መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ወደ አምላክ ለመጸለይ የግድ ወደ አንድ የአምልኮ ስፍራ መሄድ ይኖርብሃል?
ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ ለመጸለይ አዘውትረው ወደ ተለያዩ ሃይማኖታዊ ስፍራዎች ይሄዳሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ወዳሉት ቦታዎች ለመሄድ ረጅም መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ። አንተስ ወደ አምላክ ለመጸለይ የግድ ወደ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ክርስቲያን ወይም ሌላ የአምልኮ ስፍራ መሄድ እንዳለብህ ይሰማሃል? ወይስ ደግሞ አምላክን በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ ልታነጋግረው እንደምትችል ይሰማሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
የሰው ልጆች ሲፈጠሩ አምላክን ለማምለክ ሃይማኖታዊ ስፍራ አላስፈለጋቸውም። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሚኖሩት ውብ በሆነ የአትክልት ስፍራ ውስጥ ነበር። (ዘፍጥረት 2:8) እዚያ ሆነው ከፈጣሪያቸው ከይሖዋ አምላክ ጋር መነጋገር ይችሉ ነበር። በኋላም የሰው ልጆች እየበዙ ሲሄዱ እንደ ኖኅ ያሉ ጻድቃን ሰዎች ሃይማኖታዊ ስፍራ መገንባት ሳያስፈልጋቸው ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ማድረግ’ ችለዋል። (ዘፍጥረት 6:9) እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ይወዱና አዘውትረው ወደ እሱ ይጸልዩ ነበር፤ ይህን ያደረጉት ሃይማኖታዊ ስፍራ ሳይኖራቸው ቢሆንም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል።
አምላክ በእጅ በተሠሩ ሕንፃዎች ውስጥ አይኖርም
በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣ የምድርና የግዙፉ አጽናፈ ዓለም ፈጣሪ በእጅ በተሠሩ የአምልኮ ስፍራዎች ውስጥ እንደማይኖር ያውቁ ነበር። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን?” በማለት ጠይቆ ነበር። አክሎም “እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም” በማለት እውነታውን በትክክል ገልጿል። (2 ዜና መዋዕል 6:18) እርግጥ ነው፣ ጥንት የነበሩት እስራኤላውያን የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት ሃይማኖታዊ በዓላትን ለማክበር የሚሰበሰቡበት የመገናኛ ድንኳን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ቤተ መቅደስ ነበራቸው። (ዘፀአት 23:14-17) ይሁን እንጂ በማንኛውም ጊዜ ማለትም መንጎቻቸውን ሲጠብቁ፣ በእርሻቸው ላይ ሲሠሩ፣ በቤተሰብ ሆነው ጊዜ ሲያሳልፉ ወይም ብቻቸውን ሲሆኑ ወደ አምላክ መጸለይ ይችሉ ነበር።—መዝሙር 65:2፤ ማቴዎስ 6:6
እኛም በተመሳሳይ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ ወደ አምላክ መጸለይ እንችላለን። ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ ጸጥ ወዳሉና ገለልተኛ ወደሆኑ ስፍራዎች በመሄድ ይጸልይ ነበር። (ማርቆስ 1:35) ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት ያደረገውን ነገር ሲገልጽ “ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ” ይላል።—ሉቃስ 6:12
ኢየሱስ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ በሚደረጉ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ በታማኝነት ይገኝ ነበር። (ዮሐንስ 2:13, 14) ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል መሆኑ የሚያከትምበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል። ኢየሱስ፣ ሳምራውያን ቤተ መቅደሳቸውን በሠሩበት አንድ ተራራ አጠገብ ካገኛት ሳምራዊት ሴት ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ “በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት እየመጣ ነው” ብሏል። አክሎም እውነተኛ አምላኪዎች “አብን በመንፈስና በእውነት [እንደሚያመልኩት]” ተናግሯል።—ዮሐንስ 4:21, 23
አዎን፣ ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው በጡብ በተሠራ ሕንፃ ላይ ሳይሆን በቅን ልብ በሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ላይ ነበር። ታዲያ ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች ተብለው የተጠሩት የኢየሱስ ተከታዮች አምላክን ለማምለክ የአምልኮ ስፍራዎችን አይጠቀሙም ማለት ነው? (የሐዋርያት ሥራ 11:26) በፍጹም፤ እንዲህ የምንልበት በቂ ምክንያት አለን።
የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ እንደ አንድ ቤተሰብ ናቸው
የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደ አንድ ቤተሰብ ናቸው። (ሉቃስ 8:21) አንድ ጥሩ ቤተሰብ አብሮ መመገብን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን በጋራ ያከናውናል፤ ይህ ደግሞ የቤተሰቡን አንድነት ያጠናክራል። መንፈሳዊውን ቤተሰብ አስመልክቶም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ውስጣዊ ማንነታችንን የሚገነቡና በመካከላችን ያለውን አንድነት የሚያጠናክሩ በመሆናቸው መንፈሳዊ ድግስ ናቸው ሊባል ይችላል። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ . . . እርስ በርስ እንበረታታ።”—ዕብራውያን 10:24, 25
እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች፣ እያንዳንዱ አባል መንፈሳዊ ባሕርያትን እንዲያዳብር በመርዳት ረገድ ጉባኤ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይገነዘባሉ፤ አንድ ክርስቲያን ግን ብቻውን እነዚህን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ማዳበር አይችልም። እነዚህ ባሕርያት ፍቅርን፣ ይቅር ባይነትን፣ ደግነትን፣ ገርነትንና ሰላምን ይጨምራሉ።—2 ቆሮንቶስ 2:7፤ ገላትያ 5:19-23
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከሌሎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትና ለአምልኮ የሚሰበሰቡት የት ነበር? ብዙውን ጊዜ የሚሰበሰቡት በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ነበር። (ሮም 16:5፤ ቆላስይስ 4:15) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንድ የእምነት ባልደረባው በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በቤትህ ላለው ጉባኤ” የሚል ሐሳብ ጠቅሷል። *—ፊልሞና 1, 2
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች፣ ለአምልኮ የሚያስፈልጓቸው የተንቆጠቆጡ ሕንፃዎች ሳይሆኑ ምቹና ሁሉንም ተሰብሳቢዎች ማስተናገድ የሚችሉ ስፍራዎች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያሉ የአምልኮ ስፍራዎች ያሏቸው ሲሆን እነዚህንም የመንግሥት አዳራሽ ብለው ይጠሯቸዋል። እንዲያውም አንተ በምትኖርበት አካባቢ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ሊኖር ይችላል። እነዚህ ሕንፃዎች ለተፈለገው ዓላማ አገልግሎት የሚሰጡና ልከኛ ናቸው። በዚያ የሚካሄደው ሃይማኖታዊ ሥርዓትም የተወሳሰበ አይደለም፤ ስብሰባዎቹ መዝሙርን፣ ጸሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን ያካትታሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ለብቻቸው ሆነው ለአምላክ የልባቸውን አውጥተው በመናገር የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። በመሆኑም ጊዜ መድበው በቤተሰብም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በየዕለቱ ይጸልያሉ። ያዕቆብ 4:8 “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 “ጉባኤ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአንዳንድ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ “ቤተ ክርስቲያን” ተብሎ ተተርጉሟል።
ይህን አስተውለኸዋል?
● አምላክ በእጅ በተሠሩ ሕንፃዎች ውስጥ ይኖራል?—2 ዜና መዋዕል 6:18
● ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ያደረው የት ነበር?—ሉቃስ 6:12
● እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች አንድ ላይ መሰብሰብ ያለባቸው ለምንድን ነው?—ዕብራውያን 10:24, 25
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ወደ አንድ ስፍራ ሄደህ በመጸለይህ ልመናህ ይበልጥ ተሰሚነት እንደሚያገኝ ይሰማሃል?