በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሙታን በሕይወት ያሉትን ሊረዱ ይችላሉ?

ሙታን በሕይወት ያሉትን ሊረዱ ይችላሉ?

ሰዎች ለብዙ ዘመናት፣ ሙታን በሕይወት ላሉ ሰዎች መመሪያ መስጠት ይችላሉ ብለው ሲያምኑ ኖረዋል። ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር ስለ ኦዲሲዩስ (ዩሊሲዝ ተብሎም ይጠራል) የጻፈው አንድ መጣጥፍ ሰዎች ከረጅም ጊዜ አንስቶ እንዲህ ዓይነት እምነት እንደነበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በሆሜር ሥራ ላይ የተጠቀሰው ይህ ታዋቂ ጀግና፣ ኢታካ በምትባለው ደሴት ወደሚገኘው ቤቱ የሚወስደውን መንገድ እንዲጠቁመው ሞቶ የነበረን አንድ ባለ ራእይ ለመጠየቅ ወደ ሙታን ዓለም አደገኛ ጉዞ እንዳደረገ ተገልጿል።

ብዙ ሰዎች፣ ለሚያስጨንቋቸው ጥያቄዎች ሙታን መልስ እንደሚሰጧቸው ተስፋ በማድረግ መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቀዋል፤ በቅድመ አያቶቻቸው መቃብር ውስጥ ተኝተዋል፤ ወይም መናፍስታዊ የሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶችን አካሂደዋል። ይሁንና ከሙታን መመሪያ ማግኘት ይቻላል?

በጣም የተስፋፋ ልማድ

በዓለም ላይ ከሚገኙት ዋና ዋና ሃይማኖቶች መካከል ብዙዎቹ ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገር እንደሚቻል ያስተምራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪልጅን “ሙታንን ማነጋገር ማለትም ምትሃታዊ በሆነ መንገድ የሟቹ ነፍስ እንዲገለጥ ማድረግ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች አንዱ” እንደሆነ ይናገራል። አክሎም ይህ ልማድ “በጣም የተስፋፋ” እንደሆነ ገልጿል። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይህን ሲያረጋግጥ እንዲህ ብሏል፦ “በተለያዩ መንገዶች የሚከናወነው ሙታንን የማነጋገር ልማድ በዓለም ዙሪያ የተስፋፋ ድርጊት ነበር።” በመሆኑም በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች በመንፈሳዊው ዓለም ካሉ አካላት አንዳንድ ነገሮች ለማወቅ መሞከራቸው የሚገርም አይደለም!

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደጠቀሰው እንዲህ ያለውን ከሙታን ጋር የሚደረግ ግንኙነት “ቤተ ክርስቲያኒቷ አጥብቃ ብታወግዘውም ይህ ልማድ በመካከለኛው ዘመንና በተሃድሶው ዘመን እንደነበር የሚጠቁሙ በርካታ ጽሑፎች” አሉ። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ሙታንን መጠየቅ ይኖርብሃል?

በጥንት ጊዜ፣ ይሖዋ አምላክ “ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 18:9-13) ይሖዋ እንዲህ ያለ ትእዛዝ የሰጠው ለምንድን ነው? በሕይወት ያሉ ሰዎች ሙታንን ማነጋገር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ አፍቃሪ የሆነው አምላክ እንዲህ ያለውን የሐሳብ ልውውጥ እንዳናደርግ ይከለክለን ነበር? በፍጹም! እንደ እውነቱ ከሆነ ከሙታን ጋር መነጋገር ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?

ሙታን ምንም እንደማያውቁ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ተጠቅሷል። ለምሳሌ፣ መክብብ 9:5 “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ይላል። መዝሙር 146:3, 4 ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።” በተመሳሳይም ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ሙታን ሲናገር “መንፈሳቸው ተነሥቶ አይመጣም” ብሏል።​—ኢሳይያስ 26:14

ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በመናፍስታዊ ድርጊቶች አማካኝነት በሞት ከተለዩዋቸው የሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደተገናኙ ይናገራሉ። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች በጣም የተለመዱ ናቸው፤ በመሆኑም ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊው ዓለም ከሚኖር የሆነ አካል ጋር እንደተነጋገሩ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ካየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች የተነጋገሩት ከሙታን ጋር አይደለም። ታዲያ የተነጋገሩት ከማን ጋር ነው?

የሚነጋገሩት ከማን ጋር ነው?

የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በፈጣሪያቸው ላይ ዓምፀው አጋንንት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:1-5፤ ይሁዳ 6, 7) እነዚህ አጋንንት፣ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሕይወት ይቀጥላሉ የሚለውን የሐሰት ትምህርት ያስፋፋሉ። አጋንንት ከመንፈሳዊው ዓለም የመጡ የሙታን መናፍስትን መስለው በመቅረብ በሕይወት ካሉት ጋር ስለሚነጋገሩ ሰዎች እስካሁን ድረስ በዚህ የሐሰት ትምህርት ያምናሉ።

የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ታዛዥ ባለመሆኑ የተነሳ ይሖዋ ሲተወው ምክር ለማግኘት፣ ሞቶ ከነበረው ከነቢዩ ሳሙኤል ጋር በመናፍስት ጠሪ አማካኝነት ለመነጋገር ሙከራ እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሳኦል ከመንፈሳዊው ዓለም መልእክት የተቀበለ ቢሆንም መልእክቱ የመጣው ከሳሙኤል አልነበረም። ሳሙኤል በሕይወት እያለ ንጉሡን ለማየት ፈቃደኛ አልነበረም፤ እንዲሁም መናፍስት ጠሪዎችን ይቃወም ነበር። በመሆኑም ሳኦል መልእክት የተቀበለው ሳሙኤልን መስሎ ከቀረበ አንድ ጋኔን ነበር።​—1 ሳሙኤል 28:3-20

አጋንንት የአምላክ ጠላቶች ስለሆኑ ከእነሱ ጋር መገናኘት አደገኛ ነው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ” የሚል ትእዛዝ ይሰጣል። (ዘሌዋውያን 19:31) ዘዳግም 18:11, 12 “ሙት አነጋጋሪ . . . በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። ይሖዋ ንጉሥ ሳኦልን በሞት የቀጣው ታማኝ አለመሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ጥፋቶችን በመፈጸሙ ነው፤ ከእነዚህ ድርጊቶች አንዱ ደግሞ ‘ከሙታን ጠሪ ምክር መጠየቁ’ ነው።​—1 ዜና መዋዕል 10:13, 14

ታዲያ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ወይም ውሳኔ የሚያሻቸው ነገሮች ቢያጋጥሙህና መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ብትፈልግ ወደ ማን ዘወር ማለት ይኖርብሃል? ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ አምላክን ታላቅ “አስተማሪ” በማለት ይገልጹታል። አንተም ሆንክ የምትወዳቸው ሰዎች የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለማግኘትና ምክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት የምታደርጉ ከሆነ ጆሯችሁ ከኋላ “‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ” የሚሰማ ያህል ይሆናል። (ኢሳይያስ 30:20, 21) እውነት ነው፣ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ቃል በቃል የእውነተኛውን አምላክ ድምፅ እንሰማለን ብለው አይጠብቁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ የሚመራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንደሆነ ይገነዘባሉ። በእርግጥም፣ ይሖዋ ‘እኔ እንድመራችሁ ፍቀዱልኝ’ በማለት እየተናገረ ነው ሊባል ይችላል።

ይህን አስተውለኸዋል?

● ከሙታን ጋር ለመነጋገር የሚደረገውን ሙከራ አምላክ እንዴት ይመለከተዋል?​—ዘዳግም 18:9-13

● ሙታን፣ በሕይወት ላሉት ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን ሊያሳውቋቸው ይችላሉ? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?​—መክብብ 9:5

● አስተማማኝ መመሪያ ለማግኘት ወደ ማን ዘወር ማለት እንችላለን?​—ኢሳይያስ 30:20, 21