ለፍትሕ መዛባት መንስኤ የሆኑ ነገሮች
ለፍትሕ መዛባት መንስኤ የሆኑ ነገሮች
ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁባቸውን አንዳንድ ባሕርያት በትክክል ጠቅሶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ . . . ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4
በዘመናችን እንዲህ ያሉ መጥፎ ዝንባሌዎችን የሚያንጸባርቁ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መብዛታቸውን የሚክድ ሰው አይኖርም። እነዚህ ባሕርያት ከሚገለጡባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ ስግብግብነት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ፀረ-ማኅበረሰብ የሆነ አመለካከት፣ ሙስናና ከፍተኛ የኑሮ ልዩነት ናቸው። እስቲ እነዚህን አንድ በአንድ እንመልከት።
ስግብግብነት፦ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” እንደሚሉ ያሉ ስግብግብነትን የሚያበረታቱ አባባሎችን ሰምተህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለእነዚህ አባባሎች ጆሮ መስጠት የለብህም። ምክንያቱም ስግብግብነት ጎጂ ነው! ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ከሒሳብ መዝገብ አያያዝ ጋር በተያያዘ እንዲያጭበረብሩ፣ በአቋራጭ ለመክበር እንዲሞክሩ እንዲሁም ሲበደሩም ሆነ ሲያበድሩ ይሉኝታ ቢስ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው በአብዛኛው ስግብግብነት ነው። ይህ ደግሞ እንደ ኢኮኖሚ ውድቀት የመሳሰሉ መጥፎ ውጤቶች ያስከተለ ሲሆን በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል። እርግጥ ከተጎጂዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ራሳቸው ስግብግቦች እንደሆኑ እሙን ነው። ይሁን እንጂ የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ደፋ ቀና የሚሉ ንጹሐን ሰዎችም የሚገኙበት ሲሆን ከእነሱም አንዳንዶቹ ቤታቸውንና ጡረታቸውን አጥተዋል።
ጭፍን ጥላቻ፦ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ሌሎችን ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የሚይዙ ሲሆን ዘራቸውን፣ የቆዳ ቀለማቸውን፣ ፆታቸውን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ወይም ሃይማኖታቸውን መሠረት በማድረግ መድሎ ይፈጽሙባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በተባበሩት መንግሥታት ሥር የተቋቋመ አንድ ኮሚቴ፣ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የምትኖር አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ሆስፒታል ስትደርስ ሕይወቷ ማለፉን ደርሶበታል፤ ይህች ሴት ለሞት የበቃችው በዘሯ ምክንያት እንዲሁም ከድሃና ዝቅተኛ ተደርጎ ከሚቆጠር የኅብረተሰብ ክፍል የመጣች በመሆኗ በጤና ጣቢያ ውስጥ ተገቢውን እርዳታ ስላላገኘች እንደሆነ ኮሚቴው ገልጿል። እንዲያውም አንዳንዶች ጭፍን ጥላቻቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደ ዘር ምንጠራና ዘር ማጥፋት ያሉ ዘግናኝ ድርጊቶች ፈጽመዋል።
ፀረ-ማኅበረሰብ የሆነ አመለካከት፦ ሀንድቡክ ኦቭ አንቲሶሻል ቢሄቪየር የሚለውን መጽሐፍ ፍሬ ነገሮች የያዘ አንድ ጽሑፍ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ፀረ-ማኅበረሰብ የሆነ አመለካከት ባላቸው ሰዎች ምክንያት በየዓመቱ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ይበተናሉ፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ይበላሻል እንዲሁም በብዙ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ንብረት ይወድማል። በማኅበረሰባችን ውስጥ ዓመፅና ጠብ አጫሪነት በጣም የተስፋፉና ሥር የሰደዱ ከመሆናቸው የተነሳ ወደፊት የሚነሱ የታሪክ ምሁራን፣ የሃያኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ‘የሕዋ
ዘመን’ ወይም ‘የመረጃ ዘመን’ መባሉ ቀርቶ ‘የፀረ-ማኅበረሰብ ዘመን’ ይኸውም ኅብረተሰቡ በራሱ ላይ ጦርነት የከፈተበት ጊዜ ተብሎ መጠራት አለበት ቢሉ የሚገርም አይሆንም።” ይህ መጽሐፍ ከታተመ ከ1997 ወዲህም ቢሆን በሰዎች አመለካከትና ባሕርይ ላይ ምንም መሻሻል አልታየም።ሙስና፦ በደቡብ አፍሪካ የሚፈጸምን ሙስና አስመልክቶ የወጣ አንድ ዘገባ እንደጠቀሰው በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ፣ ለአንድ የክልሉ ጤና ቢሮ ከተመደበው 25.2 ቢሊዮን ራንድ (በወቅቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል) ውስጥ ከ81 በመቶ በላይ የሚሆነው ለታሰበው ዓላማ ሳይውል ቀርቷል። “በክልሉ ያሉትን ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮችና የጤና ጣቢያዎች ለመጠገን” መዋል የነበረበት ገንዘብ በተገቢው መንገድ ሳይሠራበት እንደቀረ ዘ ፐብሊክ ማኔጀር የተሰኘው መጽሔት ተናግሯል።
ከፍተኛ የኑሮ ልዩነት፦ በ2005፣ ከብሪታንያ ዓመታዊ ገቢ ውስጥ ወደ 30 በመቶ የሚጠጋው “5 በመቶ በሆኑት ሰዎች እጅ” እንደገባ ታይም መጽሔት ዘግቧል። በተመሳሳይም “ከአሜሪካ ገቢ ውስጥ ከ33 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚሄደው 5 በመቶ ወደሚሆኑ ሰዎች እጅ” እንደሆነ ይኸው መጽሔት ተናግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ በመላው ዓለም 1.4 ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከ1.25 የአሜሪካ ዶላር ባነሰ የቀን ገቢ የሚኖሩ ሲሆን በድህነት የተነሳ በየቀኑ 25,000 ሕፃናት ይሞታሉ።
የፍትሕ መዛባት መፍትሔ አለው?
በ1987 የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰብ በ1990 በአውስትራሊያ በድህነት የሚኖር አንድም ሕፃን እንዳይኖር ለማድረግ ግብ አውጥተው ነበር። ይሁንና ይህ ግባቸው ፈጽሞ አልተሳካም። እንዲያውም በኋላ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ግብ በማውጣታቸው ተጸጽተዋል።
አዎን፣ አንድ ግለሰብ ሥልጣን ወይም ሀብት አሊያም ተሰሚነት ቢኖረውም ሰው ምንጊዜም ሰው ነው፤ በመሆኑም የፍትሕ መዛባትን ማስወገድ አይችልም። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎችም እንኳ የፍትሕ መዛባት ይደርስባቸዋል፣ ያረጃሉ እንዲሁም ይሞታሉ። እነዚህ እውነታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን የሚከተሉትን ሁለት ጥቅሶች ያስታውሱናል፦
‘ሰው አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም።’—ኤርምያስ 10:23
“በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ።”—መዝሙር 146:3
እነዚህ ጥበብ ያዘሉ ጥቅሶች እውነት መሆናቸውን አምነን የምንቀበል ከሆነ የሰው ጥረቶች መና ሲቀሩ ግራ አንጋባም። ታዲያ የፍትሕ መዛባት መፍትሔ አይኖረውም ማለት ነው? በጭራሽ! ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ በመጨረሻው ላይ እንደምንመለከተው እውነተኛ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም በቅርቡ ይመጣል። እስከዚያው ድረስ ግን የበኩላችንን ማድረግ እንችላለን። በሌላ አባባል የሚከተሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ራሳችንን መመርመር እንችላለን፦ ‘ከሰዎች ጋር ባለኝ ግንኙነት ይበልጥ ፍትሐዊ መሆን እችላለሁ? በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገኝ አንዳንድ መስኮች አሉ?’ እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ጥሩ ማብራሪያ ማግኘት እንችላለን።
[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሀ. ቻይና ውስጥ ፖሊሶች፣ በጎሳ ግጭት የተካፈለን አንድ ሰው ሲያስሩ
ለ. በለንደን፣ እንግሊዝ ውስጥ ሰዎች ዘረፋ ሲያካሂዱና ንብረት ሲያወድሙ
ሐ. ሩዋንዳ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ሰፈር የሚገኙ ሰዎች እጅግ አስከፊ በሆነ ድህነት ውስጥ ይኖራሉ
[የሥዕሉ ምንጭ]
Top left: © Adam Dean/Panos Pictures; top center: © Matthew Aslett/Demotix/CORBIS; top right: © David Turnley/CORBIS