ባቲክ—የሚያምር የኢንዶኔዥያ ጨርቅ
ባቲክ—የሚያምር የኢንዶኔዥያ ጨርቅ
የባቲክ ጨርቅ መመረት ከጀመረ ብዙ ዘመን ቢሆነውም አሁንም ጊዜ አላለፈበትም። ከተራው አንስቶ ከፍ ያለ ማዕረግ እስካለው ሰው ድረስ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ይለብሰዋል። በጣም የሚያምር፣ በቀለማት ያሸበረቀና የተለያየ ንድፍ ያለው ነው። ለመሆኑ ባቲክ ምንድን ነው? የሚሠራው እንዴት ነው? መሠራት የተጀመረውስ የት ነው? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለምን ዓላማ ይጠቀሙበታል?
የባቲክ ጨርቅ አሠራር ጥንታዊ ነው። በባቲክ ጨርቅ ላይ ያሉት ንድፎች የሚዘጋጁት ለየት ያለ የማቅለም ዘዴ በመጠቀም ሲሆን የዚህ ጨርቅ አሠራር ከኢንዶኔዥያውያን አኗኗርና ባሕል ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ከባቲክ ጋር የሚመሳሰሉ ጨርቆች በመላው ዓለም ተወዳጅ ናቸው።
የቀለምና የሰም ጣምራ ውጤት
አንድ የዕደ ጥበብ ባለሙያ የቀለጠ ሰም በተሞላ አነስተኛ የመዳብ መሣሪያ ተጠቅሞ በጣም ውስብስብ የሆነ ንድፍ ጨርቁ ላይ በእጁ ይሠራል። ሰሙ ሲደርቅ ጨርቁ ቀለም ይነከራል። በዚህ ጊዜ ሰሙ ያረፈበት ቦታ ቀለም ስለማይቀበል ሰሙ የተቀባባቸው ቦታዎች በሙሉ የጨርቁን የመጀመሪያ ቀለም እንደያዙ ይቀራሉ። ብዙውን ጊዜ ይህንን ሂደት ተከትሎ ጨርቁን በተለያዩ ቀለማት ደጋግሞ በማቅለም ጨርቁ የሚያምር ንድፍ እንዲኖረው ይደረጋል።
በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የባቲክ ሙያተኞች ሰሙን ጨርቅ ላይ ለመቀባት የተለያየ ዓይነት ንድፍ የተቀረጸባቸውን የመዳብ ማኅተሞች ይጠቀሙ ነበር። ይህ ዘዴ ንድፉን በእጅ ከመሥራት የበለጠ የሚያፈጥን ከመሆኑም በላይ አንድ ዓይነት ጌጥ ያላቸው ጨርቆችን በብዛት ለማምረት ያስችላል። በ20ኛው መቶ ዘመን ትላልቅ ፋብሪካዎች በማሽኖች ተጠቅመው የተለያዩ ንድፎችን ጨርቅ ላይ ማተም ጀመሩ። ዛሬም ቢሆን በእጅ የተሠራን ባቲክ ገበያ ላይ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም በአብዛኛው ገበያውን የተቆጣጠረው በፋብሪካ የሚመረተው ባቲክ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ባቲክ ለመሥራት የሚያገለግለው ከጥጥ ወይም ከሐር የተሠራ ጨርቅ ነው። እነዚህን ጨርቆች ለማቅለም የሚያገለግሉት ቀለማት ደግሞ የሚዘጋጁት በአካባቢው ከሚገኙ ቅጠሎች፣ እንጨቶች፣ የዛፍ ቅርፊቶችና ከተለያዩ ቅመማት ነው፤ እርግጥ ነው፣ ሰው ሠራሽ የሆኑ ቀለማት ጥቅም ላይ የሚውሉበት ጊዜም አለ። ሰዎች ንድፎችን ለመሥራት ሰም መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት ሙጫ፣ ሞራ ሌላው ቀርቶ ጭቃ ይጠቀሙ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በአብዛኛው ንድፍ ለማውጣት የሚጠቀሙት ሰው ሠራሽ ሰም ነው። ይሁን እንጂ ፓራፊንና የማር ሰፈፍ በመቀየጥ የሚዘጋጀውን ሰም ዛሬም ድረስ ይጠቀሙበታል።
ጥንታዊና ወደፊትም የሚቀጥል
ባቲክ መሠራት የተጀመረው መቼና የት እንደሆነ በትክክል መናገር አይቻልም። በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም ገደማ እንደተሠሩ የሚገመቱ የባቲክ ቁርጥራጮች በቻይና ተገኝተዋል። የባቲክ አሠራር ዘዴ በኢንዶኔዥያ የተጀመረው መቼ እንደሆነ በውል ባይታወቅም በ17ኛው መቶ ዘመን በኢንዶኔዥያ የባቲክ ጨርቅ የማስመጣትና የመላክ ንግድ ይካሄድ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ተገኝቷል።
ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ባቲክ ከፍተኛ ተወዳጅነት እያገኘ የመጣ ሲሆን የኢንዶኔዥያ መለያ እስከመሆን ደርሷል። ባቲክ በኢንዶኔዥያ ረጅም ታሪክ በማስቆጠሩና በአገሩ ባሕል ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደሩ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ2009 “የሰው ልጅ ባሕላዊ ቅርስ” ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጓል።
ከባቲክ የሚዘጋጁ ነገሮች
ባቲክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የራሱ የሆነ የአለባበስ፣ የአስተጣጠፍና የአሠራር ሥርዓት አለው፤ እርግጥ የአካባቢው እምነትና አንዳንድ አጉል አመለካከቶች በዚህ ባሕላዊ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ብዙዎቹ የኢንዶኔዥያ ግዛቶች የራሳቸው የሆነ የአቀላለምና ንድፍ የማውጣት ዘዴ አላቸው። ለምሳሌ በጃቫ ሰሜናዊ ዳርቻ የሚሠራው ባቲክ ደማቅ ቀለም ያለው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የአበቦች፣ የወፎችና የሌሎች እንስሳት ምስል ይሳልበታል። በማዕከላዊ ጃቫ የሚዘጋጀው ባቲክ ግን ደብዘዝ ያለ ቀለም ሲኖረው
የተለያዩ ቅርጾች ይሳሉበታል። እስካሁን በተመዘገበው መሠረት 3,000 ገደማ የባቲክ ንድፎች አሉ።በባቲክ ጨርቅ ከሚሠሩ ባሕላዊ ነገሮች መካከል አንዱ ሴሌንዳንግ ተብሎ የሚጠራው ሲሆን ትከሻ ላይ ጣል የሚደረግ ወይም ለዕቃ መያዣነት የሚያገለግል ሴቶች የሚጠቀሙበት ሻርፕ ነው። ሴቶች ብዙ ጊዜ ልጆቻቸውን ለማዘል ወይም ከገበያ የገዙትን ዕቃ ለመያዝ ይጠቀሙበታል። በተጨማሪም ይህ ሻርፕ ፀሐዩ ኃይለኛ በሚሆንበት ጊዜ አናትን ለመሸፈን ያገለግላል።
ወንዶች ራሳቸውን ለመሸፈን ኢኬት ኬፓላ የሚባል ባሕላዊ ጥምጥም ይጠቀማሉ። ወንዶች፣ ከባቲክ የሚዘጋጀውን ይህ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ጨርቅ አናታቸው ላይ ይጠመጥሙታል። ኢኬት ኬፔላ በአብዛኞቹ ሰዎች ዘንድ የሚታየው ትልቅ ግምት በሚሰጣቸው ዝግጅቶች ላይ እንደሚደረግ የክብር ልብስ ነው።
ሌላው ከባቲክ የሚሠራው የተለመደ ልብስ ሳሮንግ የተባለውና አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ግልድም ነው። አንዳንድ ጊዜ የጨርቁን ሁለት ጫፎች በማጋጠም በሽርጥ መልክ ይሰፋል። ብዙ ጊዜ ግን ጨርቁ ሰውነት ላይ ከተጠመጠመ በኋላ ወገብ ላይ ያለው ጫፍ ወደታች ተቀልብሶ ይጠቀለላል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይህን ባሕላዊ ልብስ ይለብሳሉ።
የባቲክ ጨርቅ ዘና ሲባል ከሚለበስ ሱሪ አንስቶ እስከ ጌጠኛ ካባ ድረስ የተለያዩ የልብስ ዓይነቶችን ለመሥራት ያገለግላል። በሌላ በኩል ደግሞ ጨርቁ፣ በባቲክ የማቅለም ስልት የሚሳሉ ሥዕሎችን ለመሥራትም ያገለግላል፤ በተጨማሪም ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ ጌጦችን፣ የጠረጴዛ ጨርቆችን፣ አልጋ ልብሶችንና የመሳሰሉትን ለመሥራት ይውላል። ቱሪስቶች በኢንዶኔዥያ በሚገኙ ገበያዎች ውስጥ ከባቲክ ጨርቅ የተሠሩ ቦርሳዎችን፣ ነጠላ ጫማዎችን፣ የራስጌ መብራቶችንና የላፕቶፕ ልባሶችን ሳይቀር ማግኘት ይችላሉ። በባቲክ ጨርቅ የሚሠሩ ነገሮች ዓይነታቸው ብዙ ነው፤ በእርግጥም ባቲክ በጣም የሚያምር ጨርቅ ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቀለጠ ሰም በተሞላ አነስተኛ የመዳብ መሣሪያ በመጠቀም በጣም ውስብስብ የሆነ ንድፍ በእጅ ይሠራል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰም በመቀባት ንድፍ የወጣለት ጨርቅ በተለያዩ ቀለማት ተደጋግሞ ይነከራል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባቲክ የሚዘጋጁ ነገሮች
1. ሴሌንዳንግ
2. ኢኬት ኬፓላ
3. ሳሮንግ