የወጣቶች ጥያቄ
የማንን አርዓያ ብከተል ይሻላል?
አርዓያ ስለሚሆኑ ሰዎች በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች ትመለከታለህ፦
ለምን አስፈለጉ?
የት ይገኛሉ?
እንዴት ልትመስላቸው ትችላለህ?
ለምን አስፈለጉ?
የሕይወት እውነታ፦ ሰዎች፣ የሚያደንቋቸውን ግለሰቦች መምሰል ይቀናቸዋል። ይህ ደግሞ እንደምታደንቀው ሰው ማንነት፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል።
የሚያስፈልግህ፦ ጥሩ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ማግኘት።—ፊልጵስዩስ 3:17
ችግሩ፦ ብዙ ሰዎች እንደ አርዓያ አድርገው የሚመለከቱት ዝነኛ የሆኑ ሰዎችን ለምሳሌ ሙዚቀኞችን፣ ታዋቂ ስፖርተኞችን ወይም የፊልም ተዋንያንን ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች የጎደፈ ስም ቢኖራቸውም እንኳ እነሱን ከመከተል ወደኋላ አይሉም።
ልታስብበት የሚገባ ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስብዕናችንን ከልብስ ጋር ያመሳስለዋል። (ቆላስይስ 3:9, 10) ልብስ ልትገዛ ገበያ ብትወጣ ጥሩ አለባበስ የሌለው ሻጭ እንዴት መልበስ እንዳለብህ ቢነግርህ ትቀበለዋለህ? ታዲያ የጎደፈ ስም ያለው አንድ ታዋቂ ሰው የአንተን ስብዕና እንዲቀርጸው ልትፈቅድለት ይገባል? እንዲህ ከማድረግ ወይም በጭፍን ብዙኃኑን ከመከተል ይልቅ ጥሩ አርዓያ የሚሆኑህ ሰዎች መምረጥህ (1) ልታዳብር የምትፈልጋቸውን ባሕርያት ለይተህ ለማወቅ የሚረዳህ ሲሆን (2) እነዚህን ባሕርያት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ለመምሰልም ያስችልሃል።
የት ይገኛሉ?
እውነት ወይም ሐሰት በል።
1. አርዓያ ሊሆንህ የሚገባው በአካል የምታውቀው ሰው ብቻ ነው።
□እውነት □ሐሰት
2. አርዓያ የሚሆንህ ሰው ፍጹም መሆን አለበት።
□እውነት □ሐሰት
3. በርካታ ሰዎች አርዓያ ሊሆኑልህ ይችላሉ።
□እውነት □ሐሰት
መልስ
1. ሐሰት። በጥንት ዘመን ከኖሩ ሰዎች መካከልም እንኳ አርዓያ የሚሆኑህ ሰዎች ማግኘት ትችላለህ። ከእነዚህም መካከል የተሻሉ ምሳሌዎች የምታገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ለአብነት ያህል፣ ዕብራውያን ምዕራፍ 11ን ብታነብ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ የሚሆን እምነት ያላቸው 16 ወንዶችና ሴቶችን በስም እንደጠቀሰ ማየት ትችላለህ። ጳውሎስ በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ክርስቲያኖች ኢየሱስን “በትኩረት በመመልከት” እንዲከተሉት የመከራቸው መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዕብራውያን 12:2) ከሁሉ የላቀው አርዓያችን ኢየሱስ ነው።—ዮሐንስ 13:15 *
2. ሐሰት። ከኢየሱስ በቀር የአዳም ዘሮች በሙሉ ፍጹም አይደሉም። (ሮም 3:23) ደፋር የነበረው ነቢዩ ኤልያስም እንኳ “እንደ እኛው . . . ሰው ነበር።” (ያዕቆብ 5:17) የሙሴ እህት ስለሆነችው ስለ ማርያም እንዲሁም ስለ ዳዊት፣ ዮናስ፣ ማርታ፣ ጴጥሮስና የመሳሰሉት ሰዎችም ቢሆን እንዲሁ ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ምንም ሳይደብቅ ይናገራል። ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ነገሮችን ስላከናወኑ ጥሩ አርዓያ ሊሆኑን ይችላሉ።
3. እውነት። አርዓያ የሚሆኑ በጣም ብዙ ሰዎችን ማግኘት ትችላለህ። አንዳንዶች ትጉህ ሠራተኛ ሌሎች ደግሞ ታጋሽ ሊሆኑ ይችላሉ። ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ብሩሕ አመለካከት ይዘው መቀጠል የሚችሉ ሰዎችም አሉ። (1 ቆሮንቶስ 12:28፤ ኤፌሶን 4:11, 12) የሌሎችን መልካም ጎን ለማስተዋል የምትሞክር ከሆነ ልትኮርጃቸው የምትችል ባሕርያት እንዳላቸው መገንዘብህ አይቀርም።—ፊልጵስዩስ 2:3
እንዴት ልትመስላቸው ትችላለህ?
1. አስተውል። አርዓያ ሊሆኑህ የሚችሉ ሰዎችን ፈልግ። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች “እኛ ከተውንላችሁ ምሳሌ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚመላለሱትን . . . ልብ ብላችሁ ተመልከቱ” ብሏቸው ነበር።—ፊልጵስዩስ 3:17
2. ተዋወቅ። የሚቻል ከሆነ አርዓያ እንዲሆኑህ ከመረጥካቸው ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፍ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” ይላል።—ምሳሌ 13:20
3. አሰላስል። አርዓያህ እንዲሆን የመረጥከው ግለሰብ ባሉት መልካም ባሕርያት ላይ አሰላስል። ዕብራውያን 13:7 “ምግባራቸው ያስገኘውን ውጤት በጥሞና [በማስተዋል] እምነታቸውን ኮርጁ” ይላል።
ታዲያ አርዓያ የሚሆንህ ሰው ለመፈለግ ዝግጁ ነህ? ከሆነ ከታች ያለውን መልመጃ እንድትሠራ እንጋብዝሃለን።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
አንድ ባሕርይ ምረጥ። ልታዳብረው የምትፈልገው ባሕርይ ምንድን ነው? (ይበልጥ ተግባቢ፣ ለጋስ፣ ትጉህ ሠራተኛ፣ ብርቱ ወይም እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን ትፈልጋለህ?)
․․․․․
አንድ ሰው ምረጥ። ልታዳብረው የምትፈልገውን ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ሰው ታውቃለህ? *
․․․․․
ጥሩ አርዓያ የሚሆንልህ ሰው ስትመርጥ ግብህ የዚያ ሰው ግልባጭ መሆን አይደለም። አንተ ራስህ ልዩ የሚያደርጉህ መልካም ባሕርያት እንዳሉህ ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ጥሩ አርዓያ የሚሆኑህ ሰዎች ካገኘህ እነዚህ ሰዎች አዋቂ ስትሆን መልካም ባሕርያትህ ይበልጥ ጎልተው እንዲወጡ ይረዱሃል። ከዚህም ሌላ የእነሱን ምሳሌ በመከተል አንተም ለሌሎች ጥሩ አርዓያ መሆን ትችላለህ።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን በእንግሊዝኛ ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.21 እርግጥ ነው፣ በዘመናችን ያሉ ብዙ ሰዎችም ጥሩ አርዓያ ሊሆኑልህ ይችላሉ። ለአብነት ያህል ወላጆችህ፣ ወንድምህ ወይም እህትህ፣ በመንፈሳዊ የጎለመሰ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ወይም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሌላ የምታውቀው ወይም ተሞክሮውን ያነበብከው ሰው ጥሩ አርዓያ ሊሆንልህ ይችላል።
^ አን.32 ይህን መልመጃ ስትሠራ ቅደም ተከተሉን ማገላበጥም ትችላለህ። በመጀመሪያ፣ የምታደንቀውን ሰው አስብ። ቀጥሎ፣ ‘ይህን ሰው እንዳደንቀው ያደረገኝ የትኛው ባሕሪው ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም የዚህን ሰው አርዓያ በመከተል የምታደንቅለትን ባሕርይ ለመኮረጅ ጥረት አድርግ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የጎደፈ ስም ያለው አንድ ታዋቂ ሰው የአንተን ስብዕና እንዲቀርጸው ልትፈቅድለት ይገባል?
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እኩዮችህ ምን ይላሉ?
ሌይላ—ጓደኛዬ ሳንድራ የነገሮችን መልካም ጎን ለማየት ትጥራለች። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ታውቀዋለች። በዚህ ምክንያት መፍትሔ የማታገኝለት ችግር ያለ አይመስለኝም። ትልቅም ሆነ ትንሽ፣ ችግር ባጋጠመኝ ቁጥር አማክራታለሁ።
ቴረንስ—ካይልና ዴቪድ የተባሉት ጓደኞቼ ለሌሎች ስሜት ምንጊዜም ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። የራሳቸውን ጉዳይ ወደ ጎን ተወት አድርገው ሌሎችን በችግራቸው ለመርዳት ሁልጊዜ ዝግጁ ናቸው። ትልቅ ምሳሌ ሆነውኛል።
ኤመሊን—ለእኔ አርዓያ የምትሆነኝ እናቴ ናት። መጽሐፍ ቅዱስን በቃሏ ታውቀዋለች ማለት እችላለሁ፤ ደግሞም ሁልጊዜ ስለ እምነቷ ለሌሎች ለመናገር አጋጣሚ ትፈልጋለች። አገልግሎት አሰልቺ ሥራ ሳይሆን ልዩ መብት እንደሆነ ይሰማታል። እንዳደንቃት ያደረገኝ ይህ ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት፦
ጥሩ አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች ለማግኘት እርዳታ ትፈልጋለህ? ዕብራውያን ምዕራፍ 11ን አንብብና እዚያ ላይ ከተጠቀሱት ወንዶችና ሴቶች መካከል አንዳቸውን ምረጥ። ከዚያም የመረጥከው ግለሰብ ያሉትን ግሩም ባሕርያት መምሰል እንድትችል ስለ ግለሰቡ ምርምር አድርግ።
በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጁት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተሰኙ መጻሕፍት ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) እና ጥራዝ 2 ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አርዓያ የሚሆኑ ሌሎች ሰዎችን ማግኘት ትችላለህ። በእያንዳንዱ መጽሐፍ የጀርባ ሽፋን የውስጥ ገጽ ላይ ያለውን “አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች ማውጫ” ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?
ወላጆችህን በአንተ ዕድሜ እያሉ እና አሁን አርዓያ ስለሆኗቸው ሰዎች ጠይቃቸው። ወላጆችህ፣ አርዓያ የሚሆኗቸው ሰዎች ማግኘታቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?