የወጣቶች ጥያቄ
ቅርርባችን ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ነው? ክፍል 1
ይህን ርዕስ ስታነብ ወደ አእምሮህ የመጣ ሰው አለ?
አዎ → በዚህ ርዕስ ሥር ያለውን ሐሳብ ዛሬ ነገ ሳትል አንብበው። የያዘው ቁም ነገር ከምታስበው በላይ ያስፈልግህ ይሆናል።
አይ → ያም ቢሆን ከታች ያሉትን ነጥቦች አንብባቸው። ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለህ ቅርርብ ግልጽነት የሚንጸባረቅበትና ችግሮች የማያስከትል እንዲሆን ይረዳሃል።
እውነት ወይም ሐሰት በል
ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ እስክሆን ድረስ ተቃራኒ ፆታ ያላቸው ጓደኞች ሊኖሩኝ አይገባም።
․․․․․ እውነት ․․․․․ ሐሰት
እስቲ ይህን አስብ፦ ኢየሱስ፣ የማግባት እቅድ ባይኖረውም ሴት ጓደኞች ነበሩት። (ማቴዎስ 12:46-50፤ ሉቃስ 8:1-3) ነጠላ የነበረው ጢሞቴዎስም ከወንዶች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሴቶች ጋርም ይቀራረብ የነበረ ይመስላል፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ “ወጣት ሴቶችን . . . እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው” ብሎታል።—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
ጢሞቴዎስ በተለያዩ ጉባኤዎች በሚያገለግልበት ጊዜ በርካታ ወጣት ሴቶችን እንደሚያገኝ ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። (ማርቆስ 10:29, 30) ታዲያ ጢሞቴዎስ ከእነሱ ጋር መቀራረቡ ስህተት ይሆን ነበር? አይሆንም። ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ በዚያ ወቅት የማግባት እቅድ ስላልነበረው በቅርርባቸው ረገድ ገደብ ማበጀት ያስፈልገው ነበር፤ እንዲህ ማድረጉ በመካከላቸው መሳሳብ እንዳይፈጠር ወይም እነዚያን ወጣት ሴቶች በማሽኮርመም ስሜታቸውን የሚጎዳ ነገር እንዳያደርግ ጥበቃ ይሆናል።—ሉቃስ 6:31
አንተስ? ለማግባት ዝግጁ ነህ?
መልስህ አዎ ከሆነ ⇨ ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ሰዎች ጋር የምትመሠርተው ጓደኝነት የዕድሜ ልክ አጋር ለማግኘት ያስችልህ ይሆናል።—ምሳሌ 18:22፤ 31:10
መልስህ አይ ከሆነ ⇨ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለሚኖርህ ቅርርብ ገደብ ማበጀት ያስፈልግሃል። (ኤርምያስ 17:9) ‘ይህን ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም’ ትል ይሆናል። ደግሞም አልተሳሳትክም! “ጓደኛሞች ብቻ ሆኖ መቀጠል ከባድ ነው” በማለት የ18 ዓመቷ ኒያ * ትናገራለች። “ምን ዓይነት ድንበር ማበጀት እንዳለባችሁ ማወቅ አስቸጋሪ ነው።”
ይሁንና መጀመሪያውኑስ ቢሆን ገደብ ማበጀት የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ካላደረግህ ራስህን አሊያም ሌሎችን ልትጎዳ ትችላለህ። ይህን የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
የሕይወት እውነታ፦ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም ብትቀራረብ ከሁለት አንዳችሁ ስሜታችሁ መጎዳቱ አይቀርም። የ19 ዓመቷ ኬሊ እንዲህ ያለ ሁኔታ “ሁለት ጊዜ” እንዳጋጠማት ትናገራለች። “በአንድ ወቅት ከአንድ ልጅ ጋር ፍቅር ይዞኝ የነበረ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ልጅ ወዶኝ ነበር። በሁለቱም ጊዜያት አንደኛው ወገን ስሜቱ ተጎድቷል፤ ይህ ሁኔታ በእኔ ላይ የተወው የስሜት ጠባሳ እስካሁን አልጠፋም።”
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦
● ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ ተገቢ የሚሆነው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ነው? ተገቢ የማይሆነውስ?
● በቡድን ሆናችሁ በምትጫወቱበት ጊዜም እንኳ፣ አዘውትሮ ከአንድ ሰው ጋር ነጠል ብሎ መጨዋወት ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው? ሌላው ወገን ምን ስሜት ሊያድርበት ይችላል? አንተስ ምን ስሜት ሊፈጠርብህ ይችላል?
“‘ከእሱ ጋር ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ነገር የለንም። እንደ ወንድሜ እኮ ነው የማየው’ በማለት ራሴን ያታለልኩባቸው ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ ከእኔ ጋር ብቻ መሆን ያለበት ይመስል ከሌላ ሴት ጋር ሳየው ቅር ይለኛል።”—ዴኒዝ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ብልኅ ሰው መከራ ሲመጣ አይቶ ይሸሻል፤ ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ ከገባ በኋላ እንደገና ይጸጸታል።”—ምሳሌ 22:3 የ1980 ትርጉም
የሕይወት እውነታ፦ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም ብትቀራረብ ጥሩ ጓደኛህን ታጣለህ። የ16 ዓመቷ ካቲ እንዲህ ብላለች፦ “ከአንድ ልጅ ጋር በስልክ የጽሑፍ መልእክት እንለዋወጥ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ለእኔ የተለየ ስሜት እንዳለው የሚጠቁሙ መልእክቶችን መላክ ጀመረ፤ በየቀኑ ማለት ይቻላል መልእክት እንለዋወጥ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን በጣም እንደወደደኝና ከጓደኝነት ያለፈ ግንኙነት ቢኖረን ደስ እንደሚለው ገለጸልኝ። እኔ ግን ልጁን ፈጽሞ በዚህ መንገድ አላስበውም። ይህን ከነገርኩት በኋላ እንደ ድሮው ማውራታችን የቀረ ሲሆን ጓደኝነታችንም አከተመለት።”
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦
● ካቲ በገለጸችው ሁኔታ የተጎዳው ማን ነው? ለምንስ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ሁለቱም ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ነበር? ከሆነ ምን?
● በስልክ የጽሑፍ መልእክት በምትለዋወጥበት ጊዜ ከጓደኝነት ያለፈ ግንኙነት እንዲኖራችሁ እንደምትፈልግ የሚጠቁም ሐሳብ ሳይታወቅህ ልታስተላልፍ የምትችለው ምን ካደረግህ ነው?
“ከአንድ ልጅ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ብፈልግም እንዲህ ከማድረግ የተቆጠብኩባቸው ጊዜያት አሉ። ወንዶች ጥሩ ጓደኛ ሊሆኑ ቢችሉም ከዚያ ያለፈ ግንኙነት በመፍጠር ጓደኝነታችንን ማጣት አልፈልግም።”—ሎራ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል።”—ምሳሌ 14:15
ዋናው ነጥብ፦ ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ በራሱ ስህተት አይደለም። ሆኖም ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ ካልሆንክ በዚህ ረገድ ገደብ ማበጀት ያስፈልግሃል።
በሚቀጥለው እትም የሚወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” . . .
የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም መቀራረብ መጥፎ ስም ሊያሰጥህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን በእንግሊዝኛ ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?
እውነተኛ ታሪክ፦ “ከ1,500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ለሚኖር አንድ ጓደኛዬ በስልክ የጽሑፍ መልእክት ላክሁለት። ከዚያ በኋላ በሳምንት አንድ ጊዜ ያህል የጽሑፍ መልእክት እንለዋወጥ ነበር። ለእሱ ምንም የፍቅር ስሜት የለኝም፤ እሱም ቢሆን ስለ እኔ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ይኖረዋል ብዬ አላሰብኩም ነበር። አንድ ቀን ‘ቆንጅዬ፣ ሰላም ነው? ናፍቀሽኛል! ምን እያደረግሽ ነው?’ ብሎ ጻፈልኝ። ክው ብዬ ቀረሁ! ከጓደኝነት ባለፈ ከእሱ ጋር የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ እንደሌለኝ ገለጽኩለት። እሱም ‘ይሁንልሽ’ ብሎ ጻፈልኝ። ከዚያ በኋላ አንድም መልእክት ልኮልኝ አያውቅም።”—ጃኔት
● ከተቃራኒ ፆታ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ዝግጁ ሳትሆኑ ወይም እንዲህ የማድረግ ሐሳብ ሳይኖራችሁ ጃኔት የደረሳት ዓይነት መልእክት ቢደርሳችሁ ምን ይሰማችኋል?
● ወንድ ከሆንክ ለጃኔት የተላኩላት መልእክቶች ተገቢ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
● በስልክ የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ በአካል ከመገናኘት ይልቅ የፍቅር ስሜት የመፈጠሩን አጋጣሚ የሚያሰፋው ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?
“ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች” በሚሉት ንዑስ ርዕሶች ሥር ለቀረቡት ጥያቄዎች ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ወላጆችህን ጠይቃቸው። እነሱ የሰጡህ አስተያየት ከአንተ የተለየ ነው? ከሆነ እንዴት? እነሱ የሰጡት አስተያየት ምን ጥቅም ያለው ይመስልሃል?—ምሳሌ 11:14
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እኩዮችህ ምን ይላሉ?
ጆሹዋ—ከአንድ ሰው ጋር ብዙ ጊዜ የምታሳልፉ ከሆነ መዋደዳችሁ የማይቀር ነው።
ናታሻ—ከአንድ ሰው ጋር ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ባታስቡም ከዚህ ግለሰብ ጋር አዘውትራችሁ ጊዜ የምታሳልፉ ከሆነ ከሁለት አንዳችሁ አሊያም ሁለታችሁም ፍቅር ሊይዛችሁ ይችላል።
ኬልሲ—መጀመሪያ ላይ ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ቅርርብ ባይኖራችሁም እንኳ አብራችሁ ብዙ ጊዜ የምታሳልፉ ከሆነ ሳታስቡት ስሜታችሁ ሊለወጥ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጓደኛሞች ሊሆኑ አይችሉም ማለት ባይሆንም ይህን ማድረግ ብስለትና ማስተዋል ይጠይቃል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም መቀራረብ ጣጣ አለው