜታ አቅልለህ አትመልከት፤ በጥያቄና መልስ በሚቀርበው የስብሰባው ክፍል ላይ ሐሳብ በመስጠትም ይሁን ከእምነት አጋሮችህ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ትችላለህ።

ጠቃሚ ምክር፦ በጥያቄና መልስ በሚቀርብ ክፍል ላይ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሐሳብ የመስጠት ግብ ይኑርህ። ከስብሰባ በፊት፣ ስብሰባው በሚካሄድበት ጊዜ ወይም ካበቃ በኋላ የሚከናወኑ እንደ ጽዳት ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት ራስህን በፈቃደኝነት አቅርብ። አጋጣሚ አግኝተህ አዋርተሃቸው ከማታውቅ የጉባኤው አባላት ጋር ለመጨዋወት ጥረት አድርግ።

“በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሳለሁ በስብሰባዎች ላይ ማይክሮፎን በማዞርና መድረኩን በማስተካከል እገዛ ማድረግ ጀመርኩ። እነዚህን ኃላፊነቶች ማግኘቴ ተፈላጊ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደረገኝ ከመሆኑም በላይ ምንጊዜም ከስብሰባ እንዳልቀርና በሰዓቱ ለመድረስ እንድጣጣር አነሳስቶኛል። ይህም ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ ፍቅር እንዲኖረኝ ረድቶኛል።”​ሚልዝ

ዋናው ነጥብ፦ ጉባኤ ሄደህ እጅህን አጣጥፈህ ከመቀመጥ ይልቅ ተሳትፎ አድርግ! ምንጊዜም ቢሆን ተመልካች ብቻ ከመሆን ይልቅ ተሳታፊ መሆን ይበልጥ ይክሳል።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን በእንግሊዝኛ ማግኘት ይቻላል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ተጋብዘሃል!

● ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ?

● የተሻልክ ሰው መሆን ትሻለህ?

● ጥሩ ጓደኞች ማግኘት ትፈልጋለህ?

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት የሚያስችልህ ከመሆኑም ሌላ በርካታ ጥቅሞች አሉት! የይሖዋ ምሥክሮች በሳምንት ሁለት ጊዜ በመንግሥት አዳራሻቸው ውስጥ ለአምልኮ ይሰበሰባሉ። ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም፤ ማንኛውም ሰው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችላል።

ይህ ግብዣ አያምልጥህ! የመንግሥት አዳራሾች ከዚህ በፊት ካየሃቸው ሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች የተለዩ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለሚገኘው ትምህርት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን አንተም የተሻለ ሕይወት መምራት እንድትችል የአምላክ ቃል እንዴት እንደሚረዳህ ትማራለህ!​—ዘዳግም 31:12፤ ኢሳይያስ 48:17

ሳይ​—መጀመሪያ ወደ መንግሥት አዳራሹ በሄድኩበት ጊዜ በአዳራሹ ውስጥ ምስሎች አለመኖራቸው፣ እንደ ቄስ የለበሰ ሰው አለማየቴ እንዲሁም ገንዘብ እንድሰጥ አለመጠየቄ አስገርሞኝ ነበር። ሁሉም ሞቅ ባለ ሁኔታ ስለተቀበሉኝ የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ። በስብሰባዎቹ ላይ የቀረበው ትምህርት ለመረዳት ቀላልና አሳማኝ ነበር። ስፈልገው የኖርኩት እውነት ይህ ነው!

ዴያኒራ​—የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጉት ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ የሄድኩት በ14 ዓመቴ ነበር። ሁሉም ሰው ጥሩ አቀባበል አደረገልኝ። ስብሰባው ላይ በመገኘቴ ሁሉም ተደስተው ነበር፤ ደግሞም ልባዊ አሳቢነት አሳይተውኛል። በዚያ ዕለት ያጋጠመኝ ነገር ስላስደሰተኝ ሌላ ጊዜ ተመልሼ ለመሄድ አልፈራሁም!

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በቀጣዩ የጉባኤ ስብሰባ ላይ የሚቀርበው ትምህርት ምን እንደሆነ ለማወቅ ፕሮግራሙን ተመልከት። ከፕሮግራሙ ላይ ትኩረትህን የሳበውን ክፍል ከመረጥክ በኋላ . . .

ቆርጠህ አውጣውና ኮፒ አድርገው

ስብሰባ ላይ ከመገኘትህ በፊት ከታች ያሉትን ባዶ ቦታዎች ሙላ።

የክፍሉ ርዕስ፦

․․․․․

ስለዚህ ርዕስ ማወቅ የምፈልገው ነገር፦

․․․․․

ክፍሉ ከቀረበ በኋላ ከታች ያሉትን ባዶ ቦታዎች ሙላ።

ያገኘሁት ትምህርት

․․․․․

በክፍሉ ላይ ያስደሰተኝና ተናጋሪውን ላመሰግንበት የምፈልገው ነጥብ፦

․․․․․