3. ምግብ ስታዘጋጁም ሆነ ስታስቀምጡ ተጠንቀቁ
3. ምግብ ስታዘጋጁም ሆነ ስታስቀምጡ ተጠንቀቁ
በጥንቷ እስራኤል አንድ ሰው ምግብ ሲያዘጋጅ ‘ምን እንደሆነ የማይታወቅ’ የዱር ፍሬ ለቅሞ ወጥ ሠራበት። ምግቡን ያቀረበላቸው ሰዎች ግን “‘በምንቸቱ ውስጥ የሚገድል መርዝ አለ!’ ብለው ጮሁ።”—2 ነገሥት 4:38-41
ከዚህ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው በቸልተኝነት የተዘጋጀ ምግብ ጉዳት ሊያደርስ አልፎ ተርፎም ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ጠንቃቆች መሆን ያስፈልገናል። በመሆኑም ራሳችንን ከምግብ ወለድ በሽታዎች ለመጠበቅ ምግባችንን በጥንቃቄ ማዘጋጀትና ማስቀመጥ ይኖርብናል። ቀጥሎ የቀረቡት አራት ነጥቦች ይህን ለማድረግ ይረዱናል፦
● በረዶው እንዲለቅ ለማድረግ ሥጋ ውጭ አታስቀምጡ
“በረዶ የሠራ [ሥጋ] ውጭ ሲቀመጥ ውስጠኛው ክፍል እንደቀዘቀዘ ቢቆይም እንኳ ላይኛው ክፍል ግን ‘የአደጋ ቀጠና’ ውስጥ ይኸውም ባክቴሪያዎች በፍጥነት በሚራቡበት ከ4 እስከ 60 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ባለው የሙቀት ክልል ውስጥ ሊሆን ይችላል” በማለት የዩናይትድ ስቴትስ የግብርና ሚኒስቴር ይናገራል። ከበረዶ ቤት የወጣውን ምግብ ታችኛው ማቀዝቀዣ ውስጥ በማድረግ ወይም ውኃ በማያስገባ ዕቃ ውስጥ አድርጎ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ በማቆየት አሊያም ማይክሮዌቭ ውስጥ በማስገባት በረዶውን ማስለቀቅ ይቻላል።
● በደንብ አብስሉት
የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው “ምግብን በደንብ ማብሰል ሁሉንም አደገኛ ጀርሞች ይገድላቸዋል ማለት ይቻላል።” ስለዚህ ምግብ፣ በተለይም ሾርባና ወጥ ስትሠሩ በደንብ እስኪበስል ድረስ ወይም እስከ 70 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ አንተክትኩት። * አንዳንድ ምግቦች ውስጣቸው በደንብ በስሎ እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ስለሆነ ብዙ ምግብ አዘጋጆች ሙቀቱን ለመለካት የሥጋ ቴርሞሜትር ይጠቀማሉ፤ አሊያም በሹካ ወጋ በማድረግ ወይም መሃሉ ላይ በመቁረጥ መብሰሉን ማየት ይቻላል።
● በትኩሱ አቅርቡት
የበሰለ ምግብ ከማቀዝቀዣ ውጭ ለረጅም ጊዜ ከተቀመጠ ስለሚበላሽ ወዲያውኑ መበላቱ የተሻለ ነው። ቀዝቃዛ እንዳለ መበላት ያለበት ምግብ እንደቀዘቀዘ እንዲቆይና በትኩሱ መበላት ያለበት ምግብ ደግሞ ትኩስ እንዲሆን አድርጉ። ሥጋ ከበሰለ በኋላ ትኩስ ሆኖ እንዲቆይ ለማድረግ 93 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ገደማ በሆነ ምድጃ ውስጥ ማስገባት አሊያም እሳቱን በጣም ቀንሶ እንደተጣደ መተው ይቻላል።
● የተራረፉ ምግቦችን በጥንቃቄ አስቀምጡ
በፖላንድ የምትኖረው አኒታ የተባለች እናት ብዙውን ጊዜ ለቤተሰቧ ምግብ የምታቀርበው ወዲያው እንደተሠራ ነው። ብዙ ምግብ ከሠራች ደግሞ ምን እንደምታደርግ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙም ሳይቆይ በትንሽ በትንሹ አድርጌ በረዶ ቤት ውስጥ አስቀምጠዋለሁ፤ ከፋፍዬ ማስቀመጤ በረዶውን ማስለቀቅ ቀላል እንዲሆን ያደርጋል።” የተረፋችሁን ምግብ ማቀዝቀዣ ውስጥ የምታስቀምጡት ከሆነ ከሦስት እስከ አራት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ብሉት።
ምግብ ቤት የምትበሉ ከሆነ ግን ምግቡን የሚያዘጋጀው ሌላ ሰው ነው። ታዲያ ውጭ ስትበሉ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ትችላላችሁ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 እንደ ዶሮ ያሉ አንዳንድ ምግቦች ከዚያ በላይ በሆነ ሙቀት መብሰል ያስፈልጋቸዋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልጆቻችሁን አሠልጥኗቸው፦ “ልጆቼ ምግብ ሲያበስሉ በምግቡ ማሸጊያ ላይ የተጻፈውን መመሪያ እንዲያነቡና ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስባቸዋለሁ።”—ዩክ ሊንግ፣ ሆንግ ኮንግ