የሚበሉ ነፍሳት—ፈጽሞ የማንረሳው ምግብ
የሚበሉ ነፍሳት—ፈጽሞ የማንረሳው ምግብ
የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጊ የሚኖሩ ወዳጆቻችን እኔንና ባለቤቴን ቤታቸው ጋብዘውናል።
እንደደረስን “ግቡ! ግቡ! መቼም ርቧችሁ መሆን አለበት” አሉን። ገና ወደ ውስጥ ሳንገባ የቀይና የነጭ ሽንኩርት እንዲሁም የተለያዩ ቅመሞች ሽታ አወደን፤ የወዳጆቻችን ሞቅ ያለ ጨዋታም ከደጅ ይሰማል። ጋባዣችን ኤላም ስለሚቀርብልን ምግብ ታጫውተን ጀመር።
ኤላ “በማዕከላዊ አፍሪካ ለሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ ነፍሳት ዋነኛ የፕሮቲን ምንጭ ናቸው” አለችን። “ነፍሳትን የምንበላው ግን ጠቃሚ እንደሆኑ ስለሚሰማን ሳይሆን በጣም ስለሚጣፍጡ ነው።” አክላም “ዛሬ ማኮንጎ ማለትም አባጨጓሬ እንበላለን” አለችን።
ይህ የሚያስገርም አይደለም። ነፍሳት ገበታ ላይ መቅረባቸው ለአንዳንዶች የሚያጓጓ ባይሆንም አንዳንድ ነፍሳት ከመቶ በሚበልጡ አገሮች ተወዳጅ ምግብ ናቸው።
ከዱር የሚገኝ ምግብ
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ የተለያዩ ነፍሳት ይበላሉ። ቦቦ የሚባሉት ምስጦች (አሸን) በክረምት ወራት በኩይሳዎቻቸው፣ በከተሞች ውስጥ ደግሞ በኤሌክትሪክ ብርሃን አካባቢ በብዛት ይገኛሉ። ማታ ላይ ኃይለኛ ዝናብ ከጣለ በኋላ ልጆች እየተሯሯጡ አሸኖቹን በመልቀም በቅርጫት ይሰበስቧቸዋል፤ አብዛኛውን ጊዜም አሸኖቹን እየዘገኑ ሲቅሙ የሚሰማቸውን ደስታ ፊታቸው ላይ መመልከት ይቻላል። እነዚህ ምስጦች በፀሐይ ደርቀው፣ በጨውና በበርበሬ ተቀምመውና ተጠብሰው አሊያም በወጥ ወይም በሳምቡሳ መልክ ተሠርተው ይበላሉ።
በበጋው ወራት ወደ አካባቢው የሚመጡት አረንጓዴ ፌንጣዎች ኪንዳጎዞ ይባላሉ። የማዕከላዊ አፍሪካ ነዋሪዎች፣ ተለቅ ተለቅ ያለውን የፌንጣዎቹን ክንፍና እግር ከቀነጠሱ በኋላ ጠብሰው ወይም አገንፍለው ይበሏቸዋል።
በተጨማሪም በመላ አገሪቱ የተለያዩ የአባጨጓሬ ዝርያዎች
ይበላሉ። እኛም ኢምብራሲያ የሚባለውን ነፍሳት እጭ እንድንበላ ተጋበዝን። ቡናማ ቀለም ያላት ትልቅ የእሳት እራት በሳፔሊ ዛፎች ላይ እንቁላሏን ትጥላለች። እጮቹ ከተቀፈቀፉ በኋላ መንደርተኞቹ ለቅመው ይወስዱና ያጥቧቸዋል። ከዚያም እነዚህ አባጨጓሬዎች ከቲማቲም፣ ከቀይ ሽንኩርትና ከሌሎች ቅመሞች ጋር እንዲበስሉ ይደረጋል። አንዳንዶቹ እንዳይበላሹ ሲባል ደርቀው ወይም በጭስ ታጥነው ይቀመጣሉ። ይህም እስከ ሦስት ወር ድረስ ሳይበላሹ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል።የተመጣጠነና ለጤና ተስማሚ
ለምግብነት የሚውሉት ሁሉም ነፍሳት ባይሆኑም ተባይ ማጥፊያና ማዳበሪያ ካልተረጨባቸው አካባቢዎች የተለቀሙና በተገቢ ሁኔታ የተዘጋጁ ከሆኑ ብዙዎቹ ነፍሳት ለጤና ተስማሚ ናቸው። እርግጥ ነው፣ ሼልፊሽ የተባለው ዓሣ የሚያሳምማቸው ሰዎች ነፍሳትን መብላት አይኖርባቸውም፤ ምክንያቱም ሼልፊሽ የተባለው ዓሣና ነፍሳት ተፈጥሯቸው ተመሳሳይ ነው። የበሰበሱ ነገሮችን ከሚመገቡት ከአብዛኞቹ ሼልፊሾች በተለየ፣ ለመብልነት የሚውሉት አብዛኞቹ ነፍሳት የሚመገቡት ንጹሕ የሆኑ ቅጠሎችንና የሰው ልጆች የሆድ ዕቃ ጥቅም ላይ ሊያውላቸው የማይችላቸውን ዕፅዋት ነው።
አባጨጓሬዎች ሲያዩአቸው ትንሽ ቢመስሉም በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንደገለጸው የደረቀ አባጨጓሬ ከበሬ ሥጋ በእጥፍ የሚበልጥ ፕሮቲን አለው። የሥነ ምግብ ሊቃውንት፣ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገሮች ነፍሳት ጥሩ የተመጣጠነ ምግብ ምንጭ እንደሚሆኑ መገንዘብ ጀምረዋል።
ከአባጨጓሬዎች የሚገኘው ጥቅም እንደ ዝርያቸው የተለያየ ቢሆንም 100 ግራም ከሚመዝን አባጨጓሬ አንድ ሰው በቀን ውስጥ ከሚያስፈልጉት እንደ ማግኒዝየም፣ ብረት፣ ካልሲየም፣ ዚንክ፣ ፎስፈረስና ፖታሲየም ያሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች መካከል አብዛኛውን እንዲሁም በርካታ ቫይታሚኖች ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም በቂ ወይም የተመጣጠነ ምግብ ለማያገኙ ሕፃናት ከተፈጨ አባጨጓሬ የተሠራ ዱቄት ተለውሶ ከሌሎች ምግቦች ጋር ቢሰጣቸው ይጠቅማቸዋል።
ነፍሳትን መብላት የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ሌሎች ጥቅሞች አሉት። ነፍሳትን ለምግብነት መጠቀም ለአካባቢ ደኅንነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። እነሱን ለምግብነት ማዘጋጀት ብዙ ውኃ የማይፈጅ ከመሆኑም ሌላ የምድርን ሙቀት ከፍ የሚያደርጉ ጋዞች እንዲበዙ አያደርግም። ከዚህም በላይ ነፍሳትን ለቅሞ መብላት ጥሩ የተባይ መከላከያ ዘዴ ነው።
ዋናው ምግብ
የሚቀርብልንን ልዩ ምግብ እየጠበቅን እያለ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር በተሰጠው ሕግ ላይ አንበጦች ንጹሕ እንደሆኑ መገለጹን አስታወስን። መጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ሌሎች የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች አንበጣ በልተዋል። (ዘሌዋውያን 11:22፤ ማቴዎስ 3:4፤ ማርቆስ 1:6) እርግጥ ነው፣ መጀመሪያ ላይ ያልለመድነውን ነገር መብላት ይከብደን ይሆናል።
ኤላ ከወጥ ቤቷ ትኩስ ምግብ ይዛ ስትመጣ የሁሉም ሰው ትኩረት በምግቡ ላይ አረፈ። አብረውን የነበሩት ስምንት የአገሬው ሰዎች በሁለት ጎድጓዳ ሳህኖች የቀረበውን አባጨጓሬ ሲያዩ ፊታቸው በደስታ ፈካ። እንግዶች እንደመሆናችን መጠን ቅድሚያውን የሰጡን ሲሆን በርከት አድርገውም አወጡልን።
“እንዲህ ያለውን ውድ ያልሆነ፣ የሚጥምና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ያሉት ምግብ ከተጋበዛችሁ ከመብላት ወደኋላ አትበሉ። ፈጽሞ የማትረሱት ምግብ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም!”
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሬ “ማኮንጎ” ወይም አባጨጓሬ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የበሰለ “ኪንዳጎዞ” ወይም ፌንጣ