በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሪህ​—መንስኤውና ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮች

ሪህ​—መንስኤውና ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮች

ሪህ​—መንስኤውና ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮች

ሪህ በጣም ከተለመዱት የአርትራይተስ በሽታ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ከፍተኛ ሥቃይ ሊያስከትል ይችላል። “ሪህ፣ ሰውነት ዩሪክ አሲድን በተገቢው መንገድ ማስወገድ ባለመቻሉ ምክንያት የሚመጣ ችግር” እንደሆነ አርትራይተስ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። መጽሐፉ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሪህ መንስኤው በግልጽ የሚታወቅ ሕመም ነው፤ ይህ ሕመም የሚከሰተው በመገጣጠሚያዎች መሃል ባለው ፈሳሽ (ሲኖቪያል ፍሉይድ) ውስጥ የዩሪክ አሲድ ቅንጣቶች ሲኖሩ ነው። ሪህ የሚያጠቃው መገጣጠሚያዎችን በተለይም በእግር አውራ ጣት ውስጥ የሚገኙትን ነው።”

ዩሪክ አሲድ፣ የሪህ በሽተኛ በሆኑ ሰዎች ደም ውስጥ የሚገኝ ከሰውነት ሊወገድ የሚገባ ነገር ነው፤ ዩሪክ አሲድ የሚፈጠረው ፕዩሪን ከተባሉት ንጥረ ነገሮች ነው። አብዛኛውን ጊዜ ዩሪክ አሲድ በሰውነት ውስጥ የሚጠራቀመው በሽንት አማካኝነት በተገቢው መጠን ባለመወገዱ ነው። በዚህ ጊዜ መርፌ መሰል የዩሪክ አሲድ ቅንጣቶች በእግር አውራ ጣት መገጣጠሚያ ላይ ሊከማቹ ይችላሉ፤ እርግጥ ነው፣ እነዚህ ቅንጣቶች በሌሎች የሰውነት መገጣጠሚያዎች ላይም ሊጠራቀሙ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት መገጣጠሚያው ስለሚቆጣ ያብጣል ብሎም ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትላል፤ እንዲሁም ሲነኩት ያተኩሳል። * አልፍሬድ የሚባል አንድ የሪህ ሕመምተኛ የታመመው ክፍል “በትንሹ ቢነካ እንኳ በጦር የተወጋ ያህል በጣም ያሠቃያል” ብሏል።

አርትራይተስ አውስትራሊያ ያወጣው መረጃ እንዲህ ይላል፦ “የሪህ ሕመም አንድ ጊዜ ከተቀሰቀሰ በኋላ ሕክምና ካላገኘ በአብዛኛው ለአንድ ሳምንት ያህል ይቆያል። ከዚያ በኋላ ለወራት እንዲያውም ለዓመታት ሕመሙ ድጋሚ ላይነሳ ይችላል። የሪህ ሕመምተኛ ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረገ ሕመሙ ቶሎ ቶሎ ሊቀሰቀስ፣ እያየለ ሊሄድ እንዲሁም በመገጣጠሚያዎች ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ሪህ ሥር የሰደደ ሕመም የሚሆንበት ጊዜም አለ።”

ሪህ በሕክምና ልንቆጣጠራቸው ከምንችል የአርትራይተስ ዓይነቶች አንዱ ነው። በሽታውን ለማከም በአብዛኛው የሚወሰዱት መድኃኒቶች ስቴሮይድ ያልሆኑ የሕመም ማስታገሻዎች ናቸው፤ በሽታው በተደጋጋሚ የሚያገረሽና ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ አሎፑሪኖል የተባለው ዩሪክ አሲድ እንዳይፈጠር የሚረዳ መድኃኒት ይወሰዳል። ሪህ እንዳያገረሽ ማድረግ ይቻላል? አዎ፣ ሕመምተኛው በሽታውን የሚያባብሱትን ነገሮች ካወቀ እንዳያገረሽበት ማድረግ ይችላል።

ሪህ እንዲያገረሽ የሚያደርጉ ነገሮች

ለሪህ በሽታ ዋነኛ መንስኤ የሚሆኑት ዕድሜ፣ ፆታና የዘር ውርስ ናቸው። አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕመምተኞች በበሽታው የሚሠቃይ የቤተሰብ አባል ያላቸው ናቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አልፍሬድ “አባቴም ሆነ አያቴ ሪህ ነበራቸው” ብሏል። ከዚህም በላይ፣ ሪህ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠቃው ወንዶችን በተለይ ደግሞ በ40 እና በ50 ዓመት መካከል ያሉትን ነው። ወንዶች በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከሴቶች በሦስት ወይም በአራት እጥፍ ይበልጣል፤ እንዲያውም ሴቶች ከማረጣቸው በፊት በበሽታው የመያዝ አጋጣሚያቸው እጅግ አነስተኛ ነው።

ከመጠን ያለፈ ውፍረትና አመጋገብ፦ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሂውማን ኒውትሪሽን እንዲህ ይላል፦ “በአመጋገብ ሪህን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በአሁኑ ጊዜ እያተኮረ ያለው ከፍተኛ የፕዩሪን ይዘት ያላቸው ምግቦችን በማስወገድ ላይ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ከሪህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጤና ችግሮችን ለምሳሌ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን፣ ሰውነት ኢንሱሊንን በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለማዋሉ ምክንያት የሚመጣ ሕመምን እንዲሁም ዲስሊፒዲሚያን በመቆጣጠር ላይ ነው።” ዲስሊፒዲሚያ እንደ ኮሌስትሮል ያሉት ቅባቶች በደም ውስጥ መብዛታቸው የሚያስከትለው የጤና ቀውስ ነው።

ያም ቢሆን አንዳንድ ሊቃውንት ከፍተኛ የፕዩሪን ይዘት ያላቸውን እንደ እርሾና ቀይ ሥጋ ያሉትን ምግቦች እንዲሁም አንዳንድ የዓሣ ዝርያዎችን መቀነስ ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። *

መጠጥ፦ አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣት ዩሪክ አሲድ ከሰውነት እንዳይወጣ ስለሚያደርግ ክምችት ሊፈጠር ይችላል።

ሕመም፦ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ማዮ ክሊኒክ እንደገለጸው አንዳንድ የጤና እክሎች ሪህ እንዲቀሰቀስ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ከእነዚህም መካከል “የሕክምና ክትትል ያልተደረገለት ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም እንደ ስኳር ሕመም፣ በደም ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የቅባትና የኮሌስትሮል ክምችት መኖር እና የደም ቅዳ ቧንቧዎች መጥበብ ያሉ ሥር የሰደዱ የጤና ችግሮች” ይገኙበታል። በተጨማሪም ሪህ “ከድንገተኛ ሕመም ወይም ከከባድ የጤና እክል አሊያም ከአደጋ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ አልጋ ላይ ከመዋል” እና ከኩላሊት በሽታ ጋር ተያያዥነት አለው። ሪህ ብዙውን ጊዜ የእግር አውራ ጣትን የሚያጠቃው ይህ የሰውነት ክፍል በቂ ደም ስለማይደርሰውና ቀዝቃዛ ስለሚሆን ነው፤ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ዩሪክ አሲድ እንዲከማች ያደርጋሉ።

መድኃኒቶች፦ ሪህን ሊያባብሱ ከሚችሉ መድኃኒቶች መካከል ታያዛይድ ዳያሬቲክ የሚባሉትና ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የደም ግፊት ላላቸው ሕመምተኞች የሚሰጡ የሚያሸኑ መድኃኒቶች፣ አነስተኛ መጠን ያለው አስፕሪን፣ የሌላ ሰው የአካል ክፍል የተሰጣቸው ሕመምተኞች ሰውነታቸው ከአዲሱ የአካል ክፍል ጋር እንዲስማማ ለማድረግ የሚሰጡ መድኃኒቶችና ኬሞቴራፒ ይገኙበታል።

ሪህ እንዳያገረሽ የሚረዱ አምስት ቁልፍ ነገሮች

የሪህ ሕመም ከአኗኗራችን ጋር ተያያዥነት ስላለው የሚከተሉት እርምጃዎች የሪህ ሕመምተኞች በሽታው እንዳይቀሰቀስባቸው ሊረዱ ይችላሉ። *

1. ሪህ፣ ሰውነት ምግብን ጥቅም ላይ ከሚያውልበት መንገድ ጋር የተያያዘ ችግር በመሆኑ ሕመምተኞች የሚወስዱትን የካሎሪ መጠን በመቆጣጠር ጤናማ የሆነ ክብደት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም በላይ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የሰውነትን ክብደት በሚሸከሙት መገጣጠሚያዎች ላይ ጫና ይጨምራል።

2. ክብደታችሁን በፍጥነት ለመቀነስ ከፍተኛ የሆነ የአመጋገብ ለውጥ ከማድረግ ተቆጠቡ፤ እንዲህ ያለው የአመጋገብ ለውጥ በደማችሁ ውስጥ ያለውን የዩሪክ አሲድ መጠን ለተወሰነ ጊዜ ከፍ ሊያደርገው ይችላል።

3. ከእንስሳት የሚገኝ ፕሮቲን አታብዙ። አንዳንዶች፣ በቀን ውስጥ የምትመገቡት ቀይ ሥጋ (የዶሮ ሥጋንና ዓሣን ጨምሮ) ከ170 ግራም መብለጥ እንደሌለበት ይናገራሉ።

4. የአልኮል መጠጥ የምትጠጡ ከሆነ ልከኛ ሁኑ። ሪህ ካለባችሁ ከነጭራሹ አልኮል አለመጠጣቱ የተሻለ ይሆናል።

5. አልኮል የሌለባቸው መጠጦችን በብዛት ጠጡ። ይህ ዩሪክ አሲድ ከሰውነት ታጥቦ እንዲወጣ ለማድረግ ያስችላል። *

ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በልማዳችን ረገድ ልከኛ’ እንዲሁም “ለብዙ የወይን ጠጅ” የማንጎመጅ እንድንሆን የሚሰጠውን ምክር ያስታውሱናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 8, 11) አፍቃሪው ፈጣሪያችን የሚበጀንን እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የካልሲየም ፓይሮፎስቴት ቅንጣቶች በመገጣጠሚያ ውስጥ፣ በተለይም በአጥንቶች መገጣጠሚያ ላይ በሚገኙ ሽፋኖች ዙሪያ በሚፈጠሩበት ጊዜም ተመሳሳይ ሕመም ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ እንደ ሪህ ዓይነት ምልክቶች ያሉት ይህ ሕመም ከሪህ የተለየ በሽታ ሲሆን ሕክምናውም የተለየ ሊሆን ይችላል።

^ አን.9 አውስትራሊያን ዶክተር ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው በፕዩሪን የበለጸጉ እንጉዳዮችን እንዲሁም እንደ ባቄላ፣ ምስር፣ አተር፣ ስፒናችና አበባ ጎመን ያሉትን የዕፅዋት ምርቶች መመገብ “ሪህ እንደሚቀሰቅስ የሚያሳይ ማስረጃ አልተገኘም።”

^ አን.14 ይህ ርዕስ የሕክምና መመሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም። እያንዳንዱ ሕመምተኛ የሚወስደው ሕክምና የተለያየ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሕመምተኛው ከሐኪሙ ጋር ሳይመካከር የታዘዘለትን መድኃኒት ማቆም ወይም ከፍተኛ የሆነ የአመጋገብ ለውጥ ማድረግ አይኖርበትም።

^ አን.19 ይህ መረጃ የማዮ የሕክምና ትምህርትና ምርምር ተቋም በሰጠው ምክር ላይ የተመሠረተ ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/​ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የተቆጣ መገጣጠሚያ

ሲኖቪየም

[ሥዕል]

የተጠራቀሙ የዩሪክ አሲድ ቅንጣቶች