በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የዓለም ሕዝብ ቁጥር “በ1999 6 ቢሊዮን” የነበረ ሲሆን በ2011 መጨረሻ ላይ 7 ቢሊዮንን አልፏል። ​—ሃርቫርድ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“በጥቅሉ ሲታይ 58.8% የሚሆኑት [የዩናይትድ ኪንግደም] ነዋሪዎች፣ ሁሉም ዓይነት የመገናኛ ዘዴዎች ተዘግተው ከቴክኖሎጂ ነፃ የሆነ ጊዜ ቢያገኙ ቤተሰባቸው እንደሚጠቀም ይሰማቸዋል። . . . ከሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ደግሞ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በጣም ስለበዙ ማምለጫ ቀዳዳ ማግኘት እንደሚፈልግ ተናግሯል።”​—ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ፣ ብሪታንያ

“ከ1976 ወዲህ የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ እያንዳንዱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚደረግበት ዓመት ከመጀመሩ በፊት ካቶሊኮች የፖለቲካ ምርጫ ሲያደርጉ እምነታቸውን ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ለመርዳት . . መግለጫ ሲያወጣ ቆይቷል።”​—ፎርድሃም ዩኒቨርሲቲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“በቂ ቁጥር ያላቸው ወንጀለኞች በጎዳና ላይ ትርምስ መፍጠር ከፈለጉ ይችላሉ። . የአንዳንድ ወጣት ብሪታንያውያን ሥነ ምግባር ላሽቋል፤ እነዚህ ወጣቶች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም አገሪቱን ለማሸበርና ለማዋረድ ግን በቂ ነው።”​—ዚ ኤኮኖሚስት፣ ብሪታንያ

በምድር ላይ ምን ያህል ዝርያዎች አሉ?

“ዛሬም እንኳ ምን ያህል ዝርያዎች እንዳሉ በእርግጠኝነት አናውቅም፤ ይህም በምድር ላይ ስላለው ሕይወት ያለን መሠረታዊ እውቀት እጅግ አናሳ መሆኑን የሚያጎላ ነው” በማለት ፒ ኤል ኦ ኤስ ባዮሎጂ በተሰኘ መጽሔት ላይ የምርምር ውጤታቸውን ያወጡ የሳይንስ ሊቃውንት ተናግረዋል። እነዚህ ሊቃውንት በምድር ላይ ያሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዝርያዎች 8.7 ሚሊዮን (ቁጥሩ በአንድ ሚሊዮን ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል) እንደሆኑ ቢገምቱም፣ ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ ይህ ቁጥር በ3 ሚሊዮን እና በ100 ሚሊዮን መካከል ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። እስካሁን ድረስ ተለይተው ስያሜ የተሰጣቸው ዝርያዎች 1.2 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፤ በዚህ አያያዝ ቀሪዎቹን ለይቶ ለመሰየም ከ1,000 ዓመታት በላይ ሊፈጅ እንደሚችል ይታመናል። “የሕያዋን ፍጥረታት ዝርያዎችን ለይቶ የመሰየሙ ሂደት አዝጋሚ መሆኑ፣ በሕይወት መኖራቸውን እንኳ ከማወቃችን በፊት ከምድር ገጽ የሚጠፉ ብዙ ዝርያዎች እንዲኖሩ ሊያደርግ ይችላል” በማለት ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

አርኪኦሎጂ በሳተላይት

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ትኩረታቸውን የሚስቡ ቦታዎችን ለማግኘት አዲስ ዘዴ መጠቀም ጀምረዋል። ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስል በሚያነሱ ካሜራዎችና በኢንፍራሬድ (ከምድር ገጽ በታች ያሉትን ነገሮች ማንሳት በሚችሉ) የሳተላይት ካሜራዎች የተነሱ ምስሎችን ምንነት ለማወቅ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች እየተጠቀሙ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በግብፅ ከ700 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ የተነሱ ምስሎች ቀደም ሲል የማይታወቁ 17 ፒራሚዶችን፣ 1,000 ጥንታዊ መቃብሮችንና 3,000 የሚያህሉ ጠፍተው የነበሩ መንደሮችን እንዳሳዩ ተዘግቧል። የኢንፍራሬድ ካሜራዎች ከምድር ገጽ በታች ያሉትን ነገሮች ማንሳት ስለሚችሉ መሬት ውስጥ የተቀበሩና የተረሱ ሕንፃዎችን ቅርጽ በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ማየት ተችሏል።