በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ራሱን የሚተካው የኒውት ሌንስ

ራሱን የሚተካው የኒውት ሌንስ

ሳላማንደር ከሚባሉት እንስሳት የሚመደበውና እንሽላሊት የሚመስለው ኒውት እግሩንና ጅራቱን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነቱን ክፍሎች እንዲሁም ሕብረ ሕዋሳትን ቢያጣ እንደገና የመተካት አስደናቂ ችሎታ አለው። ይሁን እንጂ የሚተኩት የሰውነቱ ክፍሎች እንደ መጀመሪያዎቹ ይሆናሉ? ከኒውት ዓይኖች ሌንስ ጋር በተያያዘ መልሱ አዎ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ኒውቶች የዓይናቸውን ሌንስ እንደገና የሚተኩት አይሪስ በሚባለው የዓይን ክፍል ላይ ያሉትን ሴሎች ወደ ሌንስ ሴሎች በመቀየር ነው። የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች፣ ስለዚህ ሂደት ይበልጥ ለማወቅ ስለፈለጉ በጃፓን በሚገኙ የተወሰኑ ኒውቶች ላይ ለ16 ዓመታት ጥናት አካሂደዋል። ተመራማሪዎቹ የእያንዳንዱን ኒውት ሌንሶች 18 ጊዜ ያወጡበት ሲሆን ልክ እንደተጠበቀውም ኒውቶቹ 18 ጊዜ አዳዲስ ሌንሶችን ተክተዋል።

ጥናቱ ሲጠናቀቅ ኒውቶቹ ዕድሜያቸው 30 ዓመት ገደማ ነበር፤ ይህም በተፈጥሮ መኖሪያቸው ቢሆኑ ኖሮ ከሚኖራቸው ዕድሜ በአምስት ዓመት ይበልጣል። ያም ሆኖ ሌንሶቻቸውን የሚተኩበት ፍጥነት በልጅነታቸው ከነበረው አልቀነሰም። በተጨማሪም በኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ዴይተን ዩኒቨርስቲ እንደገለጸው አዲሶቹ ሌንሶች “ሙሉ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ኒውት መጀመሪያ ላይ ከነበረው ሌንስ ምንም ልዩነት የላቸውም።” በኒውቶች ላይ ጥናት ያደረገው ቡድን አባል የሆኑት ፓናዮቲስ ቾኒስ የተባሉ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ “እኔም እንኳ በግኝቱ ተደንቄያለሁ” ብለዋል። እኚህ ሰው አዲሱ ሌንስ “ፍጹም” እንደሆነ ተናግረዋል።

የሳይንስ ሊቃውንት፣ ኒውቶች ጉዳት የደረሰበት የሰውነታቸውን ክፍል ለመተካት ያላቸው ችሎታ በሰው ልጆችም ላይ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለመረዳት እንደሚያስችል ያምናሉ። ቾኒስ እንደሚሉት “ኒውቶች፣ የሰውነት ክፍሎችን መተካት ስለሚቻልበት መንገድ (በተለይም ከእርጅና ጋር በሚደረገው ትግል ረገድ) በጣም ግሩም የሆነ መረጃ ይሰጡናል።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ራሱን የሚተካው የኒውት ሌንስ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

“የተተኩት” ሌንሶች ከመጀመሪያዎቹ ምንም ልዩነት የላቸውም

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Top photo: © Vibe Images/Alamy; middle photo: © Juniors Bildarchiv/Alamy