በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ በምትገኘው በጆርጂያ ሪፑብሊክ “ባለፉት አሥር ዓመታት የፍቺ ቁጥር በእጥፍ ያህል ጨምሯል።” ፍቺ ከሚፈጽሙት መካከል አብዛኞቹ ከ20 ዓመት በታች ያሉ ባለትዳሮች ናቸው።​—ፋይናንሻል፣ ጆርጂያ

በአየርላንድ ከ11 እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 17 በመቶ የሚሆኑት “በኢንተርኔት ላይ ለተዋወቁት ሆኖም በአካል አግኝተውት ለማያውቁት ሰው ሙሉ ስማቸውን ሰጥተዋል።” አሥር በመቶ የሚያህሉት ደግሞ “የኢ-ሜይል አድራሻቸውን፣ የሞባይል ቁጥራቸውን ወይም ፎቶግራፋቸውን” ጭምር ሰጥተዋል።​—ዚ አይሪሽ ሶሳይቲ ፎር ዘ ፕሪቬንሽን ኦቭ ክሩወሊቲ ቱ ቺልድረን

በመላው ዓለም ከሚደርሱ የደን ቃጠሎዎች መካከል በተፈጥሯዊ ምክንያቶች የሚከሰቱት 4 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የተቀሩት በሙሉ የሚከሰቱት በሰዎች ግዴለሽነት ወይም ሆን ተብሎ በተለኮሰ እሳት ነው።​—ፕሬሲፖርታል፣ ጀርመን

“ከ10 አሜሪካውያን አንዱ [12 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው] ማሪዋና፣ ኮኬይን፣ ሄሮይንና ሌሎች በሕግ የተከለከሉ አደገኛ ዕፆችን እንዲሁም በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን ራሱን ዘና ለማድረግ ብሎ አዘውትሮ እንደሚወስድ ተዘግቧል።”​—ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ራስን መግዛት ለተረጋጋ ሕይወት ቁልፍ ነው

“ራስን የመግዛት ችግር ያለባቸው ወጣቶች፣ ትልቅ ሰው ሲሆኑ የጤንነትና የገንዘብ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የመሳተፍ አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ እንደሚሆን ጥናቶች ያመለክታሉ” በማለት ታይም መጽሔት ዘግቧል። አንድ ሺህ በሚያህሉ ሰዎች ላይ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ 32 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ጥናት ተደርጎባቸው ነበር። “ስሜታዊ የሆኑና በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጡ ልጆች የሚፈልጉትን ለማግኘት መታገሥ ወይም ተራቸውን መጠበቅ እንደሚያስቸግራቸው” ተደርሶበታል፤ እንዲህ ያሉ ልጆች ትልቅ ሰው ሲሆኑ በበሽታ የመጠቃት፣ በዝቅተኛ ገቢ የመኖር፣ ነጠላ ወላጅ የመሆን ወይም ወንጀል የመሥራት አጋጣሚያቸው በሦስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው። ይሁን እንጂ መጽሔቱ “ራስን መግዛት መማር እንደሚቻል” ከገለጸ በኋላ “ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን መግዛት እንዲችሉ በትምህርት ቤትና በቤት ውስጥ የሚሰጣቸው ሥልጠና ወደፊት ጤናማ እንዲሁም የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል” ብሏል።

ለጥፋተኛ አሽከርካሪዎች ትምህርት መስጠት

የሕንድ ባለሥልጣናት፣ ከባድ የትራፊክ ሕግ ጥሰት የሚፈጽሙ አሽከርካሪዎችን ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ሲሉ አዲስ ዓይነት ዘዴ መጠቀም ጀምረዋል፤ ይህም አሽከርካሪዎቹ የትራፊክ ፖሊስ ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ግባቸው አሽከርካሪዎች እነሱ የሚሠሩት ጥፋት እንዴት ያለ ትርምስ እንደሚፈጥር እንዲገነዘቡ ማድረግ ነው። በሰሜን ምዕራብ ሕንድ በምትገኘው በጉርጋኦን ከተማ አሁን አሁን ፖሊሶች ጥፋተኛ አሽከርካሪዎችን ዳር አስይዞ የቅጣት ወረቀት ከመስጠት ባለፈ አሽከርካሪዎቹ ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር ሆነው ለግማሽ ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ሰዓት ትራፊክ እንዲያስተናብሩ ያደርጓቸዋል። አንዳንድ አሽከርካሪዎች ይህ ቅጣት ትምህርት ስለሰጣቸው አመለካከታቸው እንደተቀየረ አምነዋል። የከተማዋ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ባሃርቲ አሮራ “በጉርጋኦን ከተማ በየቀኑ ለጥፋተኛ አሽከርካሪዎች አንድ ሺህ የሚያክል [የቅጣት ወረቀት] እንሰጣለን” ብለዋል። አክለውም “[በመሆኑም] በየቀኑ አንድ ሺህ ተጨማሪ ‘የትራፊክ ፖሊሶችን’ ማግኘት ችለናል” በማለት ተናግረዋል።