በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

የወጣቶች ጥያቄ . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? (ሚያዝያ 2009) ዕድሜዬ 24 ዓመት ሲሆን ባለትዳርና የልጅ እናት ነኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሁልጊዜ ትግል ይጠይቅብኝ ነበር። በዚህ ርዕሰ ትምህርት ላይ የተሰጡትን ምክሮች እየሠራሁባቸው ሲሆን ተቆርጦ እንዲወጣ የተዘጋጀውን ሣጥንም በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀምኩበት ነው። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ የማነብበትን ጊዜ የምጠባበቀው በጉጉት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ምን ያህል ስምምነት እንዳላቸውና በተለያዩ ክሮች እንደተሠራ ውብ ጥልፍ አንድ ላይ ሲታዩ ወጥ የሆነ ሐሳብ እንደሚያስተላልፉ መገንዘብ ችያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንደ አሁኑ አስደሳች ሆኖልኝ አያውቅም። በጣም አመሰግናችኋለሁ!

ኬ. ቲ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ—ክፍል 6 (ሚያዝያ 2011) “ሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ” የተሰኘው ርዕስ “ኢየሩሳሌም ምን ደረሰባት? በቨስፔዥያንና በልጁ በቲቶ የሚመራው የሮማውያን ሠራዊት ከ60,000 ወታደሮች ጋር ተመለሰ” በማለት ይናገራል። ይህ ሐሳብ በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ሠራዊቱን የመሩት ቨስፔዥያንና ቲቶ እንደነበሩ ያመለክታል። ይሁን እንጂ የታሪክ ማስረጃዎች በዚህ ወቅት ቨስፔዥያን በሮም እንደነበረ ይጠቁማሉ።

ጄ. ኦ.፣ አውስትራሊያ

“የንቁ!” መጽሔት አዘጋጆች መልስ፦ በፖል ሚየር የተዘጋጀው “ጆሴፈስ—ዚ ኢሴንሺያል ራይቲንግስ” የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ቲቶ 15ኛውን ክፍለ ጦር ይዞ ከእስክንድርያ እየገሰገሰ በመምጣት አምስተኛውንና ስድስተኛውን ክፍለ ጦር ይዞ ይጠብቀው ከነበረው ከአባቱ ከቨስፔዥያን ጋር ጴጤሌማይስ ላይ ተገናኝቷል።” በተጨማሪም በማቲው ቡንሰን የተዘጋጀው “ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ዘ ሮማን ኢምፓየር” ስለ ቨስፔዥያን እንዲህ ብሏል፦ “ቨስፔዥያን ከልጁ ከቲቶ ጋር ሆኖ አይሁዳውያን ያስነሱትን ዓመፅ በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ በ68 የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ለመክበብ ሲዘጋጅ ኔሮ እንደወደቀና ጋልባ እንደተካው የሚገልጽ መልእክት ደረሰው። . . . በ70 የበልግ ወራት ላይ ሮም ደረሰ።” ስለዚህ መጀመሪያ በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ቨስፔዥያንና ቲቶ ⁠አንድ ላይ የነበሩ ይመስላል። ይሁን እንጂ በሆነ ወቅት ላይ ቨስፔዥያን ኃላፊነቱን ለቲቶ ሰጥቶ ወደ ሮም ተመልሷል።

ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ (ጥቅምት 2011) ይህን መጽሔት በማግኘታችን በጣም አመስጋኞች ነን። መጽሔቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወላጆች የሰጧቸውን በርካታ ጠቃሚ ምክሮችና ሐሳቦች እንዲሁም የተናገሯቸውን ተሞክሮዎች ይዟል። ይህን ልዩ እትም ጊዜ ወስዳችሁ በትጋትና በጥንቃቄ እንዳዘጋጃችሁት መገመት አያዳግተንም። በዚህ አስቸጋሪ ዘመን የሚኖሩ ቤተሰቦችንና ወጣቶችን ለመርዳት ስትሉ ለምታዘጋጇቸው ድንቅ ርዕሶች ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።

ኬ. ኤፍ.፣ አውስትራሊያ

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል? (ሐምሌ 2011) ይህን ርዕስ ስላወጣችሁ በጣም አመሰግናችኋለሁ። በአሁኑ ጊዜ መገናኛ ብዙኃን ማኅበራዊ ድረ ገጾችን አስመልክተው ከሚያስፋፉት ፕሮፖጋንዳ ነፃ መሆን አይቻልም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምገኝ ወጣት እንደመሆኔ መጠን ከጓደኞቼ ጋር ለመገናኘት፣ ፎቶግራፎቼን ለሌሎች ለማሳየትና አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ ማኅበራዊ ድረ የተሻለ ነገር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ በየቀኑ ማን አዲስ ሐሳብ እንዳሰፈረ ወይም አስተያየት እንደጻፈ አሊያም ፎቶ እንዳስቀመጠ እመለከት ነበር። ይህ ልማድ መላ ሕይወቴን ተቆጣጥሮት ነበር። ይህ ርዕስ ግን የማኅበራዊ ድረ ገጽ አካውንት ያለው ሁሉም ሰው እንዳልሆነና የግድ አስፈላጊ ነገር እንዳልሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል። ጊዜዬን በጣም እየተሻማብኝ እንደሆነ ስላስተዋልኩ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አካውንቴን ዘግቼዋለሁ።

ኤስ. ኤ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ