ንድፍ አውጪ አለው?
የዝሆን ኩምቢ
● ተመራማሪዎች የተሻለ ቅልጥፍናና የመተጣጠፍ ችሎታ ያለው የሮቦት እጅ በመሥራት ላይ ናቸው። ይህን መሣሪያ የፈለሰፈው ድርጅት የዲዛይን ክፍል ኃላፊ፣ አዲሱ እጅ “በአሁኑ ጊዜ በኢንዱስትሪ ውስጥ ካሉት መሣሪያዎች ሁሉ እጅግ የላቀ” እንደሆነ ገልጸዋል። ለዚህ መሣሪያ መነሻ የሆነው ሐሳብ የተገኘው ከየት ነው? ኃላፊው “ከዝሆን ኩምቢ አሠራር ነው” ብለዋል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንድ መቶ አርባ ኪሎ ግራም የሚያህል ክብደት ያለው የዝሆን ኩምቢ “ፕላኔታችን ላይ ካሉ መሣሪያዎች ሁሉ በሁለገብነቱና በጠቃሚነቱ ተወዳዳሪ” እንደሌለው ተደርጎ ተገልጿል። ብዙ ጥቅሞች ያሉት ይህ የሰውነት ክፍል እንደ አፍንጫ፣ እንደ ክንድ ወይም እንደ እጅ የሚያገለግል ከመሆኑም ሌላ ውኃ ለመምጠጥም ያስችላል። ዝሆን በኩምቢው መተንፈስ፣ ማሽተት፣ ውኃ መጠጣት እንዲሁም ነገሮችን ማንሳት አልፎ ተርፎም ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ ማውጣት ይችላል!
አገልግሎቱ ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። የዝሆን ኩምቢ ወደ የትኛውም አቅጣጫ ለመንቀሳቀስ እንዲችል የሚረዱ 40,000 ያህል የጡንቻ ሕብረ ሕዋሳት አሉት። በመሆኑም ዝሆን የኩምቢውን ጫፍ በመጠቀም ትንሽ ሳንቲም እንኳ ማንሳት ይችላል። እንዲሁም በኩምቢው ተጠቅሞ እስከ 270 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት ይሸከማል!
ተመራማሪዎች የዝሆን ኩምቢን ቅርጽና የመተጣጠፍ ችሎታ በመቅዳት ለቤት ውስጥም ሆነ ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ የተራቀቁ ሮቦቶች ለመሥራት ያስባሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ድርጅት ተወካይ እንዲህ ብለዋል፦ “ከተለመደው ሮቦት ጋር ሲወዳደር ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነና ሰዎች አደጋ ሳይደርስባቸው በማሽን ጥሩ አድርገው መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርግ የመጀመሪያውን መሣሪያ ፈልስፈናል።”
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የዝሆን ኩምቢ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?