በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

2. ንጽሕናውን ጠብቁ

2. ንጽሕናውን ጠብቁ

2. ንጽሕናውን ጠብቁ

አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም እጁን በመታጠብ፣ መሣሪያዎቹን ከጀርም ነፃ በማድረግና የቀዶ ሕክምና ክፍሉን ንጽሕና በመጠበቅ ታካሚዎቹ በበሽታ እንዳይጠቁ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ሁሉ እናንተም የራሳችሁን፣ የወጥ ቤታችሁንና የምታዘጋጁትን ምግብ ንጽሕና በመጠበቅ ቤተሰባችሁ በበሽታ እንዳይጠቃ መከላከል ትችላላችሁ።

እጃችሁን ታጠቡ

የካናዳ የሕዝብ ጤና ቢሮ እንደሚናገረው “እንደ ጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ ካሉት ተላላፊ በሽታዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የሚዛመቱት በእጅ እንደሆነ ይገመታል።” ስለዚህ ምግብ ከመብላታችሁ በፊት፣ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀማችሁ በኋላ እንዲሁም ምግብ ልታዘጋጁ ስትሉ እጃችሁን በውኃና በሳሙና በደንብ ታጠቡ።

የወጥ ቤታችሁን ንጽሕና ጠብቁ

አንድ ጥናት እንዳሳየው በቤት ውስጥ የተሻለ ንጽሕና ያለው ቦታ መጸዳጃ ቤት ሲሆን “በዓይነ ምድር ውስጥ በሚገኝ ባክቴሪያ የተበከለው ደግሞ በወጥ ቤት ውስጥ ያለው የዕቃ ማጠቢያ ስፖንጅ/ጨርቅ ነው።”

ስለዚህ የዕቃ ማጠቢያ ጨርቆቻችሁን ቶሎ ቶሎ ቀይሯቸው፤ እንዲሁም ወጥ ቤቱን ለማጽዳት ሙቅ ውኃና ሳሙና ወይም ጀርሞችን የሚገድል ኬሚካል ተጠቀሙ። እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ቦላ የምትኖረው የቧንቧ ውኃ በሌለው ቤት ውስጥ ነው። “ንጽሕናን መጠበቅ በጣም ተፈታታኝ ነው” ትላለች። “ይሁን እንጂ የወጥ ቤቱንና የቤታችንን ንጽሕና ለመጠበቅ ምንጊዜም ውኃና ሳሙና በበቂ መጠን እንዲኖር እናደርጋለን።”

የምግብ ምርቶችን በደንብ እጠቧቸው

አንድ የምግብ ሸቀጥ ከመሸጡ በፊት ቆሻሻ ውኃ፣ ዓይነ ምድር እንዲሁም እንስሳት ነክተውት አሊያም ከሌሎች ጥሬ የምግብ ምርቶች ጋር ተነካክቶ ሊበከል ይችላል። ስለዚህ ተልጠው የሚበሉ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች እንኳ ጎጂ የሆኑ ጀርሞች ሊኖሯቸው ስለሚችሉ በደንብ መታጠባቸው ጠቃሚ ነው። እርግጥ ይህን ማድረግ ጊዜ ይጠይቃል። በብራዚል የምትኖረው ዳያን የምትባል እናት “ሰላጣ ሳዘጋጅ አትክልቶቹን በደንብ ለማጠብ ስል ተረጋግቼ ለመሥራት እሞክራለሁ” ብላለች።

ጥሬ ሥጋን ለይታችሁ አስቀምጡ

ሥጋና ዶሮ እንዲሁም ዓሣ፣ ባክቴሪያ ሊያዛምቱ ስለሚችሉ ከሌሎች ነገሮች ጋር እንዳይነካኩ በተለየ ዕቃ አድርጋችሁ አስቀምጧቸው። እንደነዚህ ላሉት ሥጋ ነክ የምግብ ዓይነቶች ብቻ የምትጠቀሙበት ቢላና መክተፊያ ይኑራችሁ፤ አለዚያም ሥጋ ነክ ነገሮችን ከመክተፋችሁ በፊትም ሆነ በኋላ ቢላችሁንና መክተፊያችሁን በሞቀ ውኃና በሳሙና በደንብ እጠቡት።

የራሳችሁን፣ ምግብ ለመሥራት የምትጠቀሙባቸውን መሣሪያዎችና የምግቡን ንጽሕና ለመጠበቅ ከላይ የቀረቡትን ነጥቦች ተግባራዊ አድርጋችኋል፤ ታዲያ ምግቡን ሳይበከል ልትሠሩት የምትችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ልጆቻችሁን አሠልጥኑ፦ “ልጆቻችንን ምግብ ከመብላታቸው በፊት እጃቸውን እንዲታጠቡ እንዲሁም ምግብ መሬት ላይ ከወደቀ እንዲያጥቡት አለዚያም እንዲጥሉት አስተምረናቸዋል።”​—ሖዪ፣ ሆንግ ኮንግ