በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የባሕር ፍጥረታትን ማጣጣም

የባሕር ፍጥረታትን ማጣጣም

የባሕር ፍጥረታትን ማጣጣም

በኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ የተቀመጡ ሰዎች የሚቀርብላቸውን ምግብ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ገበታው ሲቀርብ፣ በሳህናቸው ላይ የተቀመጠውን የባሕር ፍጥረት ቅርፊት ፈልቅቀው ለማውጣት በተዘጋጀው መሣሪያ በመጠቀም እንስሳውን ዘነጣጠሉት። ከዚያም፣ ሽቅብ አፍጥጠው የሚያዩዋቸውን የዚህን ፍጥረት ዓይኖች ከቁብ ሳይቆጥሩ የሚጣፍጠውን ሥጋ ማጣጣሙን ተያያዙት። አበላላቸውን ያየ በጣም ተርበዋል ብሎ ማሰቡ አይቀርም። ለመሆኑ የሚበሉት ነገር ምንድን ነው? ሎብስተር በመባል የሚታወቀውን የባሕር ፍጥረት ነው።

በ1700ዎቹ ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ምሥራቅ የባሕር ዳርቻ በሎብስተሮች መንጋ ይሸፈን ነበር። ሰዎች እነዚህን ባለ ቅርፊት ፍጥረታት ማዳበሪያ እንዲሆኑ አፈር ላይ ይበትኗቸው እንዲሁም ዓሣ ሲያጠምዱ በመንጠቋቸው ጫፍ ላይ ያደርጓቸው ነበር። ለእስረኞች ቀለብ ሆነውም ይቀርቡ ነበር። በዚያ ዘመን ሎብስተሮች በብዛት የሚገኙ ከመሆናቸው የተነሳ በአካባቢው የነበሩ ቅጥር ሠራተኞች ሎብስተር መብላት ስለሰለቻቸው በሳምንት ከሦስት ጊዜ በላይ ይህ ምግብ እንዳይቀርብላቸው ለማስደረግ ፍርድ ቤት ክስ አቅርበዋል! በክሱም አሸንፈዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ግን ከባሕር ዳርቻ ርቀው በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሎብስተር ብርቅ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ሎብስተር እንደሞተ ወዲያው መበስበስ ስለሚጀምርና አድርቆ ወይም ጨው ነስንሶ ማቆየት ስለማይቻል ነው። ይሁን እንጂ በ1800ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ የሎብስተር አምራቾች ሎብስተሩን በቆርቆሮ አሽገው ማቅረብ በመጀመራቸው ብዙ ሰዎች ይህን ጣፋጭ ምግብ ማጣጣም ችለዋል። በተጨማሪም የባቡር ሐዲድ መዘርጋቱ በሕይወት ያሉ ሎብስተሮችን ወደተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍሎች ለመላክ አስችሏል። በዚህ ምክንያት የሎብስተር ተፈላጊነት እጅግ አሻቀበ። እንዲያም ሆኖ ሎብስተሮችን እንደተያዙ ማጓጓዝ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ሎብስተር ሀብታሞች ብቻ የሚያጣጥሙት የቅንጦት ምግብ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም በሚገኙ የውቅያኖስ ዳርቻዎች የሚኖሩ ዓሣ አስጋሪዎች የተለያዩ ዓይነት ሎብስተሮችን ያጠምዳሉ። የአሜሪካው ሎብስተር፣ ከኒውፋውንድላንድ እስከ ሰሜን ካሮላይና ባለው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ይገኛል። ዋነኛዋ የሎብስተር አቅራቢ በሰሜናዊ ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ የምትገኘው ሜይን ናት። ከዚህች ከተማ፣ የበሰሉም ሆነ ጥሬ ሎብስተሮች ወደ መላው ዓለም ይላካሉ። አቅራቢዎች ከ36,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ሎብሰተር በአንድ አውሮፕላን ማጓጓዝ ይችላሉ።

ብዙውን ጊዜ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች፣ አትራፊ የሆኑና በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ የሆኑ ምግቦችን በብዛት ያመርታሉ። ሎብስተሮችን ግን በብዛት ማምረት አልተቻለም። በአብዛኛው የሎብስተር አስጋሪዎች በግል ተዳዳሪ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው። እነሱም እንደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ወዳሉት የሎብስተሮች ተፈጥሯዊ መኖሪያ ሄደው ያጠምዷቸዋል እንጂ በሰው ሠራሽ ዘዴ እንዲራቡ አያደርጉም።

ሎብስተር ማስገር

ሎብስተር አጥማጆች ይህን ፍጥረት የሚይዙት እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ንቁ! በባር ሃርበር፣ ሜይን የሚኖረውን ጃክን አነጋግሯል፤ የጃክ ቤተሰብ ከቅድመ አያቶቹ ጀምሮ ሎብስተር ያጠምዱ ነበር። ጃክ ይህን ሥራ የጀመረው በ17 ዓመቱ ሲሆን ዛሬም ሎብስተር የሚያጠምደው ቅድመ አያቱ ያሰግር በነበረበት የባሕር ዳርቻ ነው። የጃክ ሚስት የሆነችው አኔትም በዚሁ የሥራ መስክ ተሰማርታለች። “ይህን ሥራ የጀመርኩት ዓሣ አስጋሪ በማግባቴ ነው” ትላለች። “ለሁለት ዓመት በጃክ ጀልባ ላይ ሆኜ ይህን ሙያ ስማር ከቆየሁ በኋላ የራሴን ጀልባ ገዛሁ።”

ጃክና አኔት ሎብስተር የሚያጠምዱት እንዴት ነው? አኔት እንዲህ ብላለች፦ “አራት ማዕዝን ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ ሣጥን መሰል ማጥመጃ እንጠቀማለን፤ ማጥመጃው ትንሽ አፍ ያለው ሲሆን ሎብስተሮቹን ለመማረክ ስንል ሄሪንግ የተባለውን ዓሣ እንደ ወንፊት ባለ ከረጢት አድርገን ማጥመጃው ውስጥ እናስቀምጣለን።” ማጥመጃው ባሕር ውስጥ ሲገባ ስለማይታይ ዓሣ አስጋሪዎቹ እያንዳንዱ ማጥመጃ ላይ ከላይ የሚንሳፈፍ ምልክት ያስራሉ። አኔት “ዓሣ አስጋሪዎቹ የየራሳቸውን ማጥመጃ ለይተው ለማወቅ እንዲችሉ ምልክቶቹን የተለያየ ቀለም ይቀቧቸዋል” ብላለች።

ማጥመጃው ወደ ባሕር ሲጣል ወደ ታች ጠልቆ ይወርዳል፤ የተለያየ ቀለም ያላቸው ምልክቶችም ከላይ ስለሚንሳፈፉ ዓሣ አስጋሪዎቹ ማጥመጃቸው የት ጋ እንዳለ ማወቅ ይችላሉ። አኔት እንዲህ ብላለች፦ “ማጥመጃዎቹን ለጥቂት ቀናት ውቅያኖሱ ውስጥ እንዲቆዩ ካደረግን በኋላ ተመልሰን እናወጣቸዋለን። ማጥመጃው ውስጥ ሎብስተር ገብቶ ካገኘን አውጥተን እንመትረዋለን።” እንደ ጃክና አኔት ያሉት ጠንቃቃ ዓሣ አስጋሪዎች ትናንሾቹን ሎብስተሮች ወደ ባሕር መልሰው ይጥሏቸዋል፤ አንዳንድ እንስት ሎብስተሮችም እንቁላል እንዲጥሉ ሲባል ወደ ባሕሩ ይመለሳሉ።

ከዚህ በኋላ ዓሣ አስጋሪዎቹ የሰበሰቧቸውን ሎብስተሮች በሕይወት እንዳሉ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወደብ ሄደው ለሽያጭ ያቀርቧቸዋል። በማኅበር ተደራጅተው ከሚሠሩ አንዳንድ ዓሣ አስጋሪዎች በቀር ኮንትራት ወስደው የሚሸጡም ሆነ የሚገዙ ሰዎች የሉም፤ ሻጮቹም ሆኑ ገዥዎቹ የአካባቢው ሰዎች ናቸው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሰው ሠራሽ የማራቢያ ዘዴዎች በሎብስተር ሥራ ላይ ተጽዕኖ አላሳደሩም። ጃክ እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ሎብስተር አቅራቢዎች እንቁላል ጣይ የሆኑ እንስት ሎብስተሮችን እንዲሰበስቡ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። እንቁላሉን ካስቀፈቀፉ በኋላ ትናንሾቹን ሎብስተሮች ለጥቂት ጊዜ ያሳድጉና ወደ ባሕር ይለቋቸዋል። ይህን ማድረጋቸው በርካታ ሎብስተሮች በሕይወት እንዲተርፉ አስተዋጽኦ ያደርጋል።”

የሎብስተር አስጋሪነት ቀላል ወይም የሚያከብር ሥራ ላይሆን ይችላል። እነዚህ አስጋሪዎች ግን ሥራቸው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንዳሉ ይናገራሉ፤ ከእነዚህም መካከል የራሳቸው አነስተኛ ንግድ ያላቸው መሆኑ የሚሰጣቸው ነፃነት፣ ከማኅበረሰባቸው ወይም ከቤተሰባቸው የተረከቡትን ሥራ መቀጠላቸው እንዲሁም በባሕር ዳርቻዎች መኖርና መሥራት የሚያስገኘው ደስታ ይገኙበታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ተወዳጅ የሆነው ምርታቸው በመላው ዓለም የሚኖሩ ተመጋቢዎችን አምሮት እንደሚቆርጥ ማወቃቸው ጥልቅ እርካታ ያስገኝላቸዋል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ሎብስተር ማስገር ያለው አደጋ

ሎብስተር ማስገር አደገኛ ያልሆነ ሥራ ሊመስል ይችላል። ሐቁ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከሥራ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚሠራው የዩናይትድ ስቴትስ ተቋም እንደሚለው ከሆነ “ከ1993 እስከ 1997 በነበሩት ዓመታት በሜይን ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው 100,000 ሎብስተር አስጋሪዎች መካከል 14ቱ በሥራቸው ላይ ባጋጠማቸው አደጋ ምክንያት ሞተዋል፤ ይህ አኃዝ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በሌሎች የሥራ መስኮች በሙሉ ከሚሞቱት ሰዎች አማካይ ቁጥር ከ2 እጥፍ በላይ ይበልጣል። በሌሎች የሥራ መስኮች ላይ ከ100,000 ሠራተኞች መካከል የሚሞቱት በአማካይ 4.8 የሚያህሉ ናቸው።”

የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ድርጅት ያደረገው ምርመራ እንዳሳየው “ብዙውን ጊዜ የሎብስተር አስጋሪዎች ማጥመጃዎቹ ላይ በታሰረው ገመድ ሲጠላለፉ በማጥመጃው ክብደት ተስበው ወደ ባሕሩ ይወድቃሉ፤ እነዚህ አስጋሪዎች ራሳቸውን ማላቀቅ ወይም ወደ ጀልባው ተመልሰው መውጣት ካልቻሉ ይሰምጣሉ።” ከ1999 እስከ 2000 ባለው ጊዜ ውስጥ በ103 የሎብስተር አስጋሪዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው ከ4 አስጋሪዎች መካከል 3ቱ በሆነ ወቅት ላይ በማጥመጃው ገመድ ተጠላልፈው እንደነበረ ገልጸዋል፤ በእርግጥ ከጀልባው ተጎትተው ወደ ባሕሩ የወደቁት ሁሉም አይደሉም። የሎብስተር አስጋሪዎች የተጠላለፉበትን ገመድ ቆርጠው ለመውጣት የሚያስችላቸው መሣሪያ እንዲኖራቸው ወይም መጀመሪያውኑ እንዳይጠላለፉ የሚያደርግ የደኅንነት እርምጃ እንዲወስዱ ሐሳብ ቀርቧል።

[በገጽ 10,11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. ጃክ የሎብሰተር ማጥመጃውን ጎትቶ ሲያወጣ

2. አኔትና ጃክ ሎብስተሮቹን ከማጥመጃው ሲያወጡ

3. የእያንዳንዱ ሎብስተር ርዝመት ይለካል