በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይበልጥ ፍትሐዊ መሆን የሚቻልባቸው መንገዶች

ይበልጥ ፍትሐዊ መሆን የሚቻልባቸው መንገዶች

ይበልጥ ፍትሐዊ መሆን የሚቻልባቸው መንገዶች

ፈጣሪያችን ደስተኞች እንድንሆን፣ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረንና ሌሎችን ለማስደሰት የበኩላችንን ሚና እንድንጫወት ይፈልጋል። በመሆኑም ‘ፍትሕን እንድናደርግ እና ምሕረትን እንድንወድድ’ ጠይቆናል። (ሚክያስ 6:8) ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ፍትሐዊ እንዳንሆን እንቅፋት የሚሆኑብንን ዝንባሌዎች ለማስወገድ የሚረዱንን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ለማድረግ ሊረዳን የሚችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ስግብግብነትን ማሸነፍ፦ ስግብግብነትን ለማሸነፍ የሚረዳን ከሁሉ የላቀው መንገድ ፍቅርን ማዳበር ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በስሜት የሚመራን ቅርርብ ወይም በተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚፈጠርን መሳሳብ የሚያመለክት ሳይሆን ራስን ለሌሎች መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4, 5 ስለዚህ ዓይነቱ ፍቅር ሲናገር “ደግ ነው” እንዲሁም “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” ይላል። ከዚህም በላይ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በቤተሰብና በጓደኞች መካከል ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ኢየሱስ “የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ?” በማለት ጥያቄ ካቀረበ በኋላ አምላክን የማያውቁ ሰዎችም እንኳ የሚወዷቸውን እንደሚወዱ ተናግሯል።​—ማቴዎስ 5:46

ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ፦ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 “አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” ይላል። አምላክ ሰዎች መዳን እንዲያገኙ የሚያደርገው ዘራቸውን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ወይም ፆታቸውን መሠረት በማድረግ አይደለም። በእሱ አመለካከት “በአይሁዳዊና በግሪካዊ፣ በባሪያና በነፃ ሰው እንዲሁም በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም።” (ገላትያ 3:28) በእርግጥም አምላክን በመምሰል ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ እንችላለን። በዩናይትድ ስቴትስ ትኖር የነበረችውን ዶረቲን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

ዶረቲ የዘር ጥላቻ በጣም ስላንገሸገሻት በጥቁር ሕዝቦች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ለማስወገድ በትጥቅ ትግል ውስጥ መካፈል ፈለገች። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ በተገኘች ጊዜ ጥቁሮችም ሆኑ ነጮች ባደረጉላት ሞቅ ያለ አቀባበል በጣም ተገረመች። ብዙም ሳይቆይ የሰዎችን ውስጣዊ ማንነት መቀየር የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ ተገነዘበች። ነጮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩዋት እውነተኛ ፍቅር ልቧ በጥልቅ በመነካቱ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፤ ፍቅር ባያሳዩዋት ኖሮ እነዚህን ሰዎች በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ከመግደል እንደማትመለስ ተናግራለች።

ፀረ-ማኅበረሰብ የሆኑ አመለካከቶችን ማሸነፍ፦ ከጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች መካከል አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ከመሆናቸው በፊት ሰካራሞች፣ ቀማኞች፣ ፈንጠዝያ የሚወዱና ተሳዳቢዎች ነበሩ። ሆኖም በአምላክ እርዳታ እነዚህን መጥፎ ባሕርያት አስወግደው በምትኩ ፍቅርን፣ ደግነትንና ጥሩነትን ማንጸባረቅ ችለዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:9-11፤ ገላትያ 5:22) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አምላክ በመመለስ በሕይወታቸው ውስጥ አስደናቂ ለውጦችን አድርገዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በአዘርባጃን የሚኖረው ፊሮዲን ነው።

ፊሮዲን ያደገው ወላጅ አልባ ሕፃናትን በሚንከባከብ ድርጅት ውስጥ ሲሆን በዚያ ሳለ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ልጆች ጋር ይደባደብ ነበር። ትልቅ ሰው ሲሆን የጨበጣ ውጊያ አስተማሪ ሆነ። ፊሮዲን “ለሌሎች አክብሮት የሌለኝ፣ ጨካኝና ዓመፀኛ ነበርኩ” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ዜራ ምግብ ስታቀራርብ አንድ ነገር ከረሳች ሌላው ቀርቶ ስቴኪኒ እንኳ ከጎደለ እመታት ነበር። እንዲሁም በመንገድ ላይ አብረን ስንሄድ ማንም ሰው ቀና ብሎ ካያት እደበድበው ነበር!”

ይሁንና ፊሮዲን ኢየሱስ፣ ሰቅለው የገደሉትን ወታደሮች አምላክ ይቅር እንዲላቸው እንደጸለየ ሲያውቅ ልቡ ተነካ። (ሉቃስ 23:34) ‘እንዲህ ያለ ጸሎት ሊያቀርብ የሚችለው የአምላክ ልጅ ብቻ ነው’ ብሎ አሰበ። ከዚያ በኋላ አምላክን መፈለግ ጀመረ። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ እሱን ለመርዳትና በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ያቀረቡለትን ግብዣ በደስታ ተቀበለ። ብዙም ሳይቆይ ባሕርይው መሻሻል ጀመረ። ዜራን ደግነት በተሞላበት መንገድ መያዝ በመጀመሩ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነች። በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆነው በሰላም እየኖሩ ነው።

እርግጥ ነው፣ እኛ በግላችን የምናደርገው ለውጥ መላውን ዓለም ይቀይረዋል ማለት አይደለም። ይሁንና አምላክ አዲስና ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት ዓላማ እንዳለው ብታውቅ ምን ይሰማሃል? ደግሞም ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው! በተጨማሪም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-4 ላይ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች ስለሚኖራቸው ባሕርይ በግልጽ የሚናገር ትንቢት እንደሚገኝ ቀደም ባለው ርዕሰ መግቢያ ላይ ተመልክተን ነበር። እንደ ሌሎቹ ሁሉ ይህ ትንቢትም አንድም ሳይቀር ተፈጽሟል። በመሆኑም አምላክ ማንኛውንም የፍትሕ መዛባት ለማስወገድ የገባውን ቃል ማመን ሞኝነት አይደለም። አምላክ ይህን ዓላማውን ከግቡ ያደርሰዋል። እንዴት?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ፍትሕን ለማግኘት የተደረገ ጥረት

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ሃይዲ “ዘረኝነት፣ ጦርነት፣ ድህነትና ሌሎችም ፍትሕ የጎደላቸው ድርጊቶች በጣም ስለሚያበሳጩኝ በዚህ ረገድ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት አደርግ ነበር” በማለት ታስታውሳለች። “የሰብዓዊ መብት ንቅናቄ ከሚያካሂዱ ሰዎች ጋር እሠራ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆንኩ፤ ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ እውነተኛ ፍትሕ ማስፈን እንደማይቻል ተረዳሁ።

“ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተሰማኝ፤ ለዚህም ደግሞ የሂፒዎች ንቅናቄ ተስፋ ሰጪ መስሎ ታየኝ። ይህም ቢሆን እንዳሰብኩት ሆኖ አላገኘሁትም። ብዙዎቹ ሂፒዎች ሥርዓቱን ለመለወጥ ከመታገል ይልቅ ትኩረታቸው ያረፈው በፆታ ብልግና፣ በዕፅና በሮክ ሙዚቃ ላይ እንደሆነ ተገነዘብኩ፤ በዚህም የተነሳ በጥልቅ ሐዘን ተዋጥኩ። ከጊዜ በኋላ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘሁ፤ እሷም አምላክ ወደፊት ምን ዓይነት ለውጦችን ለማምጣት ቃል እንደገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየችኝ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ የሰዎችን እንባ ከፊታቸው ላይ እንደሚጠርግ እንዲሁም ሐዘንን፣ ጩኸትንና ሥቃይን እንደሚያስወግድ የሚናገረውን በራእይ 21:3, 4 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አሳየችኝ፤ ለእነዚህ ነገሮች መንስኤ የሆነው ነገር ደግሞ በአብዛኛው የፍትሕ መጓደል ነው። ‘እነዚህ ተስፋዎች በእርግጥ ይፈጸማሉ?’ ብዬ ራሴን ጠየቅሁ።

“መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስላለው ኃይልና ስለ ፍቅሩ የሚናገረውን ሳነብ እንዲሁም በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ፍቅር ስመለከት አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ ሆንኩ። አሁን ተስፋዎቹ የሚፈጸሙበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።”

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጭፍን ጥላቻ የሚወገደው አምላክን በመምሰል ፍቅር ስናሳይ ነው

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፊሮዲን ከባለቤቱ ከዜራ ጋር