በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ፍቅርና ሰላም አገኘሁ

እውነተኛ ፍቅርና ሰላም አገኘሁ

እውነተኛ ፍቅርና ሰላም አገኘሁ

ኤዢዲዮ ናሃክብሪያ እንደተናገረው

በልጅነቴ ችላ እንደተባልኩና ማንም እንደማይወደኝ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን እንደምወደድ የሚሰማኝ ሲሆን እውነተኛ የሆነ ውስጣዊ ሰላምም አግኝቻለሁ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።

የተወለድኩት በኢስት ቲሞር (በዚያን ጊዜ የኢንዶኔዥያ ግዛት ነበረች) ተራሮች ላይ በምትገኝ ወለሏ አፈር በሆነ አንዲት ትንሽ ጎጆ ውስጥ ሲሆን ጊዜው 1976 ነበር። በድህነት ይማቅቁ የነበሩት ወላጆቼ ከወለዷቸው አሥር ልጆች እኔ ስምንተኛው ነበርኩ። ወላጆቼ ሁላችንንም ማሳደግ ስላልቻሉ መንትያ ወንድሜን አስቀርተው እኔን እንዲያሳድገኝ ለአጎቴ ልጅ ሰጡኝ።

ታኅሣሥ 1975 ማለትም እኔ ከመወለዴ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢንዶኔዥያ ኢስት ቲሞርን ወረረች፤ በዚህም ምክንያት ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ የቆየው የሽምቅ ውጊያ ተጀመረ። በመሆኑም የልጅነት ትዝታዬ በዓመፅና በመከራ የተሞላ ነው። ወታደሮች በመንደራችን ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩና ሁላችንም ሕይወታችንን ለማዳን ስንሸሽ የነበረውን ሁኔታ አሁንም ድረስ በደንብ አስታውሳለሁ። እኔና የአጎቴ ልጅ በእግራችን ረጅምና አድካሚ ጉዞ ካደረግን በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኢስት ቲሞር ተወላጆች ወደተጠለሉበት አንድ ተራራ ደረስን።

ይሁን እንጂ የጠላት ወታደሮች እዚያ መሸሸጋችንን ስላወቁ ወዲያውኑ የቦምብ ናዳ ያወርዱብን ጀመር። በዚያን ጊዜ የነበረው ሽብር፣ ሞትና እልቂት ትዝ ሲለኝ አሁንም ይዘገንነኛል። በመጨረሻ ወደ መንደራችን ብንመለስም የምኖረው በስጋት ነበር። በወቅቱ አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን በድንገት ይጠፉ ወይም ይገደሉ ስለነበረ ቀጥሎ የእኔ ተራ ይሆናል እያልኩ እጨነቅ ነበር።

አሥር ዓመት ሲሆነኝ የአጎቴ ልጅ በጠና ታሞ በመሞቱ ወላጆቼ ከሴት አያቴ ጋር እንድኖር ላኩኝ። አያቴ ባሏ የሞተባትና በኑሮዋ የምትማረር ሴት ስለነበረች እኔን የምታየኝ እንደ ሸክም ነበር። በመሆኑም እንደ ባሪያ ታሠራኝ ነበር። አንድ ቀን በጣም አሞኝ ስለነበር ሥራ መሥራት አልቻልኩም፤ በዚህ ምክንያት በጣም ስለደበደበችኝ ሞት አፋፍ ላይ ደርሼ ነበር። ደግነቱ አንድ አጎቴ ከቤተሰቡ ጋር እንድኖር ወሰደኝ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ በ12 ዓመቴ ትምህርት ቤት ገባሁ። ብዙም ሳይቆይ አጎቴ ሚስቱ ስለታመመችበት ከባድ ሐዘን ውስጥ ወደቀ። ከዚህ በኋላ በእነሱ ላይ ሸክም መሆን ስላልፈለኩ ጠፍቼ በጫካው ውስጥ ከሰፈረ አንድ የኢንዶኔዥያ ወታደሮች ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ። በዚያም ልብስ በማጠብ፣ ምግብ በማብሰልና የጦር ሠፈሩን በማጽዳት ወታደሮቹን እረዳቸው ነበር። እነሱም በጥሩ ሁኔታ ስለያዙኝ ተፈላጊ ሰው እንደሆንኩ ተሰማኝ። ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ዘመዶቼ አገኙኝ፤ እንዲሁም ወደ መንደሬ እንዲመልሱኝ ወታደሮቹን መጎትጎት ጀመሩ።

አክራሪ ፖለቲከኛ ሆንኩ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ የኢስት ቲሞር ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ዲሊ ተዛውሬ በዚያ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። በዚያም እንደ እኔ ዓይነት አስተዳደግ ካላቸው ብዙ ወጣቶች ጋር ተገናኘሁ። እኛም ነፃነት ማግኘትም ሆነ ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ፖለቲካዊ ንቅናቄ በማካሄድ እንደሆነ ተስማማን። የተማሪ ቡድናችን ካደራጃቸውና ፖለቲካዊ ይዘት ካላቸው በርካታ ሰላማዊ ሰልፎች መካከል ብዙዎቹ የተደመደሙት በረብሻ ነበር። አብዛኞቹ ጓደኞቼ ጉዳት ደረሰባቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ተገድለዋል።

ኢስት ቲሞር በ2002 ነፃነቷን ስታገኝ አገሪቱ የፍርስራሽ ክምር ሆና ነበር፤ በወቅቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ነበር። ከዚያ በኋላ ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ ተስፋ አድርጌ ነበር። ይሁን እንጂ በመላው አገሪቱ የነበረው ሥራ አጥነት፣ ድህነትና ፖለቲካዊ ብጥብጥ እየተባባሰ ሄደ።

የተለየ ጎዳና መከተል

በዚያን ጊዜ የምኖረው ከዘመዶቼ ጋር የነበረ ሲሆን ከእነሱም መካከል ኦንድሬ የሚባለው የሩቅ ዘመዴ ይገኝበታል፤ በዕድሜ ከእኔ የሚያንሰው ኦንድሬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሮ ነበር። ቀናተኛ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ስለነበርኩ ኦንድሬ ከሌላ ሃይማኖት አባላት ጋር ግንኙነት መፍጠሩ ደስ አላሰኘኝም ነበር። ያም ሆኖ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ጉጉት ነበረኝ፤ በመሆኑም ኦንድሬ መኝታ ቤቱ ያስቀመጠውን መጽሐፍ ቅዱስ አልፎ አልፎ አነብ ነበር። የማነበው ነገር የበለጠ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርብኝ አደረገ።

በ2004 ኦንድሬ በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንድገኝ የመጋበዣ ወረቀት ሲሰጠኝ በዚያ ለመገኘት ወሰንኩ። በመጋበዣ ወረቀቱ ላይ የተጠቀሰውን ሰዓት በትክክል ባለማንበቤ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ ከሁለት ሰዓት በፊት በቦታው ደረስኩ። ከውጭ አገር የመጡትን ጨምሮ በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በቦታው ሲደርሱ ሞቅ ባለ ስሜት በመጨበጥ ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ፤ ይህም በጣም አስደነቀኝ። በመታሰቢያው በዓል ላይ ንግግር ሲሰጥ እያንዳንዱን ጥቅስ በማስታወሻዬ ላይ ጻፍኩኝ፤ ወደ ቤት ስመለስ ደግሞ ተናጋሪው የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ጥቅሶቹን ከራሴ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥቼ አነበብኩ። በእርግጥም የተናገረው በሙሉ ትክክል ነበር!

በቀጣዩ ሳምንት በራሴ ቤተ ክርስቲያን በሚካሄደው ሥርዓተ ቁርባን ላይ ለመገኘት ወደዚያ ሄድኩ። እኔና አንዳንድ ሰዎች ዘግይተን ስለደረስን ቄሱ በንዴት እንጨት አንስቶ እያባረረ ከቤተ ክርስቲያኑ አስወጣን። ውጭ ቆመን ሳለን ቄሱ ሥርዓቱን ሲደመድም “የኢየሱስ ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” አለ። በዚህ ወቅት አንዲት ደፋር ሴት ጮክ ብላ “አሁን እነዚያን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያኑ አባረህ እንዴት ስለ ሰላም ትናገራለህ?” አለችው። ቄሱ መልስ አልሰጣትም። ከዚያን ጊዜ በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አልተመለስኩም።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ከኦንድሬ ጋር የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በዚህ የተደናገጡት ዘመዶቻችን ይቃወሙን ጀመር። የኦንድሬ ሴት አያት “እናንተ ልጆች፣ ከዚህ አዲስ ሃይማኖት ጋር ያላችሁን ግንኙነት ካላቆማችሁ ጉድጓድ ቆፍሬ ነው የምቀብራችሁ” በማለት አስፈራሩን። ይሁን እንጂ የእሳቸውን ዛቻ በመፍራት ጥናታችንን አላቆምንም። ደግሞም መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ቆርጠን ነበር።

ለውጦች ማድረግ

በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ በትክክል እንደማላውቅ ይሰማኝ ጀመር። አስቸጋሪና ግትር የነበርኩ ሲሆን ሰዎችን ማመን ይከብደኝ ነበር። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ልባዊ አሳቢነት ያሳዩኝ ነበር። በአንድ ወቅት፣ በጣም ታምሜ ሳለ ዘመዶቼ ችላ ቢሉኝም የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው የጠየቁኝ ከመሆኑም በላይ ረድተውኛል። የይሖዋ ምሥክሮቹ ያሳዩኝ ፍቅር “በቃልና በአንደበት ብቻ” ሳይሆን “በተግባር የሚገለጽ እውነተኛ ፍቅር” ነበር።​—1 ዮሐንስ 3:18 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን

ጠባዬም የማይመችና ኮስታራ የነበርኩ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ‘ስሜቴን ይረዱ’ እንዲሁም “የወንድማማች መዋደድ” ያሳዩኝ ነበር። (1 ጴጥሮስ 3:8) በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምወደድ ተሰማኝ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕርዬ እየተሻሻለ ሲሄድ ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ፍቅር ማሳደር ጀመርኩ። በመሆኑም ታኅሣሥ 2004 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ተጠመቅኩ። ብዙም ሳይቆይ ኦንድሬም ተጠመቀ።

ችግሮች ቢኖሩም በረከት አግኝቻለሁ

ከተጠመቅሁ በኋላ እውነተኛ ፍቅር የራባቸውን ወይም ፍትሕ የጠማቸውን ሰዎች የመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ። በመሆኑም በሙሉ ጊዜ ክርስቲያናዊ አገልግሎት (የይሖዋ ምሥክሮች አቅኚነት ብለው ይጠሩታል) መካፈል ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን አጽናኝ መልእክት ማካፈል ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው ሰላማዊ ሰልፎችና ረብሻዎች ላይ ከመካፈል የበለጠ ደስታ አስገኝቶልኛል። አሁን፣ ለሰዎች እውነተኛ እርዳታ እየሰጠሁ ነው!

በ2006 ከፖለቲካና ከድንበር ጋር በተያያዘ በኢስት ቲሞር ውስጥ ውጥረት ተፈጠረ፤ በተጨማሪም በርካታ አንጃዎች በመካከላቸው በነበረው ለረጅም ጊዜ በቆየ ቅሬታ የተነሳ እርስ በርሳቸው መዋጋት ጀመሩ። የዲሊ ከተማ ስትከበብ ከምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሹ። እኔም ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሆን ከዲሊ በስተምሥራቅ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ባውካው የምትባል ትልቅ ከተማ ሸሽቼ ሄድኩ። ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም በዚያ አዲስ ጉባኤ ማቋቋም በመቻላችን እጅግ ተባርከናል፤ ከዲሊ ውጭ ጉባኤ ሲቋቋም ይህ የመጀመሪያው ነው።

ከሦስት ዓመት በኋላ ማለትም በ2009 በጃካርታ፣ ኢንዶኔዥያ ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በተዘጋጀ ልዩ ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ። በጃካርታ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውን ብቻ ሳይሆን ልባቸውን ወለል አድርገው ከፍተውልኛል። ያሳዩኝ እውነተኛ ፍቅር ልቤን በጥልቅ ነክቶታል። በእርግጥም፣ ከልብ የሚያስብልኝ ዓለም አቀፋዊ “ቤተሰብ” የሆነ “የወንድማማች ማኅበር” አባል እንደሆንኩ ተሰማኝ።​—1 ጴጥሮስ 2:17

ውስጣዊ ሰላም አገኘሁ!

በትምህርት ቤቱ ከተካፈልኩ በኋላ ወደ ባውካው የተመለስኩ ሲሆን አሁንም የምኖረው በዚያ ነው። በአንድ ወቅት ሌሎች እኔን እንደረዱኝ ሁሉ እኔም በበኩሌ በባውካው፣ ለሰዎች መንፈሳዊ እርዳታ መስጠት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ለምሳሌ ያህል፣ ከባውካው ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ገለልተኛ መንደር ውስጥ እኔና ሌሎች ወንድሞች ማንበብም ሆነ መጻፍ የማይችሉ አረጋውያንን ጨምሮ 20 የሚያህሉ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እያስተማርን ነው። በቡድኑ ውስጥ ያሉት በሙሉ በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሦስቱ ተጠምቀው የጉባኤው አባላት በመሆን ከመንፈሳዊው “ቤተሰባችን” ጋር ተቀላቅለዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብላ ፈጣን እድገት በማድረግ ከተጠመቀች ፌሊዛርዳ ከምትባል አንዲት ወጣት ጋር ተዋውቄ ነበር። በ2011 ከፌሊዛርዳ ጋር ተጋባን። ዘመዴ የሆነው ኦንድሬም በኢስት ቲሞር በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገለ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ። በአንድ ወቅት ጉድጓድ ቆፍረው እንደሚቀብሩን ሲዝቱብን የነበሩትን የኦንድሬ አያት ጨምሮ አብዛኞቹ ዘመዶቼ አሁን ለእምነቴ አክብሮት አላቸው።

ቀደም ሲል ቁጣ የሚቀናኝ ሰው ነበርኩ፤ እንዲሁም ሰዎች እንደማይወዱኝ ሆኖ ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ለሰው የማይመች ባሕርይ ነበረኝ። አሁን ግን ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና እውነተኛ ፍቅርና ሰላም አግኝቻለሁ!

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤዢዲዮ አክራሪ ፖለቲከኛ በነበረበት ወቅት

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤዢዲዮና ፌሊዛርዳ በኢስት ቲሞር ካለው የባውካው ጉባኤ አባላት ጋር