በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዩሮ 2012—ታሪካዊ ውድድር

ዩሮ 2012—ታሪካዊ ውድድር

ዩሮ 2012—ታሪካዊ ውድድር

የእግር ኳስ ጨዋታ ማየት ትወዳለህ? ወይስ ከማየት ባለፈ ትጫወታለህ? ከሆነ የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበሮች ኅብረት ስለሚያዘጋጀውና ሰኔ 8 በዋርሶ፣ ፖላንድ ተጀምሮ ሐምሌ 1 ላይ በኪየቭ፣ ዩክሬን ስለሚጠናቀቀው ዩሮ 2012 የእግር ኳስ ውድድር ሰምተህ መሆን አለበት። ስለ ዩሮ 2012 ምን ማለት ይቻላል? ይህን ውድድር ለማካሄድ ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል? ውድድሩን ታሪካዊ የሚያሰኘውስ ምንድን ነው?

“በጋራ ሆነን ታሪክ እንሥራ”

የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ከ1960 ጀምሮ በየአራት ዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል። ይህን ውድድር ካዘጋጁት በርካታ አገሮች መካከል ኦስትሪያ፣ ቤልጅየም፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድ፣ ፖርቱጋል፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድና ዩጎዝላቭያ ይገኙበታል።

በዚህ ዓመት የሚደረገውን ውድድር በጋራ እንዲያዘጋጁ የተመረጡት ፖላንድና ዩክሬን ናቸው። በፖላንድ የሚደረገውን ጨዋታ የሚያስተናግዱት ከተሞች ግዳንስክ፣ ፖዝናን፣ ዋርሶ እና ቭሮትስላፍ ናቸው። በዩክሬን ደግሞ ዲኔትስክ፣ ካርኪፍ፣ ኪየቭ እና ለቪፍ የተባሉት ከተሞች ያስተናግዳሉ።

የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበሮች ኅብረት እንዳለው ከሆነ “ውድድሩን ሁለት አገሮች በኅብረት እንዲያስተናግዱ ሲመረጡ (በ2000 በቤልጅየም/በኔዘርላንድ [እና] በ2008 በኦስትርያ/በስዊዘርላንድ ከተካሄደው ቀጥሎ) ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።” ያም ሆኖ ዩሮ 2012 ታሪካዊ ነው። እንዲህ የተባለበት ምክንያት ምንድን ነው? በዚህ ዓመት የሚካሄደው ውድድር የተዘጋጀው የጋራ አስተናጋጅ በሆኑት ሁለት አገሮችና ውድድሩን በሚያደራጁ ኮሚቴዎች ከፍተኛ ትብብር ከመሆኑም በላይ እንዲህ ዓይነቱ ውድድር በማዕከላዊና በምሥራቅ አውሮፓ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው። በመሆኑም ለዚህ ዓመት ዝግጅት መሪ ቃል እንዲሆን የተመረጠው “በጋራ ሆነን ታሪክ እንሥራ” የሚል ነው።

ዝግጅት

ማንኛውንም ውድድር ለማድረግ በቅድሚያ ከሚታሰብባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ጨዋታውን ለማካሄድ የሚያመች ስፍራ ማግኘት ነው። ለዚህም ሲባል አስተናጋጅ ከተሞች የሆኑት ፖዝናን እና ካርኪፍ ቀደም ሲል የነበሯቸውን ስታዲየሞች ያደሱ ሲሆን በሌሎች ስድስት ከተሞች ደግሞ አዳዲስ ስታዲየሞችን ገንብተዋል። እነዚህ ስታዲየሞች በድምሩ 358,000 ተመልካቾችን እንደሚይዙ ይገመታል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተመልካቾች እንደሚኖሩ ስለሚጠበቅ አስተናጋጆቹ ከተሞች ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት የሰጡ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የደኅንነት ሠራተኞች ሥልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል። ሳይንስ ኤንድ ስኮላርሺፕ ኢን ፖላንድ እንደገለጸው ከሆነ ከተሰጣቸው ሥልጠና መካከል “ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል 140 በሚሆኑ ሌሎች ዝግጅቶች ላይ አስቀድሞ ልምምድ ማድረግን” ያጠቃልላል፤ “ከእነዚህም መካከል የሕዝቡን እንቅስቃሴ መቆጣጠር፣ የደኅንነት ቀጠናዎችን መፍጠርና ከሌላ አገር ከሚመጡ የደኅንነት ቡድኖች ጋር ተባብሮ መሥራት ይገኙበታል።”

እንደዚህ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ለምን አስፈለገ? አንደኛው ምክንያት፣ ትላልቅ የስፖርት ዝግጅቶች በሚደረጉበት ወቅት አሸባሪዎች ጥቃት የመሰንዘራቸው አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ባለሥልጣናት መገንዘባቸው ነው። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከተከሰቱት ረብሻዎችና ብጥብጦች እንደታየው ሥርዓት አልበኛ የሆኑ አንዳንድ ተመልካቾች ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ነው።

ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ

የሚያሳዝነው፣ ብዙ ተመልካቾች ለአንዳንድ ስፖርቶች ያላቸው ፍቅር ገደቡን ያለፈ ነው። የአንድ የቡድን ደጋፊ የሆነ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የምደግፈው [የእግር ኳስ] ቡድን ጥሩ ውጤት ካላገኘ ሕይወቴ ደስታና እርካታ የራቀው ይሆናል። እውነቱን ለመናገር፣ የኑክሌር ጦርነት ሊፈነዳ እንደሆነ ብሰማ ከሁሉ በላይ የሚያስጨንቀኝ ነገር በሳምንቱ መጨረሻ የሚካሄደውን ውድድር ያስተጓጉለው ይሆን የሚለው ጉዳይ ነው።”

ከዚህ በተቃራኒ ለመዝናኛ ሊኖረን ስለሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት የጥበብ ጎተራ የሆነ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ልብ ማለት ያስፈልጋል። የአምላክ ቃል ጤናማ መዝናኛ ያለውን ጠቀሜታ ሲጠቁም “ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1-4) በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ልከኛ እንድንሆን ያበረታታናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11) በመሆኑም በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምን መሆን እንዳለባቸው በምንወስንበት ጊዜ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለይተን እንድናውቅ የተሰጠንን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ጥበብ ነው።​—ፊልጵስዩስ 1:10

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ዩሮ 2012​ከትንባሆ ነፃ የሆነ ዝግጅት

የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበሮች ኅብረት ጥቅምት 20, 2011 ባወጣው መግለጫ መሠረት “ዩሮ 2012 በሚካሄድባቸው ስታዲየሞች በሙሉ ትንባሆ ማጨስ፣ መሸጥ ወይም ማስተዋወቅ ሙሉ በሙሉ እንዲታገድ አድርጓል።” እገዳው የተጣለበት ምክንያት ምንድን ነው? የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበሮች ኅብረት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሚሼል ፕላቲኒ “ዩሮ 2012 ከትንባሆ ነፃ የሆነ ዝግጅት እንዲሆን የተፈለገው ለተመልካቾቻችንና በውድድሩ ወቅት ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ ጤንነት ሲባል ነው” ብለዋል። እገዳውን ከደገፉት መካከል የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነር የሆኑት አንድሩላ ቫሲሉ የሚገኙበት ሲሆን እሳቸውም በሌሎች አካባቢዎች ጨምሮ በምግብ ቤቶችና በሕዝብ መጓጓዣዎች ውስጥ እንዳይጨስ በማገድ ከሲጋራ ጪስ ነፃ የሆነ አካባቢን የመፍጠሩን ጉዳይ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስተናጋጅ ከተሞችን አሳስበዋል። አክለውም “እግር ኳስም ሆነ ሌሎች ስፖርቶች ጤናን እና የአካል ብቃትን ያሻሽላሉ። ትንባሆ ግን ተቃራኒ ውጤት ያስከትላል” ብለዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፖላንድ

ዋርሶ

ግዳንስክ

ፖዝናን

ቭሮትስላፍ

ዩክሬን

ለቪፍ

ኪየቭ

ካርኪፍ

ዲኔትስክ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቪየና፣ ኦስትርያ በሚገኘው ኧርንስት ሃፐል በተባለ ስታዲየም በጀርመንና በስፔይን መካከል የተደረገው የዩሮ 2008 የፍጻሜ ጨዋታ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኪየቭ፣ ዩክሬን ያለው የኦሎምፒክ ስታዲየም

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Pages 24 and 25, both photos: Getty Images